Ethiopianism

ኢትዮጵያን ለመዝረፍና ለማፍረስ የመጣ ቡድን ለሀገር እድገትና ብልፅግና ሰርቶ አያውቅም! ስዩም ተሾመ

ስዩም ተሾመ

ዋልታ ቴሌቪዥን ከሜ/ጄ አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) ያደረገው ቃለ-ምልልስ ዛሬ ከምሽቱ 2፡30 ላይ እንደሚተላለፍ ለማሳወቅ በድረገፁ ላይ ያወጣውን ማስታወቂያ ስመለከት ደንገት ነገር ከጆሮዬ ጥልቅ አለ። በዚህ ማስታወቂያ ውስጥ ጆቤ “ባለፉት አመታት ምንም አልተሰራም ማለት አይቻልም። 


ለምሳሌ ፕ/ት ኢሳያስ አፍወርቂ እየተመላለሰ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ምረቃ ላይ በመገኘት ይጎበኛል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ባለፉት ስድስት ወራት የተሰሩ አይደሉም” በማለት ይናገራል።

በእርግጥ ባለፈው አመት ሐምሌ ወር ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ጆቤን በአካል አግኝቼው ነበር። በግልና በይፋ ለጆቤ ያለኝን አድናቆትና አክብሮት ገልጬያለሁ። ከህወሓቶች ውስጥ የተሻለ ግንዛቤ እና ዕውቀት አለው።  

እውነት ለመናገር አሁን መቀሌ የመሸጉት የህወሓት አመራሮች እና ልሂቃን አንድ ላይ ቢጨፈለቁ የጆቤን ያህል ዕውቀትና ግንዛቤ ያላቸው አይመስለኝም። ነገር ግን የህወሓትን ትክክለኛ ባህሪና ዓላማ ከመረዳት አንፃር ጆቤም ቢሆን የተወሰነ የግንዛቤ ችግር አለበት። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ከላይ ያነሳሁት ጉዳይ ነው።

ጆቤን ጨምሮ ብዙ የፖለቲካ ልሂቃን “ባለፉት 27 አመታት ውስጥ በተለይ ከመሰረተ ልማት ግንባታና መስፋፋት አንፃር ጥሩ ስራዎች ተሰርተዋል። የኢኮኖሚ ልማትና እድገት ተመዝግቧል። ስለዚህ የህወሓት የበላይነት በሰፈነበት ወቅት ምንም ነገር አልተሰራም አትበሉ” ሲሉ ይደመጣሉ።  

የትኛውም የፖለቲካ ቡድን ቢሆን አንፃራዊ የኢኮኖሚ ልማትና እድገት ማስመዝገብ ከተሳነው፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን መገንባትና ማስፋፋት ካልቻለ፣ 27 አመት ቀርቶ 7 ወር በስልጣን ላይ መቆየት አይችልም።

እ.አ.አ ከ2006 – 2010 ዓ.ም ድረስ የእድገትና ልማት ኮሚሽን (Comission on Growth and Development) ሊቀመንበርና ከሌሎች ሁለት የዘርፉ ምሁራን ጋራ በ2001 ዓ.ም በስነ-ምጣኔ (ኢኮኖሚክስ) የአለም ኖቤል ሎሬት አሸናፊ የሆነው ሚካኤል ስፔንስ (Michael Spence) በሰጠው አስተያየት ፣ በመጀመሪያ የእድገት ደረጃ ላይ ባሉ ሀገራት (early – stage developing countries) በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት በቅድሚያ የኢኮኖሚ እድገት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቅሳል።  


ከዚሁ ጋር አያይዞ፣ የአንድ ሀገር ልማትና እድገትን ለማስቀጠል የመንግስት አስተዳደር (Governance) እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይገልፃል። በዚህ መሰረት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የሚመዘገበው ለውጥና መሻሻል አራት ደረጃዎች አሉት። እነሱም፡- ህልውና (Survival)፣ እድገት (Growth)፣ ልማት (development) እና ብልፅግና (Evolution) ናቸው።

በየትኛውም ሀገር ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ቀዳሚው ተግባር የሀገሪቱን አስተዳደራዊ መዋቅር መዘርጋት እንደ አዲስ መዘርጋት ወይም የነበረውን ማሻሻል ነው።

የደርግ ሥርዓትን በኃይል አስወግዶ ወደ ስልጣን የመጣው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት የመጀመሪያዎቹን አስር አመታት አዲስ ፖለቲካዊ አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋትና ሥርዓቱን ህልውና በመጠበቅ ላይ ተወጥሮ የነበረበት ወቅት ነው።  

ለምሳሌ፣ በሽግግሩ ወቅት እንደ ኦነግና ኦብነግ ካሉ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር የነበረው ፍጥጫና ግጭት፣ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ ህወሓት ውስጥ የተከሰተው መከፋፈል እና የመሳሰሉት በመንግስታዊ ሥርዓቱ ህልውና ላይ አደጋ ላይ ጥሎታል።

በዚህ መሰረት ከ1983 – 1994 ዓ.ም ባሉት አመታት ህወሓት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ፖለተካ ውስጥ ህልውናውን ለማረጋገጥ የሚውተረተርበት ወቅት ነበር። ለምሳሌ “Trading Economics” ድረገፅ መረጃ መሰረት በእነዚህ አመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ይዋዥቅ ነበር።  


ስለዚህ እንደ ህወሓት ያለ የፖለቲካ ቡድን የራሱን ህልውና ለማረጋገጥ ሲል ፈጣን እና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል። ስለዚህ ህወሓት/ኢህአዴግ ህልውናውን ማረጋገጥ የቻለው ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ በመቻሉ ነው። ይህን ደግሞ ከታች ባለው ምስል ላይ መመልከት ይቻላል።
ምስል 1፡ የኢትዮጲያ አመታዊ የምርት መጠን እድገት፣ ከ1991 – 2014 (1983 – 2007) ዓ.ም
ከላይ በተገለፀው መሰረት ከ1995 – 2005 ዓ.ም (ከ2003 – 2013) ባሉት ሁለተኛ አስር አመታት ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል። በዚህ ወቅት የመንግስትና የህዝብ ትኩረት በዋናነት በሀገሪቱ የኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ይሆናል። 

የፖለቲካ መብትና ነፃነት ጥያቄን በቁሳዊ ሃብትና ጥቅም በመሸፋፈን ማለፍ ይቻላል። ይሁን እንጂ የፖለቲካ ጥያቄን በቁሳዊ ሃብትና ጥቅም መደለል አይቻልም።

ሀ) የኢኮኖሚ እድገቱ ፍጥነት በነበረበት ማስቀጠል አይቻልም።

በእርግጥ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እየገዘፈ በሄደ ቁጥር የሚያድግበት ፍጥነት ይቀንሳል። ከላይ በምስል ላይ እንደሚታየው የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት በፍጥነት እያደገ ቢመስልም፣ ቀጥሎ ባለው ምስል ላይ ግን ፍጥነቱን እየቀነሰ እንደሆነ በግልፅ ይታያል። 

በመጀመሪያዎቹ አስር አመታት የሚታየው የኢኮኖሚ እድገት በዋናነት ከመንግስት የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያዎች ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው። በመቀጠል፣ በ2ኛው አስር አመት ለሚታየው የኢኮኖሚ እድገት የመንግስት ድጋፍና ማበረታቻ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። 

በሦስተኛው አስር አመትና ከዚያ በኋላ ባሉት አመታት ግን መንግስት ድጋፍና ማበረታቻ የመስጠት አቅሙ እየቀነሰ ይመጣል። ከዚህ በኋላ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት መሰረቱ አዳዲስ ፈጠራዎችና ቴክኖሎጂዎች፣ የምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ አሰራሮች እና አደረጃጀቶች ይሆናሉ።
ምስል 2፡ የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት፣ ከ2003 – 2014 (1995 – 2006) ዓ.ም
ለ) ተከታታይ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት የሚጨምረው እሴት ዝቅተኛ ይሆናል።

ሁለቱም መንግስታት የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል ጠንክረው እየሰሩ ቢሆንም፣ የህዝቡ ጥያቄ ግን ከቀድሞው የተለየና ሰፊ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ላይ የታየው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ቁሳዊ ሃብትና ንብረት በሕብረተሰቡ ዘንድ የነበራቸውን ዋጋ ያሳጣቸዋል። 


አንድ ደቡብ ኮሪያዊ በወቅቱ በዚህ ወቅት ስለነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ባደረገው ጥናት (pdf) የሚከተለውን የማጠቃለያ ሃሳብ አስቀምጧል፦
“…it can be generalized that a bureaucratic authoritarian regime will not be efficient unless it can co-opt societal interests, especially when prolonged economic success nullifies the effectiveness of material gains at the cost of political freedom”

ሐ) ዴሞክራሲ በራሱ የኢኮኖሚውን እድገትን ለማስቀጠል ዋና ግብዓት ስለሆነ።
የኢኮኖሚ እድገቱን ከማስቀጠል ጋር ተያይዞ በተራ.ቁ (ሀ) ላይ እንደተገለፀው፣ ከሦስተኛው አስር አመት በኋላ የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት በዋናነት በአዳዲስ ፈጠራዎችና ቴክኖሎጂዎች፣ የምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ የተሻሻሉ የአሰራር ዘዴዎች እና አደረጃጀቶች ላይ የተመሰረተ ነው። 


መንግስት ምንም ያህል በጀትና ድጋፍ ቢያደርግ ዜጎች አዳዲስ ፈጠራዎች፣ ቴክኖሎጂዎች እና አሰራሮችን እንዲፈጥሩ ማድረግ አይችልም። ነፃ የመረጃ ፍሰት በሌለበት፣ ሃሳብን በነፃ መግለፅ በማይቻልበት እና በራስ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ በማይቻልበት ሁኔታ ለአዳዲስ ፈጠራዎች ምቹ የሆነ አከባቢ መፍጠር አይቻልም። በመሆኑም የዴሞክራሲ ጥያቄ እንደ አማራጭ የሚቀርብ ሳይሆን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገቱ የማስቀጠል ወይም ያለማስቀጠል ጥያቄ ነው።

ከላይ በተገለጸው መሰረት፣ እንደ ህወሓት/ኢህአዴግ ያለ መንግስት ወደ ስልጣን በመጣ የመጀመሪያ አስር አመታት የመንግስታዊ ሥርዓቱን ህልውና ለማረጋገጥ ጥረት ያደርጋል። የራሱን ህልውና ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት በቀጣይ አስር አመታት ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘግባል። የኢኮኖሚ እድገቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል በሚያደርገው ጥረት በፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ ስር-ነቀል ልውጥና መሻሻል ያደርጋል።

በዚህ መሰረት የዜጎች ፖለቲካዊ መብትና ነፃነትን ያከብራል፥ ያስከብራል፣ በመንግስት ሥራና አሰራር ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያደርጋል። በዚህ መልኩ የኢኮኖሚ እድገትና ፖለቲካዊ ለውጥን በጥምረት ማካሄድ ሲቻል በአራተኛው አስር አመታት የበለፀገ ኢኮኖሚ እና የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት ይቻላል። 


ስለዚህ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት መገምገም ያለበት የራሱን ህልውና ለማረጋገጥ ሲፍጨረጨር ባስመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት አይደለም። ከዚያ ይልቅ የኢኮኖሚ እድገቱን ቀጣይነት ከማስቀጠል እና የዜጎችን እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንፃር በወሰደው የለውጥ እርምጃ ነው።

ህወሓት/ኢህአዴግ የራሱን ህልውና ለማረጋገጥ ባደረገው ጥረት በሁለተኛው አስር አመታት ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቧል። ነገር ግን የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች የኢኮኖሚ እድገቱን ከማስቀጠል ይልቅ ለራሳቸው መቀራመት ጀመሩ። 


ሌብነትና ዘረፋ ከኢኮኖሚ እድገቱ በብዙ እጥፍ ፍጥነት አደገ። ብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ከኢኮኖሚ እድገቱ ተጠቃሚ ከመሆኑ በፊት ከገዢው ፓርቲ ጋር የቀረበ ግንኙነትና የጥቅም ትስስር ያላቸው ጥቂት ሰዎች ተቀራመቱት። በሦስተኛው አስር አመት መጀመሪያ (ከ2006 ዓ.ም) ጀምሮ ዜጎች የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ሲያነሱ በወታደራዊ ጉልበት ማፈንና ማዳፈን ተጀመረ። በዚህ ምክንያት ብዙዎች ለሞት፣ ስደት፣ እስራት እና እንግልት ተዳረጉ።

በአጠቃላይ ህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ያመጣው የመሰረተ-ልማት ማስፋፋትና የኢኮኖሚ እድገት የራሱን ህልውና ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ አስቦ አይደለም። ከኢኮኖሚ እድገቱ ተጠቃሚ የሆኑት የገዢው ፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እና ከእነሱ ጋር የጥቅም ትስስር ያላቸው ባለሃብቶችና ተቋማት ናቸው።  


ፖለቲካዊ ቡድኑ ለሀገርና ለህዝብ የሚሰራ ቢሆን ኖሮ በእንዲህ ያለ የዘረፋና ሌብነት ተግባር አይሰማራም፣ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በሚያነሱ ዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይፈፅም። 

ስለዚህ ባለፉት አመታት የተመዘገበው ልማትና እድገት ለራሱ ህልውና እና ጥቅም ሲል እንጂ ለኢትዮጵያን እድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ አይደለም። ኢትዮጵያን ለመዝረፍና ለማፍረስ ወደ ስልጣን የመጣ ቡድን ለእድገትና ብልፅግና ሰርቶ አያውቅም!!
ኢሳት ዜና 

ESAT DC Daily News 
Tuesday Nov 20, 2018



ኢሳት ትኩረት 

Esat Tikuret 
Tuesday November 20, 2018

No comments