Ethiopianism

ኤፈርትን የመሳሰሉ ኢንዶውመንቶች በቀጥታ የሚመለከታቸው የተመሰረቱበት ክልል ነው

ቢቢሲ አማርኛ

(ቢቢሲ አማርኛ) - በቅርቡ በሙስና ተጠርጥረው የተያዙትን የሜቴክ አመራሮች እና ሌሎችም ሰራተኞች እስር ፖለቲካዊ አንድምታ የሌለው እንዲሁም የትኛውም ብሔር ላይ ያነጣጠረ እንዳልሆነ የፌደራል አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ጡኑ ገለፁ።

ዳይሬክቶሩ ይህንን የተናገሩት ዛሬ ማለዳ የፌደራል አቃቤ ህግ የመቶ ቀናት የሥራ አቅጣጫ እና ዕቅድ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

በቅርቡ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል መንግሥት ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከከፍተኛ ሙስና ጋር በተያያዘ የተጀመረው ዘመቻ በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ጉዳዩ ከሰብዓዊ መብትና ሙስና ጥያቄዎች ወጥቶ የትግራይ ህዝብን ወደ መምታት የፖለቲካ እርምጃ ሄዷል ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ሜቴክን አስመልክቶ በተሰራው ዘጋቢ ፊልም የፍርድ ቤቱን ሂደት ያዛባል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ዝናቡ ሲመልሱም ከፍርድ ቤቱ የተለየ ነገር እንዳልቀረበና "የማንም ስም ማጥፋት አንፈልግም" ብለዋል።

የሙስናው ምርመራ በሜቴክ ብቻ የሚያቆም ሳይሆን በተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ምርመራ እንደተጀመረና፤ ምርመራው እንደተጠናቀቀም ለህዝብ እንደሚያሳውቁ የተናገሩት አቶ ዝናቡ አሁን ለእስር መነሻ የሆነው የሙስና ምርመራ ሜቴክ ላይ ብቻ ያለመጀመሩን ገልፀዋል።

"በሙስና ተጠርጥረው እየተመረመሩ ስላሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት ምንም መግለፅ አንፈልግም" ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኤፈርትን በመሳሰሉ ኢንዶውመንቶች ላይ ምርመራ ተጀምሮ እንደሆነ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም አቶ ዝናቡ ሲመልሱ በኢንዲውመንቶቹ ላይ "የተጀመረ ምንም አይነት ምርመራ የለም። እነዚህ ኢንዶውመንቶች የተመሰረቱበት ክልል ነው በቀጥታ የሚመለከታቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

ከተለያዩ አቅጣጫዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ሕገ ወጥ መሳሪያዎች የመያዛቸው መረጃ መሰራጨት ከጀመረ ውሎ አድሯል።

በተለይም ባለፉት ጥቂት ወራት ባልተለመደ መልኩ መዲናዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር መበራከቱ እየተሰማ ነው።

አቶ ዝናቡ የነዚህ ጦር መሳሪያዎች መበራከት ለውጡን ለማደናቀፍ ያለሙ እንደሆነ ገልፀዋል።

ከነዚህ ጦር መሳሪያዎች ጀርባም የተለያዩ ሀገራት፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ሀብትን ለማካበት እየተረባረቡ እንደሆነ ተናግረዋል።

የህገወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ለመቀነስ ከፌደራል አቃቤ ህግ፣ ፖሊስና ሌሎች የደህንነት ቢሮዎች የተውጣጣ ግብረ ኃይል እንደሚቋቋም ተናግረዋል። ዝውውሩን የተመለከተ ህግ በማርቀቅ ላይ መሆኑንም አክለው ግለፀዋል።

የጥላቻ ንግግር እና የህገ ወጥ የሰው ዝውውር ሌሎች ህግ እየተረቀቀላቸው ያሉ ጉዳዮች ናቸው ተብለዋል።

አቶ ዝናቡ ባለፈው ሐምሌ በተደነገገው የምህረት አዋጅ 584 ግለሰቦች ከወንጀል ነፃ የሆኑበትን የምስክር ወረቅት ወስደዋል ሲሉ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

No comments