Ethiopianism

የባሕር ማዶ ደብዳቤ፣ የሕወሃት መግለጫና አዋጇን ይመለከታል (ቁጥር ፩) ከአቢቹ ነጋ

የባሕር ማዶ ደብዳቤ፣ የሕወሃት መግለጫና አዋጇን ይመለከታል (ቁጥር ፩) ከአቢቹ ነጋ

ይድረስ ለውድ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቸ
ጉዳዮ፥ የሕወሃት መግለጫና አዋጇን ይመለከታል፤
ውድ ወገኖቸ።

ይህን ደብዳቤ ከባሕር ማዶ ስልክ ደስታና ሀዘን፤ ናፍቆትና ሲቃ ተናንቀውኛል። በተለይ ጠ/ሚ ዓብይ የሚአደርጓቸው ንግግሮች፤ የሚሰጡት አመራርና ውሳኔ፤ የሚወስዱት እርምጃ፤ የሚአስተምሩት ትምህርት ያስደሰተኝ መሆኑን ስገልጽላችሁ በሃሴት፤ ኩራትና ተነሳሽነት ነው። 


አብያችን የእግዚአብሔር ዓብይ ስጦታ ናቸው። ጥላቻን በፍቅር፤ ጉልበትን በውይይት፤ ዘረኝነትን በአንድነት ለማሸነፍ የጀመሩ፤ ያልተሄደበት መንግድ በድፍረት የጀመሩ በመሆኑ ተመስጫለሁ።  

 ለኢትዮጵያ በሰነቁት የልማትና የእድገት ዘመቻ ምርኮኛ በመሆኔ ጊዜና ሁኔታ እንዳመቸኝ ደበብዳቤ ልልክላችሁ ወስኛለሁ። የዛሬው ደብዳቤ በሕወሃት መግለጫና አዋጁ አንደምታ ላይ የሚአጠነጥን ይሆናል።

ማክሰኞ ሕዳር 4፤ 2011 ዘራፊውና ግፈኛው ክንፈ ዳኘው ሁመራ ላይ ዶላር ተሸክሞ ሲፈረጥጥ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ሰማን። ወገኖቸ ጉድ ሳይሰማ ሰኔ አይጠባ፤ ህዳር ሲታጠን እውነት ይፈተን ነው ነገሩ። በደከመ ጉልበታችሁ፤ በታጠፈ አንጀታችሁ የለመናችሁት፤ ሁሌማ የማያሳፍራችሁ ፈጣሪ ጤናና ዕድሜ ሰጧችሁ ጉዱን ማየት በመብቃታችሁ እንኳን ደስያላችሁ። 

መሰንበት ደጉ ያሳያል ደግና ክፉ አይደል የምትሉት። ግን ተረጋጉ ለ27ዓመታት የተፈጸመው ግፍ፤ ሰቆቃ፤ ዝርፊያና መከራ መችተነካና። ጤናና እድሜ ከሰጠን ብዙ እናያለን። ወገብን በቀበቶ፤ ንዴትን በጉያ፤ ሞራልን በአዕምሮ፤ ሃዘንን በድርበብ አርጋችሁ አይቀሬውን ለምስማት ዝግጁ ሁኑ። የቅድሚያ ዝግጅት ከድንገተኛ ማዕበልና ውርጅብኝ ስለሚአድናችሁ።

ምስጋና ለቴክኖሎጂ ይሁንና ዜናውን እናንተ በሰማችሁበት ስዓት ሰምቻለሁ። በምናቤ አብረን እንደፈነደቅን ተሰምቶኛል። ክንፈ ሸሽቶ ሱዳን ለመደበቅ፤ ወይም ማን ያውቃል? ስሙን ቀይሮ ወደ ሰፊው ዓለም ለመጓዝ እና በሕዝብ ላይ ለማሴር አስቦ ሳይሆን ይቀራል። 

ይህን ለጠንቋይ እንተወውና አልተሳካለትም። እንኳን ደስያላችሁ ሳልል ብቀር የኢትዮጵያ አምላክ ይገስጸኛል። ክንፈን እንዲጠፋ ያደረጉት፤ የመከሩት እና የተባበሩት የጥፋት አጋሮቹ ህውሃቶች እንደሆኑ ይገመታል። ግን ሕወሃት ይህን ለምን አደረገች ብላችሁ እንዳሰባችሁ ይሰማኛል።  

አልፈርድባችሁም እኔም አስቤዋለሁ። ለዚህ ብዙ መላምቶች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ’ እኔን የሚሰማኝን ላካፍላችሁ። በመጀመሪያ የማነው እብድ አትበሉኝና የደብረጽዮን መግለጫ የተመቸኝ መሆኑን እወቁልኝ። አይዟችሁ ተረጋጉ እብድም የሕወሃት አፈቀላጤም አይደልሁም። ተመቸኝ ያልሁበትን ምክንያት ግን እነሆ፤

አንደኛ የክንፈን ግፍና ሌብነት ከማንም በላይ የሚአውቁት ህወሃቶች ናቸው። ከደበቁት በላይ ሊደብቁት እና ሊከላከሉሊት አልተቻላቸውም። ሁለትኛ ህወሃት ከ40 ዓመታት በላይ ግብረአበሯ የነበረውን ወንጀለኛ እጁን አስራ ለዓብይ መንግስት መስጠት ውርደትና ጓዳዊ ክህደት ስለሚሆንባት ተሰውሮ ሲያመልጥ ተያዘ በሚል ገፅታዋን ለማሳመር ያሰበችው ዘዴ እንደሆነ ይሰማኛል። 

ሶስተኛ ህወሃት በትዕቢት ስለታበዬች የሚነካህ የለም ዝምብለህ ወደ ሱዳን ሽሽ የሚል መተማመኛ ተሰጥቶት ለማምለጥ የሞከረ ይመስላል። ሌላው አተያይ የህወሃት ወንጀለኞችና ዘራፊዎች ወደፊት እንደሚፈለጉና እንደሚጠየቁ ጠንቅቀው ቢያውቁም የክንፈን ያህል በወንጀል በስብስን ከርፍተናል ብለው ካለማመናቸው የተነሳ ከእስር እንተርፍ ይሆናል የሚል እሳቤ ሳይኖራቸው አይቀርም። 

እንዳሰቡት ሳይሆን ቢቀር በሚል መሰደጃ መንገዳቸውን ለመፈተሽ ክንፈን እንደ ቤትሙከራ (litmus test) የተጠቀሙበት ይመስላል።

ምንም ይሁን ምን፤ ክንፈ በለስ አልቀናውም። ደረቱን እንደነፋ እጁን በካቴና ታስሮ፤ በቢጫዋ ሄሊኮፕተር ተይዞ እስር ወርዷል። የዶክተር መረራ ትንቢት “እስር ቤቱን በደንብ ያዙት፤ ጽዳቱን ጠብቁት ለወደፊቱ ለናንተም ይሆናል” ያሉት ትንቢት እውን ሆኗል። የተማረ ይናገር ሌባም ይደናበር የሚለው ትንቢተ ቅላጼ ቃል ሆነ። ዓቢይ ቃል ይተክላል ቃል ይነቅላል ያሉትም ይህንኑ እይደል።

ይህን ትዕይንት ተከትሎ ሕወሃት መግለጫ አወጣች። በመግለጫው ብዙ ሰዎች ደስተኞች እንዳልሆኑ ጽፈዋል፤ ተናግረዋል። ወገኖቸ መግለጫው ሁላችንንም ሊመቸን ይገባል። ምክንያቱም መግለጫው ሁለት አበይት ነገሮችን ስለያዘ።  

አንደኛው፤ ሕወሃት የክንፈና ሌሎች ወንጀለኞች መያዝ እየመረራትም ቢሆን ተገቢም ህጋዊም እንደሆነ ገልጻበታለች። በዚህም “ሕገ መንግስቱ ይከበር!” እያለች በአደባባይ የምታላዝነውን ቃሏን ለማስጠበቅ ስትል የክንፈን እስር ተገቢነትና ሕጋዊነት መስክራበታለች። ለ27 ዓመት ሲሸራርፉት፤ ሲገነጣጥሉትና ያሻቸውን ሲያደርጉበት ለነበረው ሕገ መንግስት “የህግ የበላይነት ሳይሸራረፍ…” እንዲፈፀም መጠየቃቸው አስደሳች ዜና ነው።  

በሕገ መንግስቱ ላይ ያለኝ አተያይ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህን ሰንካላ ሕጋቸውን በተግባር እንዲውል በኦፊሴል ከጠየቁ ጥቅሙ ለሁላችን ነው። ይሄውም ሕግ ተብየው በተግባር ቢተረጎም ማንኛቸውም ቢሆን በአፄ ዮሐንስ ጎዳና ላይ በነፃ እንዲዘዋወሩ እያደርጋቸውም። 

ሕጉ በተግባር ከዋለ ስብሃት ነጋ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ዓባይ ፀሐየ፤ በረከት ስሞዖን፣ ጌታቸው ረዳ፣ አዜብ ጎላ፣ ዓባይ ወልዱ፣ ህላዌ ዮሴፍ፣ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አዲሱ ለገሠ፤ አባዲ ዘሙ፤ ወዘተ ቢያዙ ቅር እንደማይሰኙ ያረጋገጡበት መግለጫ ስለሆነ ሊመቸን ይገባል።

ህውሃት በመግለጫዋ ወንጀለኞች መያዛቸውን ብትደግፍም አንድን ብሔር (ከላይ የተጠቀሱትን ሰዎች በሄር ያጢኑ) ለይቶ የሚያጠቃ ስርዓትና እስራት እንዳይሆን ትምህርት መሰል ማስጠንቀቂያ ሰጣለች። ይህ ማለት ክንፈ መያዙንና ሕግ ፊት መቅረቡን እንደግፋለን ግን ትግሬን ብቻ አታጥቁ ለማለት ነው። 

በዚህም የዘር ፖለቲካ ጠበቃና አቀንቃኝ መሆኗን ብቻ ሳይሆን ወርቃማውን ወገኗን ከጥቃት የምትከላከል እንደሆነ ለወገኗ ለማንጸባረቅ ሞክራለች። የክንፈንና የሕውሃትን ውርደት የሚመለከተው ሕዝቧ እየከዳት መሆኑን ስላወቀች ደጋፍ ለማፍራት የነፋችው ጥሩምባ ይመስላል። ለእኛ ግን መግለጫው ሕዝቧ እየከዳት መሆኑን ስለሚያሳየን ሊመቸን ይገባል።

በሌላ መልኩ፤ “ክንፈንና ሌሎችን ካቅማችን በላይ በሆነ ምክንያት በቁጥጥር ሥር ማዋል ብትችሉም ከዚህ በኋላ ሌላ የህወኃት አባል እንዳይያዝ ዋስትና ስጡን” ለማለት የተፈለገ ይመስላል። ተባባሪ የሆኑ የሌላ ብሔረሰብ አባላት መከሰሳቸው የማይቀር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ህወሃት በጥቆማው እንድትተባበር እንጠይቃታለን። 

በቂ አይደሉም የሚል ጥያቄ ከሆነ ግን አንድ ምክር እንስጣቸው። ለተጠርጣሪነት በቂ የአማራ፤ የኦሮሞ ወይም ሌላ ብሄር “የብሔረሰብ ተዋፅዖ” ስለሌለ፤ የብሔረሰብ ተዋፅዖ ለማሟላት ፈቃደኛ የሆኑ ዜጎችን ይጠይቁና ፈቃደኛ የሆኑ ያልዘረፉ ወይም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያላደረሱ የሌላ ብሔረሰብ አባላት ገብተው (በደመውዝ) ያሟሉላቸው።

መግለጫው የኦሮሚያ ክልል መንግስት የህግ የበላይነት እንዲከበር እየወሰደ ያለውን እርምጃ ከማድነቅ አልፎ አጀግኗል። የክልሉ መሪ ዶ/ር ለማ መገርሳ ከአቶ ገዱ ጋር ሆነው ለውጡን ያነሳሱትና ያቀጣጠሉት ስለሆነ በተዛዋሪ የሁለቱን አመራር አድነቀው ደግፈውብታል። ድጋፉ ሶስት ዓላማ አለው። 

አንደኛው ለውጥ አምጭዎችን በማድነቅ የሕጋዊነት ካባ መልበሷን ስትገልጽበት፤ ሁለተኛው በሕወሃት ውስጥ ያሉ መሪዎች የዓብይን መደመር ፖለቲካ መቀላቀላቸውን የነገሩበት ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ሶስተኛው እንደ ሾህ የምትፈራውን እና በቀንደኛ ጠላትነት የፈረጀችውን የዐማራ ክልል ከኦሮሚያ ነጥላ ለሕዝቧና ለካድሬዎቿ ለመግለጽ የተጠቀመችበት ተራ ፖለቲካ ነው።

መግለጫው ክንፈን የፋሲካ በግ አድርገው እንደጲላጦስ ከደሙ ንጹሕ ነን ለማለት የፈለጉበት በመሆኑ ሊመቸን ይገባል። ምክንያቱም ለክንፈም ሆነ ለግብረአበሮቹ የምናወርደው እንባ፤ የምንጮኸው ጩኸት፤ የምናባክነው ጊዜ የለንም። በጥቅሉ መግለጫው ህወሃት መዳከሟን እና በበረሃ የተማማሉትን የእምነት ቃል እየናዱ ለመጠፋፋት መነሳታቸዉን አሳይቶናል። 

በእርግጠኝነት ክንፈን ጓዶቹ ክደዉታል። ድሮም ቢሆን ሌባ ሲሰርቅ ተስማምቶ የሰረቀውን ሲከፋፈል ተጣልቶ ይለያያል፤ አለያም አንዱ ሌላውን ጭዳ አርጎ ይበተናል። በፖለቲካ እግር ኳስ ቋሚ ወዳጅም ሆነ ቋሚ ጠላት የለም ለሚለው እሳቤ ጥሩ ማሳያ ነውና ይመቻችሁ።

ከክንፈ እስር በኋላ ጌታቸው አሰፋ “አሳልፋችሁ ለዓቢይ ከሰጣችሁኝ የህወሃት ጉድፍ በጄ ስለሆነ ሁላች ሁን ይዤ እስር ቤት እገባለሁ” አለ የተባለው ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። ይህም መሰረታዊ የሆነዉ ጉልበታቸዉ ማለቁን ያመለክታል። 

የፍትሕ ስርዓቱም ግለሰቦቹና ህወሃት በኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ ለፈጸሙት ጥፋት ማስረጃ ማቅረብ ሳያሻው ተጠርጣሪዎቹ ያቀርቡለታል ማለት ነው። ምን ቀረ አየር ቀለለ።

እዚህ ላይ ክንፈና ጌታቸው ጥፋታችውን ያምናሉ ወይስ አያምኑም የሚለው ጥያቄ ብዙ አያከራክረንም። ከርክር የሚኖረው ፍርዱንና ቅጣቱን እቅልሉልን ብለው ከጠየቁ ነው። የጥፋት ማቅለያና መዳኛዉ መፍትሄ አንድና አንድ ብቻ ይሆናል። 

ይሄውም አሳልፈዉ የሰጧቸውን ደም መጣጭ ጓዶቻቸው የዘረፋትን፥ የገደሉትን፥ ያጠፋትን ነገር በሙሉ በግልጽ ለመንግስትና ሕዝብ ምስጢሩን ከሰጡ፤ ህወሃት የሚባል የወሮበላ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ በራሱ ፈጣሪዎች ፈርሶ ሲአሳዩንና ሁሉም ንስሐ ሲገቡ ይጠናቀቃል።  

በዚህም ኢትዮጵያና ሕዝቧ ሃሴትን ያገኛሉ፤ እኛም ሁሉ በሱ ሆነ ተከናወነ ብለን ዝማሬ እናሰማለን። ዝማሬ መላዕክት ያሰማልን እያልን ከዶክተር ዓብይ ጋር ወደፊት።

አቢቹ ነጋ፤ ህዳር 12፤ 2011

No comments