Ethiopianism

"የኖርዌይ ፓስፖርቴን መልሼ ኢትዮጵያዊ መሆን እችላለሁ" አቶ ሌንጮ ለታ

አቶ ሌንጮ ለታ

(ቢቢሲ አማርኛ) - በኢትዮጵያ ፖለቲካ የለውጥ መንፈሱን ተከትሎ መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ ወደ አገር ውሰጥ ከተመለሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አንዱ ነው።  

በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ አንጋፋ የሆኑት አቶ ሌንጮ ለታ 'ፖለቲካ በቃኝ' እያሉ ነው የሚል መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ እየወጣ በመሆኑ አቶ ሌንጮ ለታን ስለ ጉዳዩ አነጋግረናል።

የፖለቲካ ሩጫዎን ጨርሰዋል እየተባለ ነው።
አቶ ሌንጮ፡- ፖለቲካ በቃኝ ብዬ አላውቅም፤ መረጃውን ከየት እንዳመጡት አላውቅም።

ከፓርቲ ኃላፊነትዎ ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል?
አቶ ሌንጮ፡- ገና ፈረንጅ አገር እያለሁ ጀምሮ እየጠየቅኩ ነው።ይህን ለድርጅቴም አሳውቄያለሁ፤ በይፋም ተናግሪአለሁ። ግን ራሴ ፈልጌ ነው። ገና ድርጅቱ መወሰን አለበት።

በይፋ በደብዳቤ ድርጅትዎን የጠየቁት መቼ ነው?
አቶ ሌንጮ፡- ጥያቄዬን በጽሑፍ አላቀረብኩም። ነገር ግን ለአባላት ስብሰባ ላይ በይፋ ከሚቀጥለው የማእከላዊ ኮሚቴ ምርጫ በኋላ ይሄን ኃላፊነት ተሸክሜ መቀጠል እንደማልፈልግ ተናግሪያለሁ።

ፓርቲዎ ለጥያቄዎ ምን ምላሽ እየሰጠ ነው?
አቶ ሌንጮ፡- ገና ነው። ነገር ግን አሁን ስብሰባ ሊካሄድ ስለሆነ ውሳኔ ይሰጣል።

ኃላፊነትዎን መልቀቅ የፈለጉት ለምንድን ነው?
አቶ ሌንጮ፡- እርጅና

እርጅና ከኃላፊነት ብቻ ነው የሚያግድዎት? ቀጣይ ተሳትፎዎት ምን ይሆናል?
አቶ ሌንጮ፡- እንደ አንዳንድ ኃላፊዎች እያነከስኩ ስብሰባ መሄድ አልፈልግም። ነገር ግን ሕይወቴ እስካለ ድረስ የፖለቲካ ሥራን መተው አልችልም።

ረዥም ዓመታት በውጭ ሃገር ከቆዩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር በተያያዘ የዜግነት ጉዳይ ይነሳል። ዜግነትዎ ምንድን ነው?
አቶ ሌንጮ፡- የኖርዌይ ፓስፖርት ነው ተሸክሜ የምዞረው። ግን የዜግነቴ ጉዳይ በውሳኔዬ ላይ ምንም ተፅእኖ አልነበረውም። ነገሩ ኃላፊነት መልቀቅ ከመፈለጌ ጋር አይገናኝም።ብፈልግ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ለመመዝገብ ሲቃረብ የኖርዌይን ፓስፖርት ለኖርዌጅያኖቹ መልሼ ኢትዮጵያዊነቴን እንደገና ኅራ ላይ ማዋል እችላለሁ። ይህ ለውሳኔዬ ምክንያት የሆነ ነገር አይደለም።

በውሳኔዎ እንደ እርሶ ለረዥም ዓመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እየመሩ ላሉ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልእክት አለ?
አቶ ሌንጮ፡- በተለይ ኦነግ ውስጥ ሃምሳ ዓመት ያገለገሉ ሁሉም ኃላፊነት ቢለቁ ጥሩ ነው ብዬ አምናለው። አሁን አዲስ ትውልድ ትግሉን ተረክቧል እና ለእነሱ መተው ነው የተሻለው መንገድ።

በቀጣይ ተሳትፎዎት በምን መንገድ ይሆናል?
አቶ ሌንጮ፡- ፓርቲውም እያገለገልኩ እቆያለሁ።ከሌሎች ጋር በስፋት ለመሥራትም እቅድ አለኝ።

ስለዚህ ቆይታዎ የሚሆነው በኢትዮጵያ ነው?
አቶ ሌንጮ፡- አዲስ አበባ

No comments