Ethiopianism

“ሰው ማጣት የአገርን አንገት ያስደፋል፣ ያሳፍራል”



“ሰው ማጣት የአገርን አንገት ያስደፋል፣ ያሳፍራል”

“የሚሰማኝን መናገር መብቴ ነው” (my trade is to say what I think) ይለናል ቮልቴር፡፡ ከ150 ዓመታት በኋላ ደግሞ ፍሬዴሪክ ኒች … “የማይነገር ዕውነት መርዝ ነው፡፡ የልብህን ተናግረህ የፈለገው ይምጣ (un uttered truth can be poisonous, say your words and break in pieces) ብሎ ነበር፡፡ አሁን ዓለም የሚስማማበት ዕውነት ሆኗል፡፡ … የኛንም ህገ መንግስት ጨምሮ!!

ጨዋታችንን ስንጀምር በእግዜር ታላቅነት እየተገረምን ነው፡፡ … ከፊት ለፊቱ የተቆለለውን ማመልከቻ እየተመለከተ በሳቅ ሲንከተከት ስላየነው። በምድራችን የሚገኙ አገራት ተወካዮች በአዳራሹ ተሰብስበዋል፡፡ ሁሉም በየማመልከቻቸው ‹ዋናና አንገብጋቢ› የሚሉትን ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ 

አንዳንዶቹ- ሳቅ አማረን፣ ቀልድ አሰኘን፣ አንዳንዶቹ- ወንዝ ስጠን፣ ወደብ ይበጅልን፣ አንዳንዶቹ- በጋ ወይም ክረምት ይርዘምልን፣ ድንጋይ ወይም ዛፍ ይሰጠን፣ አንዳንዶቹ- ሴት ወይም የወንድ ቁጥር ይብዛልን፣ አንዳንዶቹ- ዘፋኝና ኳስ ተጫዋች አውርድልን የሚሉ ናቸው፡፡ 

… ያልተጠየቀ ነገር የለም፡፡ … ዕውቀት፣ ስልጣኔ፣ የጦር መሳሪያ፣ ግመል፣ ዝሆን፣ ዕባብ፣ ዕንቁራሪት፣ ኮከብ፣ ጨረቃ፣ ዴሞክራሲ .. ሌላም ሌላም ነገሮች፡፡ የኛ አገር ተራ ደረሰ፡፡ ማመልከቻችን ሲነበብ … ፍቅር. አንድነት፣ ዕምነት፣ ሰላም፣ ብልፅግና ይሰጠን የሚል ነው፡፡ 

“እስከ አሁን ካየኋቸው ማመልከቻዎች ውድ፣ ተገቢና ውብ ነገሮችን የጠየቀችኝ ኢትዮጵያ ናት” አለ እግዜር … ደስ እያለው፡፡ በመቀጠልም “እስኪ ተወካይዋን ልየው” በማለት ጠየቀ፡፡ ስልሳ አምስት ሰዎች ብድግ አሉ፡፡ “ተወካይዋን ነው የምፈልገው” አላቸው፡፡

አማራውም ‹እኔ›፣ ኦሮሞውም ‹እኔ›፣ ትግሬውም፣ ሲዳማውም፣ ጉራጌውም፣ በርታውም ከፍቾውም--ሁሉም ሳይደማመጥ፤ “እኔ፣ እኔ” እያለ ለመሰማት ሲጮህ … እግዜር በእጅጉ ግራ ተጋባ፡፡ “ለመሆኑ እናንተ እነማን ናችሁ?” ብሎ ሲጠይቅ … ሁሉም ዘር፣ ጎሳና ብሔሩን ተናገረ… መታወቂያውን እያሳየ፡፡ 

እግዜር አንዱንም አያውቀውም፡፡ አንዱም በመዝገቡ ላይ አልሰፈረም፡፡ … አዘነ፡፡ ራሱን እየነቀነቀ … “ከጠየቃችሁኝ ነገሮች በላይ አገራችሁ የሚያስፈልጋት መድኃኒት አለ፤ መጀመሪያ እሱን ፈልጉ” ብሏቸው ማመልከቻቸውን ቦጫጨቀው፡፡ “ምንድን ነው?” አሉት፤ አንድ ላይ፡፡ ነገራቸው። ሁሉም አንገታቸውን ደፉ፡፡ … ምን ብሏቸው ይሆን?

“ጣሊኖች ሪናይዛንስ፣ ጀርመኖች ሪፎርሜሽን አላቸው፡፡ ፈረንሳይ ግን ሁለቱም አላት… ቮልቴር!!... የ18ኛው ክፍለ ዘመን መገለጫና የለውጥ አባት።  
To name voltair is to characterize the entire 18th century … Italy had a renaissance, and Germany had a reformation, but France had voltair; he was both renaissance and reformation, and half the Revolutuon” 
ይለናል… ታላቁ ቪክቶር ሁጎ!! … ፈረንሳይን ትልቅ ስላደረጋት፣ “መጀመሪያ እንደ ሰው፣ ከዚያ እንደ ፈረንሳዊ አስባለሁ” በሚለው አቋሙ ስለሚታወቀው ሊቅ ሲናገር፡፡ … ስለ ቮልቴር!!

ወዳጄ፡- ሰው ማጣት የአገርን አንገት ያስደፋል፣ ያሳፍራል፡፡ … ዕድለኛ የሆኑ ሃገሮች ደግሞ እንደ ቮልቴር ዓይነት ሊቃውንትና የመብት ተሟጋቾች አሏቸው፡፡ … መታደል ነው፡፡ በቮልቴር ከመጣጥፎቹ ባንዱ …. “በማምንበት ካላመንክ ወዬልህ! … በማለት የሚያስፈራራኝ እሱ ማነው? … ከኔ የተለየ ነፃነት ማን ሰጠው? ይልቁን ዕውነት በራሷ መንገድ እንዳትራመድ፣ እንቅፋት ባይሆን ይሻለዋል፡፡ … ዕውነት ለውጥ ነው፤ ለውጥ ደግሞ እውነት የሚሆነው ማንም ሊያስቆመው ባለመቻሉ ነው” ይላል፡፡  

ወዳጄ፡- የሰው ልጅ አስተሳሰብ እየተቀየረ በመጣበት በዚህ የኒውክለር ዘመን፣ ሃሳብን ለማፈን መሞከር አይቻልም፡፡ ከላይ ቢደፈን በታች ይፈሳል፣ በአንድ ጎን ቢሰፋ በሌላኛው ይቀደዳል፡፡ ፖለቲካዊ ፍልስፍናም በሰሚ ሰሚ በተላለፉ ተረቶችና እምነቶች የሚያተኩር ሳይሆን በተጨባጭ ዕውነቶች ላይ ተመስርቶ፣ መጭውን ጊዜ ያገናዘበ ትንታኔ ማቅረብ ሲችል ነው፤ አሳማኝ ወይም ጥበባዊ አስተሳሰብ የሚሆነው፡፡ አለበለዚያ ጥቅም አልባ፣ ባዶ ጩኸት ሆኖ ያልፋል፡፡ 

የጩኸት ነገር ሲነሳ ሁለት ውሾች ያሉት ጎረቤቴን ያስታውሰኛል፡፡ አንዱ ትልቅና አስፈሪ ነው፡፡ አንዷ ደግሞ ድመት የምታክል ድንክዬ፡፡ የግቢው በር ሲንኳኳ ሁለቱም ይጮሃሉ፡፡ ባለቤቱ በር ከፍቶ ለመጣው እንግዳ ሞቅ ያለ ሰላምታ ከሰጠው ትንሿ ጭጭ ትላለች። ትልቁ ጩኸቱን አያባራም፡፡ … ካልተመታ በስተቀር፡፡ እንግዳው በማግስቱ ወይም ሌላ ጊዜ ቢመለስ ድንክየዋ ቀና ብላ አታየውም፡፡ 

“ባለቤቱ እየሳመው እኔ ለምን እጮህበታለሁ” ብላ የምታስብ ትመስላለች፡፡ ትልቁ ግን ይጮኃል፡፡ … እስኪደበደብ አያቆምም፡፡ … “ይቺ ቡዳ!” ይላታል ባለቤቷ፡፡
ወዳጄ፡- “ከአለቃህ የበለጠ እንደምታስብ አታሳውቅ። እንደውም አውቀህ እየተሳሳትክ እንዲያርምህ አድርገው፡፡ ይህን ካደረግህ ትሾማለህ፣ ትሸለማለህ፡፡ ማወቅህን ካወቀ ወይም ከሱ እንደምትሻል ከተረዳ ግን ይጠላሃል፡፡ ባየህ ቁጥር ያነሰ ስለሚመስለው ይሳቀቃል፡፡ ስለሚያባርርህ ተጠንቀቅ” እያለ የሚመክረው ደግሞ ሮበርት ግሪን ነው። ብዙ ሰዎች ከነሱ የተሻለ ከሚያስቡ ሰዎች ጋር መሆን ምቾት አይሰጣቸውም፡፡ 

“ታላላቅ ሰዎች ከፍ፣ ከፍ እንዲሉ አንፈልግም፡፡ እነሱ ሲበሩ እኛ የምንጨልም ስለሚመስለን በልባችን እንጠላቸዋለን፡፡ ድክመታቸውንና ስህተታቸውን ስንረዳ ቀና እንላለን፡፡ ሲቸገሩ፣ ሲታመሙ ወይ ሲታሰሩ ውስጣችንን ደስ እያለው ከንፈራችንን እንመጣለን፡፡ … “አዛኝ ቅቤ አንጓች” እንዲሉ፣ ስናስመስል፣ በማለት የፃፈልን ደግሞ ኸርበርት ስፔንሰር ነው፡፡  

ወደኛ ጉዳይ ስንመጣ፤ ሰውን በስራው መዝነን አዋቂውን አዋቂ፤ ጎበዙን ጎበዝ ለማለት ይተናነቀናል። የነበረው ስርዓት ጨዋ፣ አስተዋይና ጎበዝ ሰዎችን የሚገፋ ነበር፡፡ “አስበሃል፣ አውቀሃል” በሚል መንፈስ፣ ሰበብ እየተፈለገ፣ በውሸት ክስና ማስረጃ ፍዳቸውን ያዩ ብዙ ናቸው፡፡ 

አሁንም ለውጡ በእግሩ ባልቆመበት፣ የነበረው የስለላ ራኬት ባልተሰበረበት፣ ህግ አስፈፃሚ አካላት በአስተማማኝ ደረጃ የለውጡ አካል ባልሆኑበት፣ ከዘር ፖለቲካ፣ ከጥቅም ፖለቲካ፣ ከዘመድ አዝማድ ፖለቲካ---ተፅዕኖ የፀዱ፣ ደፋር፣ ሩቅ አሳቢ፣ ሚዛናዊና ምክንያታዊ የሆኑ የለውጥ አራማጆች ስልጥነው ዓቅም ሳይገነባ፣ ሰዎችን ማሳቀቅ ተገቢና ህጋዊ አይመስለኝም፡፡

“ከኑግ የተገኘሽ ሰሊጥ አብረሽ ተወቀጭ” እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ተሽሎ መገኘትና ስር ሰደው፣ መሬት ነክሰው፣ ስርዓቱ ቆንጥጦ እንዲይዝ ያደረጉትን መዋቅሮች በጣጥሶ፣ ፍትህና ነፃነትን ለማስፈን መትጋት ነው፡፡

ወደ ጨዋታችን እንመለስ፡፡ … እግዜር፤ ተወካዮቹ የጠሩለትን የጎሳና የዘር ዝርዝር ሰምቶ፣ አንዱንም አላወቀውም ብለን ነበር፡፡ ማመልከቻቸውን ቀዶ፤ “ከሁሉም በላይ አገራችሁ የሚያስፈልጋት ነገር አለ፡፡ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ” ነበር ያላቸው፡፡
“ምንድነው?” ሲሉት
“እንደ ‹ሰው› … የሚያስብ ‹ሰው›” አላቸው፡፡
“እንደ ቮልቴር ማለትህ ነው?”
“ትክክል!!”
ሠላም!!!

No comments