Ethiopianism

እውነቱን መነጋገር ካለብን ጊዜው አሁን ነው!! (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

እውነቱን መነጋገር ካለብን ጊዜው አሁን ነው!! (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

ታሪክ አንዴ ከተጻፈ በኋላ ለመቀልበስ ዘመናትን ይፈጃል። አሁን በተዛባ መልኩ እየተጻፈና እየተነገረ ያለው የቄሮ ገድል በአዲስ አበባና በአጠቃላይ በሀገሪቱ ለተከሰተው ውጥረት መነሻ ሆኗል። የቄሮ ትግል መቼ ጀመረ? ዓላማው ምን ነበር? እነማን ምን አደረጉ? የሚሉትን ጥያቄዎች አንስተን ሀቁን በማፍረጥረጥ መነጋገር መቻል አለብን።

ሁላችንንም ሀገር ያሳጣን፡ ነጻነትና ፍትህ የነፈገን አንድ የዘረኛ ስርዓት ለማስወገድ የውስጥ ሹኩቻዎችን፡ የጎንዮሽ ትግሎችን ወደጎን ማድረጉ ተገቢ ነበር። ተደርጓልም። ቢያንስ በእኩልነት በህግ የበላይነት አብሮ ለመኖር የሚያስችል ዝቅተኛ የመግባቢያ መፍትሄ ላይ ያተኮረው የጥምረት ትግል ህወሀትን ከቤተመንግስት አፈናቅሎ ከመቀሌ እንዲመሽግ አድርጎታል።

የኢትዮጵያውያን የነጻነትና የፍትህ ተጋድሎ ቄሮ የሚባል ቡድን ከመጣ ወዲህ የተጀመረ አድርጎ ታሪክን በማጣመም ከእኛ በላይ ለአሳር በሚሉ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች እጅ ላይ የኢትዮጵያ እድል እጣ ፈንታ ሊወድቅ አይገባም። አሁን የልብ ልብ ተሰምቷቸው፡ እኛ ባሰመርነው ካልሆነ አትንቀሳቀሱም የሚሉ ፈንዲሻ አክቲቪስቶች ስለቄሮ ትግል ሲነግሩን የለም ሀቁ እንዲህ ነው ብሎ መጋፈጥ ለቀጣይ እውነተኛ መፍትሄ ለማምጣት የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

በነበርንበት፡ ከአይናችን ባልራቀ ዘመን የተፈጸመን የትግል ታሪክ እነሱ ሰፍተውና ጎንጉነው ለሁላችሁም ነጻነትን ያመጣነው እኛ ነን በሚል ትርክት ሲያደነቁሩን ሀገር ለማረጋጋት በሚል ሆደ ሰፊነት በጸጋ መቀበሉ ዋጋ እያስከፈለ ነው። ዛሬ ከ50 በላይ ወገኖቻችን ለአሰቃቂ ግድያ የተዳረጉት ይሀው ''ነጻነትን ያመጣንላችሁ እኛ ነን'' በሚሉ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች የተዛባ የትግል ትርክት ነው።

ስለቄሮ ትግል ዋጋ ማሳነስ አይገባም። አለመጥንም ተለጥጦ የተጠማነውን ነጻነት ይበልጥ እንድናጣው እስክንደረግ በይሉኝታ መቀበልም ለማናችንም አይበጅም። የኢትዮጵያ ትግል ከግማሽ ክፍለ ዘመን ወዲህ ያለውን ብንመለከት አያሌ መስዋዕትነት የተከፈለበት፡ በሀገሪቱ በአራቱም ማዕዘናት የኢትዮጵያ ልጆች ዘር ቀለም ሀይማኖት ሳይገድቧቸው የተዋደቁለት ነው። ከ1953 መፈንቅለ መንግስት ጀምሮ የእነ ገርማሜ ነዋይና መንግስቱ ነዋይ ተጋድሎ፡ የ1966ቱ አብዮት፡ የ1997 ምርጫ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ የኢትዮጵያውያን የፍትህና የነጻነት ትግሎች ናቸው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየጊዜው የሚያደርጉት ትግል የህወሀትን አገዛዝ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማጋለጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው። በ1997 ምርጫ አዲስ አበባ 200 ልጆቿን ያጣችበትን ትግል ዘንግቶ የአዲስ አበባን ህዝብ መንቀፍ የሞራል ክስረት እንጂ ሌላ ስም አያሰጥም። አኝዋኮች የተጨፈጨፉበት፡ ሲዳማዎች በሎቄው ትራጄዲ ውድ ህይወታቸውን ያጡለት፡ ወልቃይቶች የዘር ማጽዳት ወንጀል ተፈጽሞ ማንነት የተነጠቁበት፡ የኮንሶዎች ዕልቂት፡ ሌላም ሌላም።

የህወሀትን አገዛዝ ለመጣል አናቱን መምታት አስተዋጽኦ ነበረውና የአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈትም ትግሉን በብዙ እጥፍ ወደፊት እንዲራመድ አድርጎታል። በዚህ ረገድ አቶ መለስ ዜናዊ ላይ በጋዜጠኛ አበበ ገላው የቀረበው ተቃውሞ የሚሊዮኖችን የትግል ወኔ ያነቃቃ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከጫፍ እስከ ጫፍ የተሰለፉለት የሃይማኖት ነጻነት ትግል የህወሀትን ወንበር የነቀነቀ ነበር።

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ከእስርና ስደት እስከሞት ዋጋ የከፈሉለትን ትግል ማን ነው የሚዘነጋው? ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ፖለቲከኛው አንዱዓለም አራጌ አቋማቸውን ሳይቀይሩ መልካቸውን ቀይረው የወጡበት ትግል እንዴት ይረሳል? የዞን ዘጠኝ ጦማሪውያን ከወጣትነት እድሜአቸው ተቀንሶ በግዞት ማሰቃያ እስርቤት የማቀቁት ለግል ጥቅማቸው መከበር ሲሉ አልነበረም። የኢትዮጵያ የ50 ዓመት ታሪክ እኮ በኢትዮጵያውያን እልህ አስጨራሽ ትግል የተሞላ ነው። ከዚያ ሌላ ምን የሚጻፍ ታሪክ አለ? ዛሬ ደርሶ ቄሮ ብቻውን የትግሉ ባለቤት ነው የሚለው ታሪክ ለምን አስፈለገ?

እውነት ለመነጋገር ህወሀት አከርካሪው ተሰብሮ ወደ መከላከል ደረጃ የወረደው በ1997 አዲስ አበባ ላይ ከተመታ በኋላ ነው። ከአምስት በላይ አፋኝ ህጎች የወጡትና ህወሀትም የለየለት ጸረ ዲሞክራት አገዛዝ የሆነው ከዚያን ወዲህ ነው። የመለስ ሞት ውድቀቱን አፋጠነ እንጂ ሕወሀት የቁልቁለት ጉዞውን የጀመረው አዲስ አበባ ላይ አይሆኑ ምት ከተመታ በኋላ መሆኑ መካድ አይገባም።  


ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም የዚህን ዘረኛና ኋላ ቀር ስርዓት ባህሪ በመረዳት የነጻነት ትግሉን በተወሰነ ደረጃ መደገፍ የጀመረው በ1997 የአዲስ አበባ ህዝብ በወሰደው ቆራጥ እርምጃ ህወሀትን ማጋለጡን ተከትሎ ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ ውለታ መቼም የሚረሳ አልነበረም። ያኔ ቄሮ የሚባለው ሃይል በስም ደረጃ ስለመታወቁም እርግጠኛ አይደለሁም።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በተደረገው ትግል የቄሮ ስም ከፍ ማለቱ እርግጥ ነው። በመላው የኦሮሚያ ክልል በተደረገው ትግል ቄሮ በወጉ ባይደራጅም፡ የሚታይ መሪ ባይኖረውም፡ የህወሀትን አገዛዝ ለመጣል ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉን ታሪክ መዝግባዋለች። ይሁንና ቄሮ ብቻውን አልነበረም። እዚህም እዚያም ኢትዮጵያውያን ውድ ዋጋ እየከፈሉ ከቄሮውች ጎን ለመኖራቸው የህይወት ምስክር ሆነን መናገር እንችላለን። 

እንደውም ያዝ ለቀቅ እያደረገ የነበረውን የቄሮን ትግል እንዲቀጣጠልና የህወሀትን ጎሮሮ ሰንጎ አላላውስ በማለት ለትግሉ ወደ ፊት መራመድ ትልቅ ድርሻ የነበረው በወሎ ወልዲያ ቆቦ የተደረገው የሞት ሽረት ትግል ለመሆኑ በቅርበት የምናውቀው ሀቅ ነው። ሀምሌ አምስት በጎንደር የተካሄደው ሰልፍ የትግሉን ማርሽ ከመቀየር ባለፈ የቄሮንም እንቅስቃሴው ወደ መሀል እንዲመጣ ያደረገ ወሳኝ ምዕራፍ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም።

ባለፉት 50 ዓመታት በሰማውና በተጋጋለው የኢትዮጵያውያን ትግል ላይ የቄሮ አስተዋጽኦ የሚናቅ አይደለም። እውነት ለመነጋገር የቄሮ ትግል ከችግር የጸዳ ነው ማለት አይቻልም። የተወሰኑ የመሀል ፖለቲካን የሚያራምዱ ትንታግ የኦሮሞ ልጆች ትግሉን ቃኝተው ወደ አማካኝ ስፍራ አመጡት እንጂ መጀመሪያ ላይ አግላይና ሌላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጋብዝ አልነበረም። 

ካልኩሌተሩን የሰራነው እኛ ነን የሚሉና ሆት ዶጋቸውን እየላፉ በኮምፒውተር ስር ተጥደው ፎቶግራፍ ሲለጥፉ ቀንና ማታ የማይበቃቸው የርቀት ታጋዮች የቄሮን እንቅስቃሴ ጸረ ኢትዮጵያ እንዲሆን ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንዳልነበረ እናስታውሳለን። በመጨረሻም የውስጥ ትግል አድርገው ህወሀትን በቁሙ ገድለው ሻምፒዮን በመሆን በወጡት የቲም ለማ አባላት ነገሮች መልክ ባይዙ ኖሮ በቄሮ ስም ይደረግ የነበረው ትግል ለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምቾት የሚሰጥ አልነበረም። ይህ እውነት ነው። እወነት መነጋገር አርነት ያወጣልና።

የዘር ፖለቲካ መልካም ውጤት ኖሮት አያውቅም። የዓለም ታሪክ የሚያሳየው፡ በዘመናችንም ካየነው እንደምንረዳው የዘር ፖለቲካ መጨረሻው እልቂት ነው። ሀሳብና እውቀት የነጠፈበት፡ ጥላቻ ምግቡ የሆነው የዘር ፖለቲካ የኢትዮጵያ ትልቁ ፈተና ሆኖ ተደቅኗል። የዘር ፖለቲካ ልቦናን ይጋርዳል። 

አይንን ያውራል። አዎን! ሚኒሶታ፡ ኖርዌይ፡ ለንደናና አውስትራሊያ ተቀምጠው በቴሌቪዥን መስኮት የዘር ዕልቂት በሚያራግቡ ግልገል ምሁራን እየተፈጸመ ያለው እልቂት ለየትኛውም ወገን የሚበጅ አይደለም። የጥላቻ ማስተላለፊያ በሆነ ቴሌቪዥን ጣቢያ አማካኝነት የሚቀርቡት እንግዶች በተመቻቸ ሀገር ላይ እየኖሩ ለደሀው ህዝብ ቆንጨራና ገጀራ የሚያቀብሉበት ሁኔታ አሳፋሪ የጊዜው ፖለቲካ ሆኗል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ነገሮችን በሰከነ መልኩ እየተመለከተው መሄዱ ተገቢነት ቢኖረውም ለእንዲህ ዓይነቱ አይን ያወጣ ጋጠወጥ ተግባር ትዕግስት ሊኖረው አይገባም። የህዝቡ ትዕግስት ፍርሃት የመሰለው የዘር ፖለቲካ አቀንቃኝም ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል። የወረወሩት ሰይፍ ዞሮ የት ሊያርፍ እንደሚችል አሁን ላይ ላይታይ ቢችልም ሩቅ ግን አይደለም።

ምን በቀደደው ምን ይገባል እንደሚባለው ህወሀት ይህን ክስተት እንደሰርግና ምላሽ እየተጠቀመው ነው። ጥቂት የኦሮሞ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች ከህወሀት ጋር በጥምረት ሊሰሩ እንደሚችሉ ከሰሞኑ ክስተት መደምደም ይቻላል። የመቀሌው ግብዣ፡ የስብሃት ነጋ የኦነግን አርማ መጨበጥና በአጠቃላይ የህወሀት አክቲቪስቶች ከምንጊዜውም በላይ ኦነግ ሆነው የቀረቡበት የሰሞኑ አሳፋሪ የፖለቲካ ድራማ የሚያሳየን ህወሀት የጠ/ሚር አብይን መንግስት ለማተራመስ የመጨረሻ ካርዱን መሳቡን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር መረጋጋት አቃተው በሚል ወደ ቤተመንግስት ለመግባት እድላቸውን ለመሞከር ህወሀቶች ማሰፍሰፋቸውን በግልጽ እየተረዳን ነው። የአብይ አስተዳደር የሚወስደው እርምጃ ምን እንደሚሆን አይታውቅም። ጥቂት የኦሮሞ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞችና ህወሀት ጥምረት መፍጠራቸው ለዶ/ር አብይ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የበለጠ ቀውስ ከመምጣቱ በፊት መደረግ ያለበትን ማድረግ ይገባል። በዚህን ቀውጢ ጊዜ ጠ/ሚር አብይ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መሄዳቸው ለምን እንዳስፈለገ አልገባኝም።

ለማጠቃለል ያህል ቄሮ ለዚህ ድል አበቃችሁ የሚለውን ትርክት አቁሙትና ለእውነተኛ የለውጥ ሂደት በጋራ እንስራ። የቄሮ አስተዋጽኦ ይታወቃል። በልኩ መቁረስ አለበት። ለእኔ ነጻነት በተከፈለው ዋጋ የቄሮ ሚና እንደሚኖር አልክድም። ግን ብቸኛ አይደለም። በቅብብሎሽ በመጣ ትግል የተገኘ የለውጥ ሂደት ነው። 

ለ27 ዓመታት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግል ተገዝግዞ፡ ውስጡ ተቦርቡሮ፡ ያለቀለትን የህወሀት ስርዓት ወደ መቃብሩ ለመሸኘት ባለፉት 3 ዓመታት በተደረገ ቀጣይ ትግል የቄሮ እንቅስቃሴ ተገቢውን ቦታ ማግኘት አለበት። ከዚያ ያለፈ ታሪክ ለራስ እየጻፉ ሌላውን ማስፈራራት ብዙ ርቀት አይወስድም።

ደግሞም ለውጡ እንዲህ እልቂት የሚያመጣ፡ ሀገር የሚያሳጣ ከሆነ አንደኛውን በተደራጀ መልኩ መንግስታዊ ቅርጽ ይዞ ሲቀጠቅጥና ሲጨፈጭፍ የነበረው ህወሀት ይሻላል የሚል የህዝብ ስሜት ሊያቆጠቁጥ እንደሚችል አልጠራጠርም። እናም የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ!!!!

No comments