Ethiopianism

«ጥቂት ግለሰቦች ናቸው፤ እገሌን አይወክሉም» ብሎ ነገር አይገባኝም! (በግዛው ለገሠ)



ጥቂት ግለሰቦች ናቸው፤ እገሌን አይወክሉም

ሻሸመኔ ላይ የሰው ልጅ ዘቅዝቀን የሰቀልነው እኛ ነን፤ ጅጅጋ ላይ ኢትዮጵያዊ ከነ ነፍሱ ያቃጠልነው እኛው ነን፤ ቡሬ ላይ ጨፍጭፈን የገደልነው እኛ ነን፤ ቡራዩ ላይ በቀውጢ ሁኔታ ውስጥ ሴት ለመድፈር ብልታችን የሚቆምልንም እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን፡፡  


በጥቂቶች ማሳበቡን ትተን ያለንበትን የዘቀጠ የሥልጣኔ ደረጃ እንመን፤ የተደረገው ሁሉ በይፋ በታማኝ ሚዲያ ይዘርዘርና ሁላችንም የተደረገውን እንደዜጋ እናውግዝ፤ ያኔ ብቻ ነው ዛሬ የሆነውን ነገ የማንደግመው!

ገዳይም ሟችም እኛው ነን፤ ይሄ ነው የሥልጣኔ ደረጃችን፡፡ ኢቲቪ ላይ 'ገደሉ፣ አረዱ፣ ሚስትን ከባል ነጥለው ደፈሩ' ሲባል መስማት አስደንጋጭ ነው፡፡ ማን ናቸው? «የብሔር ግጭት ለማስነሳት በደንብ የተደራጁ ናቸው» የሚለውም አይገባኝም! ከመንግስት በላይ አደረጃጀት ካላቸው፣ መንግስት የለም ማለት ነው፡፡ ቄሮን አይወክሉም ካልን፣ ቄሮም ቢሆን የረባ አደረጃጀት የለውም ማለት ነው፡፡

በየፌስቡክ ጥግ የሚሰራጨውን ቁርጥራጭ ወሬ ለማመን እና ላለማመን ስንታገል፣ ለሁለት ቀን ተኩል የቆየው የቡራዩ እና አካባቢው ሁናቴ በመንግስት ሚዲያ ጆሮ ሲያጣ፣ እንዲሁም የሻሸመኔውን ዝቅዝቅ ስቅለት መንግስትም ሆነ ሚዲያው በይፋ ለመግለፅ ሲሽኮረመሙ ሁነኛ አውጋዥ እና ተወጋዥ ይጠፋል፤ ሁሉም ቡድን መስርቶ የቡድኑን 'ክሬዲት' በማስጠበቅ ወይም የሌላውን ቡድን 'ክሬዲት' በማጠልሸት ላይ ይጠመዳል፡፡ ጉዳዩን አስፍተን ማየት ይዘነጋናል፤ እንደ ሕዝብ እየዘቀጥን መሆኑ ይረሳናል፡፡

እናም «የሆነ አካል እያባላን ነው» የሚልውን ለማመን ይከብደኛል፡፡ ሆኖም ይህ ሁሉ ኢ-ሰብዓዊነት ሲነግስ እውነትም እጁ ኖሮበት ቁጭ ብሎ የሚስቀብን ካለ፣ እርሱ በደምብ አድርቆ የውስጣችንን መዝቀጥ የተገነዘበ ነው፡፡

«አብይን አምባገነን ለማድረግ ነው፤ እርምጃ እንዲወስድና ከሕዝብ እንዲጋጭ ነው» የሚለውም አይገባኝም፡፡ እንደመንግስት የሚጠበቅበትን እርምጃ ለመውሰድ የሕዝብ ጥያቄ አያስፈልገውም፤ ከልክ ያለፈ፣ ከሕግ ያፈነገጠ እርምጃ ቢወስድ በዚህ ዘመን ተጠያቂነት እንዳለበት አብይም መንግስትም አይጠፋውም፡፡ 

በቡራዩ መልክዓ ምድር ማሳበብም ሆነ ግጭቱ ከሁለት ቀናት በላይ መቆየቱ አብይን እና ፖሊሶችን ከቸልተኝነት አላዳናቸውም፡፡ ያን እንቃወማለን ያሉ ሰዎች ላይ ያልተመጣጠነ እርምጃ ከተወሰደ፣ አሁንም ኢሕአዴግ አለ፤ የቀውስ ማኔጅመት እንከኑ እንዳለ ነው፡፡

በአንድ በኩል ብዙዎች በቄሮ ቢያሳብቡ ይፈረድባቸዋል? ከቄሮ በላይ ስልት እና ስትራቴጂ ያለው ቡድን ካለ ሕዝቡ በቄሮ እምነት ቢያጣ ይገርማል? 

ለዚህ ሁሉ መፍትሔው እገሌ እየተባሉ በስም እየተጠቀሱ ለፍርድ ሲቀርቡ ብቻ ነው? በሻሸመኔ ክስተት የተቀጣ ሰው አለ? በቡራዩ ለሆነው ግለሰቦች ተጠያቂ ለማድረግና አሳልፎ ለመስጠት ቄሮ ምን ሚና እየተጫወተ ነው? 

ታዲያ ሕዝቡ መንግስትንም ሆነ ቄሮን እንዴት ይመን? በመንግስትም ሆነ በቄሮ ጥረት እና የለውጥ ስኬት የኮራን ብዙዎች ነን፤ ታድያ ኩራታችንን እንዴት እናስቀጥል?

እናም መንግስት በሁለት እግሩ ይቁም፤ እኛም እንደ ሕዝብ ለመሰልጠን እንጣር!

No comments