Ethiopianism

በሐረር ከተማ ውሃ ከተቋረጠ ከ2 ወር በላይ እነደሆነው ነዋሪዎች ተናገሩ - ቢቢሲ

ሐረር ከተማ

ወ/ሮ እሌኒ ሐረር ከተማ ውስጥ የቀላድ አምባ ነዋሪ ናቸው። ከሚኖሩበት ሰፈር ቀበሌ 17 የጉድጓድ ውሃ ለመቅዳት ሄደው ነው ያነጋገርናቸው። ውሃ ከጠፋ ወር እንዳለፈው የሚናገሩት ወ/ሮ እሌኒ "የጉድጓድ ውሃውን ለማግኘት ህዝቡ ወደ ገጠር እየተሰደደ ነው" ይላሉ።

"የጉድጓድ ውሃ እያፈላን ነው የምንጠጣው ድሮ ተቆፍሮ የተደፈነ የጉድጓድ ውሃ (ኤላ) አለ እሱን ከፍተን እንጠቀማለን፤ ችግራችንን ሰሚ የለንም፤ አቤቱታ ስናቀርብም ዝም ብለው አሺ ብቻ ነው የሚሉት፤ ሐረር ከተማ ውስጥ ካሉት 19 ቀበሌዎች በአንዱ እንኳን ውሃ ካለ ሰዉ ሊቀዳ ሲል ይዘጋል።

"እኔና ልጄ ሁለት ጄሪካን ይዘን እንሄዳለን ያው በመሳቢያ ተስቦ እስኪወጣ ወረፋ ስላለ ብዙ ሰዓት ይወስዳል። እኔስ ትንሽ አቅም ስላለኝ ባጃጅ ይዤ አሄዳለሁ ጉልበትም ገንዘብ አቅም የሌላቸው ደካሞች አሉ፤ በጣም ከፈተኛ ችግር ላይ ነው ያለነው" ብለውናል።

ዜሮ አምስት ቀበሌ የሚኖሩትና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ግለሰብ የሐረር የውሃ ችግር ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት የሚሄድ ጉዳይ መሆኑን በምሬት ያስረዳሉ።

ልጃቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ እስከመቸገር የደረሱበት የውሃ እጥረትን ሲያስረዱም "የደንብ ልብሷ፣ ገላዋ ሳይታጠብ፣ የምትበላው ሳይሰነቅላት እንዴት ትምህርት ቤት ትሂድ እላለሁ" ይላሉ።

የአሁኑ የውሃ እጥረት ችግር ሦስት ዓይነት ነው የሚሉት እኚህ ግለሰብ ሐረር ውሃ ታገኝ የነበረው ከሦስት አቅጣጫዎች እንደነበር ያስታውሳሉ።

አንደኛው ከሐሮማያ የሚመጣው ሲሆን በአካባቢው ነዋሪዎች 10 ሚሊየን ብር ተጠየቀ በሚል ውሃ መቋረጡ እንደሚነገር ይናገራሉ። ከድሬዳዋ የሚመጣው ደግሞ በመብራት አቅርቦት ችግር ምክንያት መቋረጡን ሰምተዋል።

ሐረሪ የብሔር ብሔረሰቦች በዓልን ባስተናገደችበት ወቅት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተመረቀውና በኤረር የሚገኘው የውሃ ጉድጓድ ደግሞ በአካባቢው የሚገኙ ገበሬዎች ባነሱት የካሳ አንሶናል ጥያቄ መቋረጡን መስማታቸውን ያስረዳሉ።

እርሳቸው በሚኖሩበት ቀበሌ "ቡዳ በር" እና "ሰንጋ በር" አካባቢ ከሚገኙ ወንዞች ለሊት ስምንት እና ዘጠኝ ሰዓት ላይ ከጅብ ጋር ተጋፍተው ውሃ እንደሚቀዱ የሚናገሩት እኚህ ግለሰብ ይህንን ውሃ ለልብስ ማጠቢያና ለምግብ ማብሰያነት እንደሚጠቀሙበት ይናገራሉ።

ለመጠጥ ግን የታሸገ ውሃ በመግዛት ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ገልፀዋል።

አቶ አብዱልናስር ከድር- ጊዮርጊስ መቃብር አካባቢ ነዋሪ ናቸው። እርሳቸው ውሃ ከጠፋባቸው 9 ወር እንደሆናቸው ይናገራሉ።

"ዝም ብለን ቆጣሪ እንዳያነሱብን የኪራይ 13 ብር እንከፍላለን። ካልከፈልን ደግሞ 30 ብር ይቀጡናል። እንዲያውም ከሦስት ወራት በፊት የአካባቢው ሰው ተሰብስቦ ኡኡ ብሎ አስተዳዳሪዎች መጥተው ለአንድ ሳምንት ብቻ ጠብቁን ብለውን ነበር። አሁን ግን ይኸው እንኳን ውሃውን ሊለቁልን ቧንቧችን ራሱ ደረቀ ከ9 ወር በፊት በወር አንድ ጊዜ የምትመጣውም ውሃ ቀረች።"

ጄሪካን ይዘን ዲፖ ከሚባል አካባቢ የጉድጓድ ውሃ በባጃጅ ለማምጣት 90 ብር እናወጣለን የሚሉት አቶ አብዱል ናስር ውሃውን በጄሪካን 5 ብር እንደሚገዙና ለባጃጅ ከአካባቢው ርቀት አንጻር እስከ መቶ ብር እንደሚከፍሉ ተናግረዋል። በአካባቢው ካለው የውሃ ችግር አንፃር አቅሙ ያላቸው ለቅቀው እየሄዱ መሆኑንና በአካባቢያቸው ተከራይም እንደማይገባ ተናግረዋል።

ሐረር ተወልደው ያደጉትና በመምህርነት ሥራ የሚተዳደሩት የቀበሌ 17 ነዋሪዋ ደግሞ በአካባባያቸው ውሃ ከተቋረጠ ከወር በላይ እንደሆነው ይናገራሉ።


እርሳቸው ትልልቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ሰቅለው በቤታቸው ውስጥ ደግሞ በርሜሎች ሞልተው በማስቀመጥ እንደሚጠቀሙ የሚናገሩት እኚህ እናት "የከተማው ነዋሪ ውሃ ፍለጋ ጀሪካን ይዞ ሲዞር ይታያል" ይላሉ።

"ሰሞኑን ዘንቦ ትንሽ ታገስን እንጂ የውሃ እጥረቱ የሚያላውስ አልነበረም" የሚሉት እኚህ እናት በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ልብሳቸውና ገላቸው ያልታጠበ ተማሪዎች አይተው አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸገሩ ነግረውናል።

ውሃ ሲጠፋ 55 ኪሎ ሜትር ድረስ ተጉዘው የሚቀዱ እንዳሉ የሚናገሩት እኚህ ግለሰብ ይህንን ማድረግ የሚችሉት መኪና ያላቸው ናቸው ይላሉ። አክለውም "ለሻይ ማፍያ አንድ ብርጭቆ ውሃ የሚቸገሩ ሰዎች አሉ" በማለት የችግሩን ግዝፈት ያስረዳሉ።

አቶ ዳንኤል በርሄ በሐረር ከተማ የሆቴል ባለቤት ናቸው። ላለፈው አንድ ወር በሳምንት ከግለሰብ ከቦቴ ውሀ በ2000 ብር እንደገዙ ያስታውሳሉ።

"ከአልጋ ኪራይ የማገኘውን ገንዘብ መልሼ ለውሃ ነው የማውለው የሚሉት አቶ ዳንኤል" በፊት በሳምንት አንድ ቀን ውሃ ይመጣ ስለነበረ በትልቅ ማጠራቀሚያ እያጠራቀምን እንጠቀም ነበር። አሁን ግን ሲቆም ያለን አማራጭ በውድ ዋጋ መግዛት ብቻ ነው" ብለዋል።

በከተማው የተፈጠረው የውሃ አቅርቦት ችግር የተከሰተው ፕሮጀክቱ በሚገኙባቸው አካባቢዎቸ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ባነሱት ጥያቄ ምክንያት መሆኑን የሐረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ አብዶሽ መናገራቸውን የሐረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ አስነብቧል።

No comments