Ethiopianism

በጎንደር ሰልፍ የተላለፈ የአማራ ሕዝብ የአቋም መግለጫ!

 የአቋም መግለጫ!

የአማራ ሕዝብ የአቋም መግለጫ
(ጥቅምት 18/2011 ዓም)


የተከበራችሁ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ!
የተከበራችሁ በክልላችን ከክልልም ውጭ በመላው ኢትዮጵያ እንዲሁም በመላው አለም የምትኖሩ የአማራ ልጆች!
የተከበራችሁ የታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ነዋሪ የአማራ የቁርጥ ቀን ልጆች!

የአማራ ህዝብ በማይሰፈር ልክት ስለ አንድነት ስለሁሉን አቃፊነት ዋጋ ከፍሏል፣ ተሳድዷል ተገድሏል ተፈናቅሏል። ሞኝም ፈሪም ሆነን አልነበረም። ሊመጣ ካለው ችግር ሰፊው ህዝብ ይጠበቅ ዘንድ ነበር፡፡


መታገሳችን እንደ ሞኝነት ማመዛዘናችን እንደ ፍርሃት ተቆጥሮ አማራን ያልነካ የማሪያም ጠላት የተባለ ይመስል ስለኢትዮጵያ ደኅንነት በከፈልነው እጥፍ በእኛ ላይ ሰይፍ አልፏል፡፡ ያለፈው መንገድ ይበቃል ብለን አማራነትን አንስተን የአባቶቻችንን ሰይፍ ስለን ስለ መገፋታችን ልንፋረድ ተነስተናል፡፡

እነሆ ዛሬ በጎንደር ከተማ በተካሄደው ሰፊ ህዝባዊ ሰልፍ ለሚመለከተው ሁሉ ባላ 9 ነጥብ የመጨረሻ የአቋም መግለጫ እናስተላልፋለን፡፡

1) ለትግራይ ክልል ህዝብ እና አባቶቻችን!
በሰሜን በኩል በደረሰው የጠላት ጥቃት ሁሉ ደማችሁ ደሜ ብለው ባለፈባችሁ መከራ ሁሉ አልፈው ሞታችሁን ሞታችን ብለው የጭንቅ ዘመን ደራሽ ሆነው አልፈዋል፡፡

የበሬ ወለደ ታሪክ አምላኪ የትላንት ልጆቻችሁ ያለፈ ታሪካቸውን ረስተው በሰፊው አማራ ህዝብ ላይ የጠላትነት አቋም ወስደው ማኒፌስቶ ቀርጸው ሲንቀሳቀሱ ደግፋችሁ መርቃችሁ ልካችኋል፣ በታሪክ በሰነድ የተረጋገጡ የአማራ የጥንት ግዛቶች ወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ራያ በስርቆት በውንብድና ወደ ትግራይ ክልል ሲካለሉ ስለ ሃቅ እንደ ህዝብ ሳትቃዎሙ ኖራችኋል፡፡ 

ከሁሉም በላይ ክቡር የሰው ልጅ ባልኖረበት ባላደገበት የማንነት ሂሳብ ሲሰላ ለምሳሌ የወልቃይት የራያ የጠገዴ የጠለምት ወዘተ ተወላጆች መከራ ሲያልፍባቸው ለዘመናት በዝምታም በድጋፍም አልፋችኋል፡፡ ስለ አብሮ መኖር ስለ ቀደመው መልካም የጋራ ታሪካችን ስንል ያለፈውን የጥፋት ዘመን ሁሉ በገዘፈ ትግስት አልፈናል። 

ነገር ግን የመከራው ሰንሰለት የትውልድ እርግማን ሆኖ መቋጫ ሳይኖረው እስከ ዛሬው የወልቀይትና የራያ አማሮች መታደን መገደል መፈናቃል ደርሰናል፡፡

አሁን ግን ያለፈው ሰይፍ ላያልፍ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያችንን እናስተላልፋለን። ትላንት በኃይል የተወሰዱ የአማራ ግዛቶች ከነ ሙሉ ህዝባቸው ከነ ማንነታቸው እንዲመለሱ እንዲጠበቁ እናሳስባለን፡፡ 

አዎን ወልቃይት ከነወልቃይቶቹ ራያ ከነራዮቹ ጠገዴ ከነ ጠገዴ አማሮቹ ጠለምት ከነ አማራ ጠለምቶቹ ወደ ልባቸው ወደ ፈቃዳቸው ወደ ህዝባቸው ወደ አማራ እና ወደ አማራነት እንዲመለሱ እናሳስባለን በአቋመችንም መልካም ድጋፋችሁን እንጠብቃለን፡፡  

አብሮነታችን ስለጋራ ጥቅማችን ይሆን ዘንድ እንደ ህዝብ ልብ አስፍታችሁ ያለፈ የሚመጣውን ተረድታችሁ ማሳሰቢያችንን በአፋጠኝ መልስ እንድትሰጡት እናስገነዝባለን።

2) ለትግራይ ልሂቃንና ፖለቲከኞች!
ትላንት በመጣው ሃሰተኛ ታሪክ ተመርታችሁ አማራ ጠል ትርክት አማራ ጠል ፖለቲካ ላራመዳችሁ ለምታራምዱ ሁሉ "የመውጊያውን ብረት ብትረግጥ ህመሙ ባንት ይብሳል" እንዲሉ ዞር መለስ ብላችሁ ባላሰላችሁት መንገድ መጓዛችሁ እንዲበቃ ይህ የመጨረሻ መልክታችን ይድረሳችሁ፡፡ 

እንደ ህዝብ እንዳጠቃችሁ ህዝብ ዋጋችሁን ይከፍላል። ቀጠሮም የሌለው ፍርድ ከፊታችሁ አለ፡፡አማራና አማራነትን በተመለከተ ባሳለፋችሁት ያልተቋረጠ የስም ማጥፋት የታሪክ ማዛባት ድርጊት ባስቸኳይ እንድትቆጠቡ ለመጨረሻ ጊዜ እናስጠነቅቃለን፡፡

3) ለኢፌዲሪ መንግስት!
አማራው በስርአተ መንግስት ምስረታ በሀገር ግንባታና ጥበቃ ወደር የለሽ ሚና ቢያበረክትም ቅሉ ላለፉት 27 ዓመታት በነበሩት የኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመናት አማራው ስልታዊ የፖለቲካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መገለል ሲደርስበት ቆይቷል። ችግሩ ዛሬም ማለቂያ ሳይኖረው አማራው እንደሰውነቱ መብቱ እና ጥቅሙ ሳይከበር በመሰረታት ሃገር ባይተዋር እንዲሆን ተደርጓል። 

አማራው በታሪኩ ለኢትዮጵያ ያበረከታቸው ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ሃብቶች አስፈላጊው ጥበቃ ሳይደረግላቸው እንዲጠፉ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ስለዚህ መንግስት ከለከት በላይ የሆነውን በአማራው ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል እንዲያስቆም የመጨረሻ እርምጃ እንዲዎስድ የመጨረሻ ማሳሰቢያችንን እንገልጻለን፡፡

በትግራይ ክልል እየተጠየቁ ያሉ የአማራው የማንነነት ጥያቄዎች በመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በኩል የሚደርስባቸው መታፈን እና አግባብነት የሌለው ስረዛ እንዲቆም እናስጠነቅቃለን፡፡

የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ከተጋረጠባቸው የመውደም አደጋ በአፋጣኝ እና ዘላቂነት ባለው መልኩ እንዲጠበቁ መንግስት ከዓለም አቀፍ የባህልና ቱሪዝም ማህበራት ጋር በማበር እንዲሰራ እናሳስባለን፡፡የጣና ሀይቅ ከተደቀነበት የመጥፋት አደጋ በአፋጣኝነትና ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲጠበቅ እናሳስባለን፡፡

4) ለኢትዮጵያ ህዝብ!
የሃገራችን ህዝቦች ሆይ - አማራው ስለአንድነታችሁ ስለክብር ስለ መብታችሁ ከጎናችሁ ሆኖ የከፈለውን የትላንት ዋጋ አክብራችሁ በደረሰብን መገፋት ሁሉ እንደ ህዝብ ከጎናችን የነበራችሁ ወንድሞች እህቶች ዛሬም ባልተገታው መገፋት መበደላችን እንዲቆም መደጋገፋችን እንዲቀጥል እንጠይቃለን፡፡

የእኛም የእናንተም የሆኑት የኩራት ቅርሶቻችን ከሚደስርባቸው ሰው ሰራሽ ና የተፈጥሮ ጉዳት እንዲጠበቁ ጠንካራ ድጋፋችሁን እንሻለን፡፡ በህግም በታሪክም የአማራ ግዛቶች የነበሩ በተለያዩ ክልሎች የተካለሉ የአማራ የጥነት ግዛቶች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ፍተሐዊ ድጋፋችሁን እንሻለን፡፡  

አማራው በመሰረታት ኢትዮጵያ ተከብሮ ተጠብቆ እንዲኖር በምናደርገው ትግል ድጋፋችሁን እንሻለን፡፡

5) ለአማራ ዴሞክራሴያዊ ፓርቲ (አዴፓ)
ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ክልሉን በማስተዳደር ብትቆዩም እንኳ ከደረሰብን ግፍና መከራ ሳንጠበቅ እንዲያውም የመከራው ዘመን የስላቅ ከበሮ ደላቂ ሆናችሁ ስታደሙን ስታቆስሉን ቆይታችኋል፡፡ ያመጣነው ለውጥ እናንተንም ነጻ ካወጣችሁ ጥያቄያችን ጥያቄያችሁ ሆኖ ትላንት ያለፈበን የጨለማ ዘመን እንዳይደገም ከፊት እንድትቆሙ እናሳስባለን፡፡

የአማራ የመኖር ጥያቄ ካሁን በኋላ የጋራ አጀንዳችን ሆኖ የወልቃይት የራያ የመተከል የጠገዴ የጠለምት እና መሰል ግዛቶች እንዲሁም የነዋሪዎቹ የአማራነት የማንነት ጥያቄ በአስቸኳይ መልስ እንዲሰጠው እንደ ህዝብ የመጨረሻ አቋማችን እናሳውቃለን፡፡አዴፓም በጥያቄዎቻችን ዙሪያ ያለውን የለዘብተኝነትና የለስላሳነት አቋም ትቶ ራሱን ስሎ የፊት ለፊት ሰይፍ እንዲሆን እናሳስባለን፡፡ 

የላሊበላ የፋሲል ግንብ እና የጣና የመጥፋት እና የመውደም ስጋት የአዴፓ የንስሃ ስራዎች እንዲሆኑ እናሳስባለን ጊዜ ሳይሰጥ መልስ እንዲሰጥ እንደ አማራ ህዝብ የመጨረሻ ህዝባዊ ማሳሰቢያ እናስተላልፋለን፡፡

አማራነት ከአባይ ከጣና አማራነት ከላሊበላ ከፋሲል ግንብ ውጭ የማይታሰብ ነውና አዴፓ አማራና አማራነትን የማዳን ስራውን የዛሬ ስራው እንዲያደርግ የመጨረሻ ማሳሰቢያ እናቀርባለን፡፡

6) ለአማራ ማህበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ!
ከተወረወረብን የጦር ብዛት አንጻር ቁጥራችሁ እልፍ ቢሆን መልካም ቢሆንም እንኳ በመንገዳችሁ ሁሉ የጋራ ግብና መተባበር እንዲኖራችሁ እንጠይቃለን፡፡ከፊት ለፊት ከመጡብን እና ሊመጡብን ካሉት ችግሮች እንድንጠበቅ የጋራ መግባባት ኖሯችሁ ትግላችሁን አበርትታችሁ እንድትቀጥሉ እንጠይቃለን፡፡
7)ለአማራ ወጣቶች በሙሉ
ወጣት ልጆቻችን ሆይ አማራው በባህሉ የሰውነት ክብሩን፤ርስቱን፤ድንበሩን በሃይል ውንብድና ሲነኩበት አይወድም፤አባቶቻችሁን አስቡ ያወረሱንን አደራ በልተን አጥንታቸው ሲዎጋን እንዳይኖር መርቀው ጠብቁ ለልጅ ልጅም አውርሱ ብለው እየሞቱ የሰጡንን የሰውነት ክብር የደማቸውም ርስት፤ግዛት ወደ ቤቱ እንዲመለስ ከምንጊዜውም በላይ የአባቶቻችሁን ሱሪ ለመታጠቅ ተዘጋጁ፡፡

አማራ የአባቱን አደራ አይበላም፣አማራ የአባቱን ርስት፤ክብር፤ግዛት አሳልፎ አይሰጥም። ያኖረን ጀግንነታችን ይሄ ነው፡፡ስለዚህ ወጣቱ ሆይ የጀመርከው ትግል ተቀጣጥሎ የአማራ ጠላት ሆነው የተነሱትን የሰደድ እሳት ሆኖ እንዲፈጃቸው ራስክን በአማራነትህ እንድታደራጅ ይህ የመጨረሻው ህዝባዊ ጥሪ ነው፡፡

8/ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት!
ቤተክርስቲያኗ ለሐገር ምስረታ ጥበቃ እና እድገት ያበረከተችው መልካም ተግባር በታሪክ የሚዘከር የትውልድ አሻራ ሆኖ ሲነገር ይኖራል፡፡

ነገር ግን ላለፉት ሁለት ሦሰት አስርት ዓመታት በደረሰባት ስልታዊ መገፋት የነበሯት ስለፍትሕ የመጮህ የመታገል የማታገል ሚና በእጅጉ ቀዝቅዞ አመራሮቿ ያለግብር ያለ ተልዕኳቸው የአንድ ብሔር ፖለቲካ ዘፋኞች ሆነው እንደ ሐገር የደረሰውን ጥፋት ከመቃዎም ይልቅ አቀጣጣይ በመሆን ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡

ጠቅላይ ቤተ ክህነት የህወሀት የሀይማኖት ክንፍ በመሆን ለደረሱት ህዝባዊ መከፋፈል እና መተላለቅ እንደ መሳሪያ ሆነው አገልግለዋል፡፡

አማራው የነበረው የሐይማኖት ልዕልና አስተሳሰብ ተሸርሽሮ ከደረሰበት የስብእና ልክ እንዲዎርድ በማድረግ መልካም እሴቱን ለማጥፋት በተደረገው ሸፍጥ ሁሉ የቤተክርሲያኗ የበላይ ጠባቂዎች ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ለዚህም ዋልድባን ከማራቆት ጀምሮ በየ አድባራቱ ሲደረጉ የነበሩት እስራት ግድያዎች ጥቂት ምስክሮች ናቸው፡፡

የቤተክርስቲያኗ የኩራት ምንጭ የሆኑት የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት እና የጣና ዙሪያ ገዳማት ከሚደርስባቸው የመጥፋት አደጋ እንዲጠበቁ የቤተክርሲያኗ የበላይ ጠባቂዎች ግንባር ቀደም ተሟጋች ሆነው መቅረብ ሲገባቸው አማራን ከነታሪኩ እንቅበር ከሚሉ ኪሳራ ከደረሰባቸው ፖለቲከኞች ጋር በማበር ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታችሁ በእጅጉ ያሳዝነናል፡፡ 

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ከትግራይ ፖለቲከኞች ጥምዘዛ ነጻ ሆኖ ቀኖናው በሚያዝዘው መንገድ ብቻ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ስንል ለመጨረሻ ጊዜ እናሳስባለን። የላሊበላ እና የጣና ጉዳይ የየእለት ስራችሁ ሆኖ በአፋጣኝ መፍተሄ እንዲያገኝ እናሳስባለን፡፡
9/ ለኢስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት፡፡
ባለፉት ሁለት ሶስት አስርት ዓመታት እንደ ህዝብ በደረሰብን መገፋት ምክኒያት የአማራው መጅሊሶች የፖለቲካ ማጫዎቻ ሆነው ፖለቲከኞች አሰጋጅ ሆነው አማራው በነበረው የሃይማኖት ልዕልና ልክ እንዳይኖር በማድረግ ሲሳለቁ ኖረዋል፡፡

የምክር ቤቱ አመራሮችም የአማራ ሙስሊሞች በተከበረው የረመዳን ጾም ወቅት ሳይቀር ተፈናቅለው የዕለት ጉርስ በተቸገሩበት ወቅት አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ አልፏል፡፡ የአማራው የኢስልምና መልካም ጠባቂዎች በፖለቲከኞች በግፍ ሲታሰሩ ሲገደሉ እንደ ሃይማኖት መሪነታችሁ አንዳችም ተቃውሞ ሳታሰሙ አልፋችኋል፡፡

ሰፊው የአማራ ህዝብ ይሄን ሁሉ እኩይ ተግባር በልበ ሰፊነት አሳልፏል፡፡ነገር ግን አሁን በምናደርገው ትግል ከቀድሞ ስህተት ተመልሳችሁ ህግና ስርዓቱ በሚፈቅደው ልክ ፍትሐዊ ድጋፋችሁን እንጠይቃለን፡፡

10) ለአማራ ጠል አክራሪ ብሔርተኞች በሙሉ፤
ትላንት ባሳለፍነው የከሰረ የፖለቲካ የትግል ዘመናችሁ በአማራው ላይ ያራመዳችሁትን የጥላች አሰተምህሮ ብሎም በተግባር የታየ ትንኮሳ በሆደ ሰፊነት በአብሮ መኖር ስሜት ስንታገስ ቆይተናል ነገር ግን መታገሳችንን በመናቅ ዛሬም ድረስ ባለተቋረጠ መልኩ ጸረ አማራነታችሁን ስታራምዱ ይታያል፡፡

ነገር ግን አማራው ካሁን በኋላ በምንም መልኩ የሚሰነዘሩ ትንኮሳዎችን እንደማይታገስ ለመጨረሻ ጊዜ እናስጠነቅቃለን፡፡ ከላይ የቀረቡት 10 የአቋም መግለጫዎች የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ባጭር ጊዜ ውስጥ መልስ እንዲሰጥባቸው እናሳስባለን፡፡

አማራነት የቀደመ ታሪኩን ሊያደስ ተነስቷል!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
ጎንደር!

No comments