Ethiopianism

"የፈረሰን ቤት መገንባት!" በብርሃነመስቀል አበበ

"የፈረሰን ቤት መገንባት!" በብርሃነመስቀል አበበ

በኢትዮጵያ ያለው ለውጥ ውስብስብ እና ትልቅ ጥበብ ይጠይቃል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ነገሩ እየፈረሰ ያለ ቤት ውስጥ እየኖሩ ማደስን ይመስላል።

ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ቤት አለችን። ቤቱ ባለፉት 27 ዓመታት በሌቦች ተዘርፎ ባዶውን ነው። የቤቱ ግርግዳ፣ በሮች እና መሰኮቶች በሌቦቹ እና በዘራፊዎቹ ወላልቆ ተወስዷል።

የቤቱ ክዳን እና የማዕዘን እንጨቶች ከፊሉ ወደቋል። ምሰሶውም ተነቃንቋል። የማገር እንጨቶቹ እየፈራረሱ ነው። ቤቱ በክረምት ዝናብ፣ በበጋ ብርድ አይከላከልም። ሌቦቹ የሚላስ፣ የሚቀመስ ቤቱ ውስጥ ስላልተው ከመቶ ሚልዮን በላይ የቤቱ ነዋሪ ባዶ ሆዱን እያደረ ነው።

ቤቱን ያፈረሱት እና የዘረፉት ሌቦች ሸሽተው አፈገፈጉ እንጂ አልተያዙም። ይባስ ብሎ ከ27 አመቱ ዝርፍያ እና ሌብነት የተረፈ ንብረት ካለም እንደገና ለመዝረፍ እያደቡ ነው።

አንዳንዶቹ ሌቦች ከቤቱ ነዋሪዎች መካከል ሆድ አደሮችን እያደራጁ ለማዘረፍ ጥረት እያደረጉ ነው። ለዘራፊዎቹ ያመች ዘንድ የቤቱ ነዋሪዎች እንዲጣሉ እና እንዲገዳደሉም እያደረጉ ነው።

ትልቁ የጋራ ቤት ፈርሶ የየራሳችንን ጎጆ እንቀልስ የሚሉም በሌቦቹ የሚደገፉ ወገኖች አሉ። አብዛኛው የቤቱ ነዋሪ ግን ቤተሰብ እንዲፈርስ እና እንዲበተን አይፈልግም።

እኔ በቤቱ ላይ ካልነገስኩ እያሉ የፈረሰው ቤት ነዋሪዎችን እና መሪዎችን የሚበጠብጡም አሉ። የፈረሰ ያለው ቤት ነዋሪዎች አሁን ሶስት ዋና ዋና ስራዎች አለባቸው።

ለ27 ዓመታት ቤቱን ሲዘርፉ፣ ሲሰርቁ እና የቤቱን ነዋሪ ቤተሰቦች ሲያባሉ የነበሩ ነገር ግን አሁን አፈግፍገው እየተደራጁ ያሉ ሌቦችን እና ዘራፊዎችን ዳግም እንዳይዘርፏቸው እና አደጋ እንዳያደርሱ መከላከል። ሌቦቹንም ይዞ ለፍርድ ማቅረብ።

የፈረሰውን የጋራ ቤታቸውን በጋራ ሆነው መገንባት እና በጋራ ጥቃት መከላከል። በቤተሰቡ አባላት መካከል መግባባት እና መቀባበል ሰፍኖ የቤተሰቡ ኑሮ እንዲሻሻል በጋራ መስራት ናቸው። ከዚህ ሁሉ የፈረሰውን ቤት መልሶ መስራት ትልቅ ትዕግስት ይጠይቃል። የፈረሰን ቤት እያደሱ ቤቱ ውስጥ መኖር አስቸጋሪ ነው። 

የቤቱ ክፍሎች በሙሉ አቧራ በአቧራ ሆነዋል። ዝናብና ብርድ የማይከላከሉ ክፍሎችም አሉ። የተዘረፈውን ቤት መልሶ ለማደስ በቂ ገንዘብ እና ባለሙያም የለም።

የቤተሰቡ ህይወት ከዚህም በላይ ውስብስብ ነው። ለስራ ያልደረሱ፣ ነገር ግን ከፍተኛ እንክብካቤ የሚፈልጉ እድሚያቸው ከ16 አመት በታች የሆኑ ልጆች እና ህፃናት ከቤተሰቡ 50% በላይ ስለሆኑ የቤተሰቡን በተለይ የአባ ዋራዎቹን ህይወት እና ቤተሰቡን የመምራት አቅም አስቸጋሪ ያደርጋል።

ለቤተሰቡ የማይታዘዙ ፍንዳታዎችም በማህበራዊ ሚዲያ እና በየመንገዱ እየተበራከቱ ነው። የቤተሰቡ ችግር እና አስተዳደር ያልገባቸው ወይም የማይገባቸው በእድሜ የጃጁ ሽማግሌዎችም የቤተሰቡ ሸክም እና ችግር ሆነዋል።

ከዚህ ቀደም ለረጅም አመት የተሰደዱ እና አሁን የተመለሱ የቤተሰቡ ኑሮ መመሰቃቀል ያልገባቸው የቤተሰቡ አባላትም ብዙ ናቸው። እነዚህ በአንድ በኩል እንግዳ ለመሆን የሚፈልጉ፣ በሌለ በኩል ደግሞ የፈረሰውን የቤተሰባቸውን ቤት ለማደስ የሚፈልጉ ከስደት ተመላሾች ለአባ ወራዎቹ ችግር መሆናቸው አልቀሩም።

"የፈረሰ ቤት ሰራተኛ እንጂ እንግዳ እና ተስተናጋጅ አይፈልግም" ብሎ ከስደት ተመላሹን ሁሉ ወደ ስራ ማሰማራት የአባ ወራዎቹ ግዴታ ይመስላል።

አንዳንድ ለአቅመ አዳም ደርሻለው ዳሩኝ እና አባ ወራ ልሁን የሚሉ አእምሮ የጎደላቸው ወጠምሻዎችም አሉ። ቤተሰቡ አሁን ሰርግ (ምርጫ) የሚደግስበት ቤትም ሆነ ገንዘብ እንዳሌለው የቤተሰቡ አባላት ሁሉ መስማማት አለባቸው። ለወጠምሻዎቹም ተነግሮ ወደ ስራ መሰማራት አለባቸው

ከሁሉም በላይ ግን አባ ወራዎቹ ቤተሰቡ በላዩ የፈረሰውን ቤት ውስጡ እየኖረ መልሶ ከመገንባት እና ከማደስ ውጭ ሌላ ምርጫ እንዳሌለው ለቤተሰቡ አባላት በግልፅ መንገር አለባቸው። የቤተሰቡ ግንባር ቀደም ኃላፊነት የፈረሰውን ቤት መገንባት (nation building) መሆን አለበት።

ቤተሰቡ ሌላ ቤት ውስጥ እየኖርኩኝ ይህን ቤት አድሳለው ወይም ይህን ቤት አፍርሼ ሌላ እሰራለው የሚልበት ተለዋጭ ቤት የለውም። አቧራም፣ ብርድም፣ ረሃብ እና ጥማት ወዘተ ብበዛበትም ቤተሰቡ የፈረሰበትን ቤት መልሶ ከመገንባት ውጭ ምርጫ የለውም።

ሁሉም ለስራ የደረሰ የቤተሰቡ አባል ወገቡን ታጥቆ ወደ ስራ መግባት አለበት። ገበሬው በአንድ እጁ እርፍ፣ በሌላ እጁ ጠብመንጃ ይዞ ቤተሰቡን ለመመገብ እና ከጠላት ለመከላከል መዘጋጀት አለበት።

ጥበበኞች እና አዋቂዎች ቤቱን ለመገንባት እና ለማደስ መሰማራት አለባቸው። ወታደሩ እና ፖሊሱ ቤተሰቡን ከሌቦች እና ከዘራፊዎች ሌት-ተቀን መጠበቅ አለባቸው።

ሽማግሌዎች የተጣሉ የቤተሰብ አባላትን ማስታረቅ አለባቸው። እናቶች ብላቴናዎች እና ህፃናትን በዚህ ችግር ጊዜ መንከባከብ እና እንደሚገባው በስነ ሥረዓት ወግና ባህላቸውን ጠብቀው ማሳደግ አለባቸው።

ከሁሉም በላይ አባ ወራው እና የቤተሰቡ መሪ ቆፍጣና እና ቆራጥ ሆኖ ቤተሰቡን መምራት እና ከዚህ ችግር ለማውጣት ሌት ተቀን መስራት አለበት።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን ተረድቶ ወደ አገር ግንባታ መግባት አለበት። ለውጡን ማስቀጠል እና ከነ ዶ/ር አብይ ጎን ቆሞ ይችን ይቺን የተዘረፈች እና የፈረሰችን ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ቤታችንን መልሶ መገንባት ምርጫ ሳይሆን የሁላችንም የሞት የሽረት ግዴታ ነው።

No comments