Ethiopianism

በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ከአስር በላይ በሚሆኑ ከተሞች ታላላቅ ሰልፎች ተደረጉ - ትንሳዔ



በአማራ ክልል ከአስር በላይ በሚሆኑ ከተሞች ታላላቅ ሰልፎች ተደረጉ

በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ከአስር በላይ በሚሆኑ ከተሞች ታላላቅ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን ሁሉም ሰልፎች በሰላም መጠናቀቃቸውን በየስፍራው የሚገኙ ሪፖርተሮቻችን ዘግበዋል።
በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ከአስር በላይ በሚሆኑ ከተሞች ታላላቅ ሰልፎች ተደረጉ። ሰሞኑን የማንነት ጥያቄ ባነሱ ራያዎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ በማውገዝ፣ በተነሱ የማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ የፌዴራል መንግስቱ ፍትሃዊ ምላሽ እንዲሰጥ እና ላሊበላ እና ጣና አፋጣኝ ትኩረት እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ነው በተመሣሳይ ሰዓት ሰልፎቹ የተደረጉት።

በተለይ በጎንደሩ ሰልፍ ከራያና ወልቃይት ማንነት ጥያቄ በተጨማሪ ሌሎች ጥያቄዎች የተስተጋቡ ሲሆን ፡ከነዚህም መካከል ፦” ውሃ የተዘጋበት እና ውሃ የተጠማው የሐረር ሕዝብ ፍትሀዎ ምላሽ ያግኝ! 

ህወኃት ከአፋር ወገኖቻችን ላይ እጁን ያንሳ!” የሚሉት ይገኙበታል። ከዓመት በፊት በተደረገው የነጻነት ትግል ከፍተኛ ሕብረትና አንድነት የተስተዋለው- በጎንደር በተደረገ ሰልፍ “የኦሮሞ ደም ደሜ ነው!”የሚል መፈክር በመስተጋባቱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።

ሰልፎቹ እየተደረጉ ባሉበት ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በመሆን በሄሊኮፕተር ወደ ጣና በማቅናት እምቦጭ አረም የደረሰበትን አስከፊ ደረጃ ጎብኝተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ በጭፈራ ለተቀበሏቸው አርሶ አደሮች “አይዟችሁ! እምቦጭን እናጠፋዋለን!! ተመልሼ መጥቼም ዐያችኋለሁ” በማለት ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፦

" ዛሬ ጠዋት ከጣና ጀምረን ደንቢያ አካባቢና ሊቦከምከም አካባቢ እምቦጭ የሚባል ብቻየን ካልኖርኩ የሚል ጠላት ጎብኝተናል፡፡ የገባኝ ሚስጥር እንደ ጣልያን ርብ ላይ እንደሚሸነፍ ተረድቻለሁ፡፡ጠላቶቻችን በዚህች ቅድስት ሀገር ላይ ጦርነት ቢያውጁም አሸንፈው አያውቁም፡፡ 

እምቦጭንም እናሸንፈዋለን፡፡ኢትዮጰያ የአፍሪካ ውኃ ማማ ካስባሏት አካባቢዎች አንዱ ይህ አካባቢ ነው፡፡ ነገር ግን ውኃ፣ ጉልበትና መሬት እያለ አቀናጅተን አልተጠቀምንም፡፡ይህንን የእልህ የሆነ ዝናብ፣ ፀሐይ፣ እምቦጭ በጋራ እንደምናሸንፍ እንድንችል በጋራ እንድንቆም ይገባል፡፡ አሁን ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው መደመር ብቻ ነው፡፡ እንደ እምቦጭ ሁሉም ለእኔ ከሆነ ተያይዞ መጥፋት ነው"ብለዋል።

አርበኞች ግንቦት ሰባት ትናንት በአርባ ምንጭ እጅግ ደማቅና ስኬታማ ሕዝባዊ ስብሰባ አደረገ። በፕሮፌሰር ብርሃኑ እና በአቶ ኤፍሬም ማዴቦ የተመሩት የንቅናቄው ልኡክ ቡድን አባላት ከትናንት በስቲያ ማምሻውን አርባምንጭ ከተማ ሲገቡ የዞኑ አመራር አካላትና የከተማ ነዋሪዎች አርባ ምንጭ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡ 

ሊቀመንበሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በግንባሩ እና በአርባምንጭ ህዝብ መካከል ያለዉ ስሜት እና ቁርኝት ጥልቅ መሆኑን ፕሮፈሰሩ ገልጸዋል።  

የግንባሩ ፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በበኩላቸዉ አርባ ምንጭ ከተማ ለግንባሩ ከፍተኛ መስዋትነት የከፈሉ ጀግኖች መኖሪያ በመሆኗ ከዚህ ህዝብ ጋር መገናኘት ደስታ የሚፈጥር ነው ሲሉ ተናግረዋል። 

በትናንትናው ዕለት በተደረገው ሕዝባዊ ስብሰባ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የከተማውና የአጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች አረንጓዴ፣ቢጫና ቀዩን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ በስፍራው በመገኘት ለንቅናቄው ያላቸውን አጋርነት አረጋግጠዋል።

ከሽብርተኝነት ክስ ጋር በተያያዘ የመዘጋት እርምጃ የተወሰደባት የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “ፍትሕ” ጋዜጣ ዳግም የህትመት ብርሃን ልታይ መሆኑ ተገለጸ።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፡ኢትዮጲስ”በሚል ጋዜጣ የዛሬ አራት ሳምንት ወደ ሙያው መመለሱን ተከትሎ አሁን ደግሞ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቀድሞዋ ታዋቂ ጋዜጣው በፍትህ ነጻውን ፕሬስ ሊቀላቀል መሆኑን አሳውቋል። 

በርካቶችም በፍትህና ጋዜጣ ዳግም መመለስ ደስታቸውን እየገለጹ ነው።“የለውጡን ፍላጎት መሸከም የሚችል 'ስቴት' ለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ፤የሽግግር ሂደት ላይ ፣ ያውም የታሪክ መጋጠሚያ ምዕራፍ ላይ መሆናችን አይካድም” ያለው የፍትሕ ጋዜጣ ወዳጅ ሙሉዓለም ገብረመድህን ፤ የለውጥ ውርጃ በበዛባት ኢትዮጵያ ፤ህዝቧ- በፖለቲከኞቹ ብኩንነት የተነሳ በእምነትና በክህደት አዙሪት ውስጥ ሲባዝን እንደኖረ እና በዚህም ሁለት ሦስት ብለን የምንቆጥራቸው የለውጥ ዕድሎች መክነው እንደቀሩ አትቷል፡፡  

“ይሄኛው የታሪክ መጋጠሚያ ምዕራፍ ግን ለአገሪቱም ሆነ ለህዝቧ የመጨረሻው ይመስላል” ያለው ሙሉዓለም ፤ ለፍትሃዊ ሥርዓትና ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች እታመናለሁ የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን አስተዳደር አራተኛው መንግሥት በሚባለው በፕሬሱ ለመሞገት፤ የግፉአን ጠበቃ የሆነ እውነተኛ ፕሬስ አስፈላጊ ነው” ብሏል። 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) አንድ የሥራ ኃላፊ ከትናንት በስቲያ ማምሻውን መታሰራቸውን የትንሳኤ ምንጭ ጠቆሙ። ከትናንት በስቲየሰ በድንገት በፖሊስ ቁጥትር ስር የዋሉት፤የቴክኒካል መረጃ ዲቪዥን ኃላፊ በመሆን ሢሰሩ የነበሩት አቶ ኃይላይ ብርሀነ ናቸው።  

አቶ ብርሃነ ማምሻውን በፌደራል ፖሊስ ተይዘው ወደ እስር ቤት የተወሰዱ ሲሆን፤ የታሰሩበት ምክንያት እስካሁን አልተገለጸም። የኢንሳ ኃላፊ የነበረው አቶ ቢኒያም ከታሰረ ሦስት ወራት መቆጠራቸው ይታወቃል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ በመስቀል አደባባይ የግድያ ሙከራ በተደረገ ማግስት የታሰረው አቶ ቢኒያም፤ በተደጋጋሚ ያቀረበው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሆኖበታል።

ሌሎችንም መረጃዎችና ወቅታዊ ፕሮግራሞች አጠናቅረናል።
ትንሳዔ የእርስዎ ራዲዮ

No comments