Ethiopianism

ለከሃዲ ትንሳዔ ሙታን የለውም! (መስቀሉ አየለ)



ለከሃዲ ትንሳዔ ሙታን የለውም!

እንደሚታወቀው በምርጫ በዘጠና ሰባት ህዝቡ የመረጠው መኢአድን ወይንም ኢዴፓን ወይንም ቀስተደመናን አልነበረም።ቅንጅትን እንጅ ። 


ነገር ግን ከምርጫው ማግስት አራቱም ድርጅቶች ይበልጥ ጠንክረው በመውጣት ወደ አንድ አገራዊ ደጀን ፓርቲነት ለመሸጋገር እንዲያስችላቸው ቀድመው በተስማሙት መሰረት ወደ ሙሉ ውህደት ለማምራት መፈራረም ሲቀራቸው ልደቱ የኢዴፓን ማህተም በኪሱ ይዞ ጠፋ። 

በወቅቱ የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ የነበሩት እነ ዶር አድማሱ፣ አቶ ክፍሌ ጥግነህና አቶ ይሳሃቅ ክፍሌ የመሳሰሉትአብላጫ ቁጥር ስለነበራቸው በድምጽ ብልጫ ወስነው ሌላ ማህተም አስቀረጹና ፊርማውም ተካሂዶ የቅንጅት የውህደት ስነስዓት እንዲያልቅ ቢደረግም ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አቶ ልደቱ ቀድሞ ለምርጫቦርድ በሚስጥር ባስገባው የተቃውሞ ደብዳቤ የተነሳ የወያኔው ምርጫ ቦርድ ውህደቱን እንደማይቀበለው አስታወቀ።  

ከዚያም ቅንጅት ሆነው የተመረጡት እነ ልደቱ ስንት የእንጨት ለቃሚ ልጅ አስገድለው "ኢዴፓ" ሆነውና የህዝብን እምባና ደም እረግጠው እነ ሙሸ ሰሙን ከመሰሉ ጥቂት ገብረበላዎቻቸው ጋር ፓርላማ ገብተው የደሃ ገበሬን ግብር ደመዎዝ አድርገው ኖሩ።

ሙሸ ሰሙን ለዚህ ውለታው አላሙዲን የበቅሎ ቤት ቅርንጫፍ የዳንሸን ባንክ ስራ አስኪያጅነቱን ስልጣን ሰጥቶታል።ልደቱ በዚያም አልበቃውም።ወያኔ "ቅንጅት መንፈስ ነው" የሚለውን የወቅቱን የትግል ስፕሪት ለመስበር ሲል ስሙን ለጫሚሶ ሲሰጥ ልደቱ ደግሞ ላይጠቀምበት "V" የሚለውን የቅንጅት አርማ እንደቅርጫ ተቃርጦ በመዉሰድ ቅንጅትን በመግደሉ በኩል የራሱን ሚና ተጫውቷል።

ባለፈው ሰሞን የወጣው ሰነድ እንደሚያሳየው እነ አየለ ጫሚሶን ጨምሮ ስንቱ "ተቃዋሚ ነኝ" ባይ ከጌታቸው አሰፋ በሚስጥር በሚመደብ በጀት ይተዳደሩ እንደነበር ይፋ ከመሆኑም በላይ አቶ አያሌው የተባለው የቀድሞው የደህንነት ባለስልጣን ልደቱ መቸና እንዴት እንደተመለመለ በዝርዝር ሲያጋልጥ ልደቱ ትንፍሽ ያለው ነገር የለም። 

በሂደት ወያኔም የልደቱ ነገር ከረሜላን ከነልጫው መምጠጥ ሲሆንበት ተጠቅሞ ጣለው ቢባልም ቅንጅትን ለማፍረስ በዋለው ውለታ ግን በወቅቱ አቡነ ጳውሎስና አላሙዲን በተወከሉበት ኮሚቴ ዳጎስ ያለ ብር ተቀብሎ ስለነበር በዚያችው ቅጽበት የሰማያት ደጅ ተከፍቶለታል።

ዛሬ ልደቱ በደብረዘይት መንገድ ያስገነባው ገስት ሃውስ፣ ላሊበላ ጥቂት ሰዎችን ለሽፋን በሸር ስም አስገብቶ በመስራት ላይ ያለው ሪዞርት፣ በአሜሪካን አገር የገዛው ነዳጅ ማደያ ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው።

እርሱና ጥቂት ጓደኞቹ ባስጨነገፉት የምርጫ ዘጠና ሰባት እነፕሮፌሰር መስፍን "ህዝብ ይበልጣል" ብለው እስር ቤት ገብተው ከብዙ ጫና በኋላ ወያኔ ሲፈታቸው አረጋውያኖች የራሳቸውን ሂደት ሄደው እድሜ ሲገድባቸው እነ ደብረ ሌጊዮን ደግሞ በበኩላቸው "አለም አስር ናት" ብለው የኢትዮጵያን ህዝብ የኢንተርኔት ዳታ ነፍገው 

እነርሱ ግን ፖርኖግራፊና የሩቅ ምስራቅ አገሮችን ሴተኛ አዳሪዎች ኤጀንሲ ሲያሳድዱ ትግሉ ሌላ መልክ ያዘና ትንሽ ልጅነት የነበራቸው የያኔዎቹ ቅንጅቶች ደግሞ አ/ግንቦት ሰባት ተብለውና ወደ ነፍጥ ማንሳቱ ጎራ ገብተው ዛሬ የወያኔን የሴኪዩሪቲና የወታደር ሞኖፖሊ በሻቢያ በኩል ጠምዝዘው ቁማሩን ከበሉ ቦሃላ መሃል አዲስ አበባ ከች ሲሉ ትንፋሽ ከሚያጥራቸው ውስጥ አንዱ ልደቱ ጭምር እንደሆነ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ በደመነፍሱ ያውቀዋል።  

እርሱም እንደሆነ በግዜው "ነውሬን ቢሸፍንልኝ" በሚል አንድ "የአርም እርሻ" የሚል የመጸሃፍ ድሪቶ ላይ የፈለገውን ዘብዝቧል። ቁም ነገር አገኝበታለሁ የሚል ካለ ፈልጎ ማንበብ ነው። በተረፈ ግን ከብዙ ቆላ ደጋ በኋላ የሞራል የበላይነቱን አስጠብቆ ዛሬ በድል ወደ አዲስ አበባ የገባው ዶር ብርሃኑ የፖለቲካ ሞት ሞቶ ገንዘብ ካተረፈው ሻይሎክ ጋር ክርክር የሚገጥምበት ሂሳብ ይኖራል ብሎ ማሰብ አንድም የፖለቲካን ጥበብ አለማወቅ አንድም እንደ እስራኤል ዳንሳ የሞተውን አስነሳለሁ አይነት ቁማር ነው። 

ህዝቡ በበኩሉ ይህችን ቀርቶ የዝንብ ጠንጋራ ያውቃልና የራሱን ፍርድ ሰጥቶ ዛሬ ሌላ ምእራፍ ላይ ደርሷል። ሰውየውም ገና ብዙ ስራ አለበትና የራሱን ሂደት ሄዶ ለሞተው ለልደቱ እንካ ስላንቲያ ቦታ፣ ትእግስትና ግዜ ቀርቶ የሚተነፍሰው አየር እንደማይኖረው ዛሬ አገራችን ያለችበትን በጣም ተለዋዋጭ የፖለቲካ ስፔክትረም የሚያውቅ ሁሉ የሚረዳው ነው።

ዋናውን ትግል ትቶ እነበረከት ስሞን በየግዜው በሚሰጥን አጀንዳ ስንነታረክ መዋል ግዜው ያለፈበት ጨዋታ ነው። መቸም ከቀን ጅቡ ጋራ መቀሌ ሲዶልት የከረመው ልደቱ ቢሆን ግን "ፖለቲካ በቃኝ" ባለ ማግስት ዛሬ ተመልሶ ለምን እንደሚርመጠመጥ ግልጽ ነው። ታሪክ አንድን ወንዝ ሁለት ግዜ አይሻገሩትም ይላል።

No comments