Ethiopianism

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ (ታፈሰ በለጠ)



የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ (ታፈሰ በለጠ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ታሪካዊነቱም ሆነ ዓላማው ጥንታዊ ነው፡፡ አንድ አገር የሚለየውና የሚታወቀው በድንበር፣ በሕዝብና በሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ አንድ አገር አንድ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ነው የሚኖረው፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ ወደ ታች፥ አረንጉዋዴ፥ ቢጫና ቀይ ቀለማት ናቸው፡፡ ይህ የሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ የነዚህ ቀለማትና ቅርስ የተረጋገጠው ከዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ በፊት ጀምሮ ነው፡፡ ቀደም ብሎም ኢትዮጵያ መንግሥታዊ አስተዳደር ከነበራት ዘመን ጀምሮ ይህ ሰንደቅ ዓለማ በሕዝብ ሲውለበለብ ቆይትዋል፡፡

ከቅርቡ ልጀምርና፥ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመንግሥታዊ አስተዳደር ዘመናት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ አረንጉዋዴ-ቢጫ-ቀይ ነበር፡፡ ይህም ሕዝብ በበዓል ጊዜ በየደጁ የሚሰቅለው፣ በየቤቱ የሚያንጠለጥለው፣ በሠርግ ጊዜ የሚሸፈንበት፣ በየመሥሪያ ቤቶች በይፋ የሚሰቀለው፣ በዓለም አቀፍ መድረኮችና በውጭ አገራት በኢትዮጵያ መልክተኛ ጽሕፈት ቤቶችና በኢትዮጵያ መርከቦች የሚውለበለብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም የዚህ ምልክት ተሸካሚ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከዳር እስከዳር በሕዝብ የሚውለበልበው ይህ ሰንደቅ ዓለማ ነው፡፡ በየትምህርት ቤቶች ጠዋት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ተማሪዎች በረድፍ ተሰልፈው …ደሙን ያፈሰሰ ልቡ የነደደ…እያሉ በሰንደቅ ላይ የሚሰቅሉትና ማታም ከክፍል ሲወጡ ..ተጣማጅ አርበኛ… እየዘመሩ አውርደው፣ በስነሥርዓት አጣጥፈው ለማግስቱ የሚያስቀምጡት ይህንኑ ባለሦሰት ቀለማትና ምንም ምልክት የሌለውን ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀልና ሲወርድ በተለይም በአካበቢው የሚገኘው ሁሉ በአክብሮት ቀጥ ብሎ ባለበት ይቆማል፡፡ በተለይም ወታደራዊ ተቋማት ባሉበት አካባቢ የሙዚቃ መዝሙር ድምፅም ከሩቅ ስለሚሰማ፣ እግረኛው በተጠንቀቅ ቀጥ ብሎ በመቆም፣ ባለመኪናውና ባለጋሪው መሬት ወርደው አክብሮታቸውን ለሰንደቅ ዓላማው በኅሊና ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ በሠርግና በኀዘንም በከፍተኛ የክብር እርከን የሚታይ የመደሰቻና የመጽናኛ ምልክት ነው፡፡ ከሙሽሮች በስተጀርባ በጌጥነት የሚታየው ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ አንድ ጊዜ የገጠመኝ፥ ከአሥመራ ወጣ ብሎ በሚገኝ ፀዓዳ ክርስትያን በሚባል መንደር የቀብር ሥርዓት ላይ ሆኜ ግብዓተ መሬቱ ሊፈጸም ሲል ድንገት ኃይለኛ ንፋስ መጣ፡፡ አንድ አስተናባሪ በጉልህ ድምፅ በትግርኛ ‹‹ሰንደቅ ዓለማዎቹን አጥብቃችሁ ያዙ›› ሲሉ በዙሪያው አጅበው የከበቡት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማዎችን የያዙት ሰዎች ሰንደቆቹን ፍርጥም አድርገው ሲይዙ የሰጡት አክብሮት የተለየ ነበር፡፡

እንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ቀለም አረንጉዋዴ፥ ቢጫና ቀይ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥታትና አስተዳደር አቋም እንዴት ነበር?

በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሥርዓተ መንግሥትና አገራዊ አስተዳደር ዘመን የሕዝብ ሰንደቅ ዓላማው እንዳለ ሆኖ የንጉሳሣ ሥርዓት መገለጫ የሆነ በሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ መሐል በቀኝ ኮቴው ሰንደቅ ዓላማ የያዘ አንበሳ ተደርጎበታል፡፡ ይህም ሰንደቅ ዓላማ በተወሰነ መንገድ ብቻ ነበር ጥቅም ላይ የዋለው፡፡ በቤተመንግሥቶቻቸው ብቻ ነበር የሚሰቀለው፡፡ ጃንሆይ በሚጉዋዙባቸው ተሽከርካሪዎች ላይም ከአሽከርካሪው በስተቀኝ ባለው የተሽከርካሪው የፊት ጫፍ ባለአንበሳው የንጉሠ ነገስቱ ሰንደቅ ዓለማ ይውለበለባል፡፡ ያሰቃቀሉም ትርጉም ጃንሆይ ከተሽርካሪው የሁዋላ ወንብር በቀኝ በኩል ተቀምጠው እየተጉዋዙ ነው ማለት ነው፡፡

ንጉሡ ለፍልሰታ ጾም ድሬዳዋ በሚቆዩባቸው ቀናት የራሳቸው ባለአናበሳው ሰንደቅ ዓላማ በድሬዳዋ ቤተመንግሥት ይሰቀላል፡፡ አምሳ እርምጃ ርቀት ላይ ባለው የድሬዳዋ ማዘጋጃ ቤት ማማ ላይ የሚሰቀለው ግን የሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ በምጽዋ ለባሕር ኃይል መኮንኖች ምረቃ በየዓመቱ ሲገኙ በምጽዋ ቤተመንግሥት ባለአንበሳው

ሰንደቅ ዓላማ ይሰቀላል፣ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ይወርዳል፡፡ ቤተመንግሥቱ ውስጥ የሉም ማለት ነው፡፡ በከፍተኛ ድምቀት በሚከበረው የባሕር ኃይል ምርቃት ላይ የሚሸበርቀው ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ነው(ነበር)፡፡ በመናገሻ ከተማውም ባለአንበሳው ሰንደቅ ዓላማ የሚውለበልበው በኢዩቤልዩ ቤተመንግሥት ላይ ነበር፡፡ ተሰቅሎ ካልታየ ወደ ውጭ አገር ሄደዋል ማለት ነው፡፡

ባለአንበሳውን የንጉሡ ሰንደቅ ዓላማ በዘመኑ ሕዝቡ እምብዛም አያውቀውም፡፡ ምክንያቱም የራሱን ሕዝባዊ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ስለሚሰቅል፡፡ የንጉሡ ሰንደቅ ዓላማ ታዋቂነት ያገኘው በቅርብ ጊዜ ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በድርቀት ወቅት ጃማይካን በጎበኙ ዕለት ዝናብ በመጣሉ ሕዝቡ የተለየ እምነት አሳደረ፡፡ ከሰማይ የተላኩ አድርጎ በመቁጠርም ማምለክ ጀመረ፡፡ በቅድመ ንግሥና መጠሪያቸው በራስ ተፈሪ መኮንን ስም የእምነት ዘመቻ ተጀመረ፡፡ በነቦብ ማርሌ ፊታውራሪነት ›‹ጃ ራስ ተፈራይ›‹…. ጃንሆይ ራስ ተፈሪ ማለት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ይህ እምነት በጃማይካ ከታወቁት የይፋ ኀይማኖቶች አንዱ ነው፡፡ ባለአንበሳውን የንጉሣዊ ሰንደቅ ዓላማ የሚጠቀሙት ራስታዎች ናችው፡፡ እንዲስፋፋ ያደረጉትም እነዚሁ ቡድኖች ስለሆኑ ባለንበት ዘመን ምልክት ከሌለው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ጎን መሰለፍ አይችልም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ በደርግ ጊዜ እንዳለ ቀጠለ፡፡ በሰንደቅ ዓላማው ምንም ዓይነት ምልክት አልተለጠፈበትም፡፡ መንግሥትና የአገር አስተዳደር አጣምሮና ጨፍልቆ ይዞ የነበረው ደርግ የራሱን ሥርዓት ነድፎ ነበር፤ በሕዝቡ ሰንደቅ ዓለማ ላይ ግን ምልክት አልለጠፈም፡፡ ሕዝቡ የራሱን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለቡን ነው የቀጠለው፡፡

ደርግን የተክት የወያኔ ወራሪዎች ሲንሰራፉ ለአምስት ዓመታት ያህል ሕዝቡ ጥንታዊውን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ቀጠለ፡፡ ዳሩ ግን፣ በኢትዮጵያ ላይ የተሸናፊውን የፋሽስትን የሽንፈት በቀል ለማስፈጸም ወያኔ ያተኮረው አገር በመከፋፈል፣ ቅርስ በማውደም፣ የጥላቻ ግጭት በመፍጠርና በታሪክ ክለሳ ላይ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ በ›‹ጨርቅነቱ‹‹ ጨው የቁዋጠሩበት ገና በረሀ እንዳሉ ሲሆን ተደላደሉና ኮከብ አይሉት አምባሻ ለጠፉበትና የሕዝብ እንዲሆን አወጁ፡፡ የሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ለመጀመሪያ ጊዜ ምልክት ተለጠፈበት፡፡ የባለምልክት ዓላማ የያዘ ተቀጣ›፣ ታሰረ፣ ተደበደበ፣ ተሰቃየ ተገደለም፡፡

ወያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማን በራሱ ዓላማ ለመተካት ሲሞክር አሻፈረን ብለው በኢትዮጵያው የተኩትን አሰረ ረሸነ፡፡ የተከራከሩትን አፈነ ሰወረ፡፡ በሕዝቡ ላይ አእምሮአዊ ተጽኖ ለማሳደር እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማውን የበለጠ ለማዋረድና ለማርከስ፣ ክብሩንም ለማሳነስ ድንክ ሰንደቅ ዓላማዎች አከፋፋፈለ፡፡

‹‹ክልል›› የኢጣልያ ንድፍ ነበር፡፡ በሥራ ሳይተረጉመው በጅምር ተሸንፎ ሄደ፡፡ አዲሶቹ የወያኔ ክልሎች ድንክ ሰንደቅ ዓላማዎች ታደላችው፡፡ አንዳንዶቹ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ በእኩልነት ተውለበለቡ፡፡ ከክልል ውጭ የሆኑም የሕዝቡን (የአገሪቱን) ሰንደቅ ዓላማ ለመተካት ከፍ ብለው በሰርጎ ገብነት መውለብለብ ጀመሩ፡፡ በየትም ዓለም የብሔራዊ ሰንደቅ ዓለማ ከውስጥ የአስተዳደር ምልክቶች በበላይነት እንጂ በእኩልነት አይውለበለብም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፎካካሪ ምልክቶች በግትርነት ይታያሉ፡፡

ኢትዮጵያ የሚኖራት አንድ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ነው፡፡ በኣንድ አገር አንድ ሕዝብ አንድ ሰንደቅ ዓላማና አንድ ድንበር ብቻ ነው የሚኖረው፡፡ አስተዳደራዊ ድንበር ለእድገት ፍጥነት ምክንያት ነው እንጂ አገሮች፣ ሕዝቦችና ምልክቶች መፈልፈያ አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ በስተቀር በአገሪቱ ውስጥ ሌሎች የአገሪቱ ምልክቶች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሕዝቡ በአሁኑ ጊዜ በትልቅ ኩራትና የወኔ ራሱን ጥንታዊ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ ነው፡፡



ጳጉሜ 2ሺ10

No comments