Ethiopianism

አንታረቅም ወይ ?! (አሌክስ አብርሃም )



አንታረቅም ወይ ?


አንታረቅም ወይ ?! 

(አሌክስ አብርሃም)



እኔ ናፍቀሽኛል መናፈቅ አይበለው 

ነፍስሽ ነፍሴን ገፍቶ በኔ ሰውነት ውስጥ አንችነት ነው ያለው!!

ከያኔ በኋላ የኔ ሳቅ ጠፍቶኛል ያንችን ነው የምስቀው

የኔ ጸሃይ ጠልቋል ያንችን ነው የምሞቀው !

ገና ዶሮ ሳይጮህ በምስራቅ አድማስ ላይ ትዝታሽ ይወጣል 

ናፍቆት ሃይ ባይ ያጣል
በፍቅር ቀለማት የጻፍነው ስንክሳር 
እንደዳዊት መዝሙር ማልዶ ይገለጣል ! 
መኖሬን አቁሜ አንችን አነባለሁ 
ደግሞ እጠይቃለሁ


በነብስ ይፋለጉ የነበሩ ነፍሳት 
ሞት አዝለው ይነፍሱ የነበሩ አንፋሳት 
እንጃ የነካቸውን ለሰላም ዘመሩ 
ፈንጅ የተሞሉ እርሾች 
ሞታቸው ተጠርጎ በቆሎ ተዘሩ 
በደም የጨቀየ ርስት ደረቀ
አኬልዳማ አፈር ላይ አበባ ጸደቀ
ዝግባ ተገርሶ ችግኞች ዛፍ ሆኑ
ገዳዮች ግድያን በጽኑ ኮነኑ
በውሃ ቀጠነ የሚጨፋጨፉ 
በጨፈጨፉት ፊት ታርቀው ተቃቀፉ !
 

ምንድነው የሷ ጸብ ምንስ ነው የኔ ጥል 
ምን አቅፈን እንድኖር ደግሞስ ምን እንድንጥል?!
እኛ ጸሃዮች ነን ?ብናኮርፍ ምድርን ጨለማ ይከድናታል?
እኛ ውቅያኖስ ነን ? ቂማችን አትንኖን ይችን ግዙፍ አለም ውሃ ይጠማታል?
አንታረቅም ወይ ? እያልኩ አስባለሁ! 

<<ምድር ከፍ ሰማይ ዝቅ>>
እየተባባልን ለጸብ ቃል ስንገባ 
ሁለት ሚሊየን እጅ ሚሊየን ጭብጨባ
ጥላቻን የማይገድል የጀግንነት ካባ !
 
እየደረቡልኝ እየደረቡልሽ 
ጥላት ባሉኝ መጠን ይሄው አፈቀርኩሽ ! 

ይኽው በቀደም ለት የቆምኩበት ምድር ወደላይ ከፍ አለ 
ከዛ ላይ ስታይው በዚች የጉድ አለም ስንት ዝቅታ አለ?
ግን ሁሉም ከነቱ ነው !! 
ወደላይም ልውጣ ወደታችም ልውረድ 
አደባባይ ልቁም ጉባኤ መካከል በሽዎች ልዋረድ 
አልያም በጓዳየ በግምጃ ልጋረድ 
አንድ እውነት ግን አለ በመንጋ ወገራ 
በር ላይ በጣሉት የርግማን ደንቃራ
 
ፈጽሞ ያልሞተ ያልተንገዳገደ
ባዳፈኑት ማግስት እንደደመራ እሳት ሽቅብ የነደደ 
ላንችም የማይገባሽ ያበደ እውነት አለ . . . 
ያን እነግርሻለሁ 
በቃ አፈቅርሻለሁ!!

ይሄው በቀደም ለት ወደታች ዝቅ አለ የማልሽበት ሰማይ
አይኖቸን ላኳቸው ከፈጣሪ እግር ስር ከደመናው በላይ 
አንድም ታሪክ የለም ካንች ፍቅር ወዲያ በህዋው የሚታይ ! 
በቃ አፈቅርሻለሁ !

ሰልችቶኝ ነው እንጅ ለገዳይ መናገር 
ያመመሽን ያህል እኔም አሞኝ ነበር !
የሚያደክሙ አጽናኞች ነገር አብርድ ይሉት ቃል ይልኩልኛል 
ከምር ይደክሙኛል ! 
አይገባኝም ቋንቋ ደንቁሬ ነው መሰል 
ምንድነው በሰው ጸብ <<ጸብ አቀዝቃዥ>> መምሰል !
 
ጸባችን አይቀዝቅዝ መቸም ምንም ቢሆን 
ለኔ ፍቅር ማለት ጥላቻ ላይ መንገስ ከጸብ በላይ መሆን 
በቃ አፈቅርሻለሁ !! 

ገሎ ማፍቀር አለ ? ተገሎስ መፈቀር 
አንዴ የሞተ ቀን እንደሰው ዘፍጥረት ይፈጠራል ካፈር? 
እያለ ነው ልብሽ ? 
ገዳይ እኔነቴን ከፈንሽ ጋር ጥለሽ !! 
አስር ጊዜ ሙች አስር ጊዜ ተነሽ
በቃ አፈቅርሻለሁ !

No comments