Ethiopianism

የዚህችን ሀገር መፍትሔ አገኘሁት!!! (በላይ በቀለ ወያ)

ኢትዮጵያ

የጀግኖች ሀገር አይመሽም
አናፈገፍግም ፣ለአንድነት አንሸሽም
ጀግና ይፈጠራል ፥ ጀግና ቢኮላሽም!!!

በብዙ ጥናትና ምርምር ፣ በብዙ ጥረት እና ጥርጣሬ ፣ ከብዙ ድካም እና ትግል በኋላ የዚህችን ሀገር መፍትሔ አገኘሁት። መፍትሔውን ያገኘሁት "ችግራችን ምንድን ነው?" ከሚል ጥያቄ ተነስቼ ሲሆን መልሱም ቀላል ነበር።

"ችግራችን መከፋፈል እና መከፋፈል ብቻ ነው!አንድነታችን የሚጠቅም ሆኖ ሳለ ፣ አብሮነታችን ኋይል ሆኖን ሳለ "መለያየታችን ለምን አስፈለገ? ማን ከፋፈለን ፣ ለምን መከፋፈላችን ተፈለገ፣ መራራቃችን ስለምን ተወረጠ?" የሚል ጠያቂ አይጠፋም።

መልሱ ግን እጅግ በጣም ቀላል ነው። "አንድ ህዝቦች ስንሆን የሚያሸንፈን ኋይል እንደሌለ ስለሚታወቅ በቻ ነው።" ጣልያንም ፣እንግሊዝም የማንበገር አንድ ህዝቦች መሆናችንን ሲያውቁ ኋያል ሀገር እንዳንመሰርት በመሀከላችን ቀብረውብን ያለፉት ነገር እየቆየ የሚፈነዳ የመለያያ ፈንጅ ነው።

ወያኔም ስልጣኑን ለማራዘም በጎሳ ፣በሀይማኖት ፣ በአርማ ሲከፋፍለን የኖረው አብሮነታችን ለወሮ በላ ፖለቲካ እድሜ እንደማይሰጥ ስላወቀ ነው። ታዲያ አንድነታችን ማንንም የማይጎዳ አማራጭ የሌለው ምርጫ ሆኖ ሳለ ኋያልነታችንን የማይፈልጉ ፀረ ኢትዮጵያ ኋይሎች ፣ የአብሮነታችን ጠላቶች ፣ ለግል ጥቅማቸው ፣ለሥልጣን ጥማቸው ፣ ሲሉ የራሳቸውን ኋያል ሀገር ለመገንባት ሲሉ ፣ የራሳቸውን ከርስ ለመሙላት ለሌላው ሀገር ቅጥረኛ ባንዳ ሆነው በማገልገል ኋገርና ህዝባቸውን ለመበደል ሲሉ ፣ ይህን ኋያል ህዝብ በዘርና በሐይማኖት ሲከፋፍሉት ኖረዋል።

ከፋፍለውትም ፣መፅሐፉን ፣ ስነ ልቦናውን ፣ ሀብት ንብረቱን ፣ርስቱን ፣ጥበቡን ፣ ላቡን ጉልበቱን ጊዜውን ፣ውብ ታሪኩን ፣ውብ ባህሉን፣ ማንነቱን ዘርፈውታል። ህብረቱን በትነውት ኋያል አንድነቱን አዳክመውታል። እርስ በእርስ አባልተውታል። ዓንድ ሳለ ዓለምን የሚረዳ ህዝብ ከፋፍለውት ድህነትን አውርሰውታል። ከአለም በፊት ለገላው ልብስ የሸመነን ህዝብ እርቃን አስቀርተውታል። አንድነቱን ካዳከሙት በኋላ የትየለሌ ግፍ አዝንበውበታል።

ሳቁን ከቀሙት በኋላ ለአመታት አስለቅሰውታል። ከዚህ ሁሉ ግፍ መኋል "አንድ ቀን ይነጋል!" የሚል ተስፋ በልቡ ይዞ በጨለማ ውስጥ ተጉዞ ፣ ከዘር በሀይማኖት ከፋፍለው እንደጎተቱት ከአለም ፊት የነበረች ሀገሩን ከአለም ኋላ አስከትሎ ዛሬ ላይ ደርሷል። ዛሬም ግን ችግሩ አልተፈታለትም ፣ችግሩ አልተቀየረለትም።

ዛሬም ችግሩ በዘር በሀይማኖት ፣በጎሳ መከፋፈል ነው። ዛሬ ግን "አንድ ቀን ይነጋል!" የሚል የተስፋ ቃሉን እውን የሚያደርግበት ጥሪ ተደርጎለታል። ዛሬም አንድነታችንን ፣ኋያልነታችንን፣ህብረታችንን የማይፈልጉ ኋይሎች እንዳናንሰራራ ለግል ጥቅማቸው ፣ለስልጣን ጥማቸው ሲሉ ህዝቡን ከህዝብ ለመከፋፈል ዘርና ሀይማኖትን መሣሪያቸው አድርገውታል።

ነገር ግን በመንግስት ደረጃ አንድነታችን ምርጫ የሌለው ምርጫ መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ ይገኛል።አንድነታችን ኋያልነታችንን እንደሚመልስልን ተገንዝበው ስጋት የሆነባቸው አካሎች የመጣውን የአብሮነት የጥሪ ድምፅ ለማፈን በየ ቦታው ዘር እና ሀይማኖት ተኮር ግፎችን ጩኸቶችን ፣ሁከቶችን ፣ብጥብጦችን ፣እየፈጠሩ ተረጋግተን ወደ ልቦናችን ተመልሰን እንዳናስብ ለማድረግ እየተውተረተሩ ይገኛሉ።ይህን የአንድነትን የጥሪ ድምፅ ለማፈን በሚደረጉ ጩኸቶች መሐል ላይ ቁሜ በጥሞና መመራመር ጀመርኩ።

ተመራምሬም ለሀገሩቱ ችግሮች ቁልፍ መፍትሔ አገኘሁ። አእምሮዬን አስጨንቄ ፣ማጥጬ ፣ጨምቄ ያገኘሁትን መፍትሔ "ጠላትን በቀላሉ የማሳፈሪያ ጥበቦች " የሚል ርእስ ሰጥቼዋለሁ።


ጥበብ አንድ፦ በዘር በሀይማኖት ፣በወዘተ ነነሮች ከፋፍለውን አንድ ሆነን ኋያል ሀገር እንዳንገነባ ያደረጉን ጠላቶች ያፍሩ ዘንድ አንድ ሆነን አንዲት ሀገር ስንገነባ ይመልከቱን።

አለዚያ የአንድነታችንን ጠላቶች ሀሳብ አስፈፃሚ ሆነን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እርስ በእርሳችን ከተከፋፈልን ፣ከተጫረስን እኛ አንጀታችን እያረረ ስንኖር የጠላትን አንጀት ቅቤ እየጠጣ ይኖራል። መሣቅ እየፈለግን መሣቂያ እንሆናለን።የከፋፈለንን የምናሸንፈው ከስልጣን በማውረድ ሳይሆን በመሰብሰብና አንድ ሆነን በፊቱ በመቆምና ህብረታችንን በመመለስ ፣ኋያል መሆናችንን በማሳየት እንደሆነ እንወቅ።

ጥበብ ሁለት፦ አንድነትህን አዳክመው በበረቱብህ ፊት አንድ ሆነህ ብርቱነትህን እንደመመለስ ፣ ጠላትህን እንደማሳፈር ምን ደስ የሚል ነገር አለ?!

ጥበብ ሶስት፦ የዚህች ሀገር ችግሮች ሁሉ ምንጫቸው መከፋፈል እንደሆነ እወቅ። ችግሩን ካወክ በኋላ መፍትሔው በቀላሉ ይገለፅልሀል። ችግሩ መራራቅ ከሆነ በአራራቂዎችህ ፊት ተቀራረብ።

በበታተኑህ ፊት ተሰብሰብ። ባቃቃሩህ ፊት ታረቅ። ለአንድነትህ ጠላት በሆኑት ፊት አንድ ሁን።ኋያል ሀገር እንዳትነነባ ባደረጉህ ፊት ኋያል ሁን። ለዚህች ሀገር ያላማራጭ እንድትመርጠው የምሰጥህ መፍትሔ የነበረህን ኋያልነትህን ፣አንድነትህን ፣ ብልፅግናህን ፣ስልጣኔህን ፣ ክብርህን ወዘተ ነገሮችህን በዘር በሀይማኖት ፣በጎሳ ከፋፍለው ቀዳሚ ሀገርህ ኋላ ቀር ባደረጉብህ ፊት ፣ ማንነትህን በቀሙህ ፊት ፣ ወደ ቀድሞው ህብረትህ ተመለስ።

ወደ ቀድሞ አንድነትህ ተመለስ።ያኔ የኋያልነትህ ጠላቶች ያፍራሉ። አንዲት ኢትዮጵያን አንድ ሆነህ ስትገነባ ያፈረሷትን እፍረት ታከናንባለህ። መፍትሔው ይሔ ነው። ትልቅ ነበርን። ትንሾች እንድንሆን በሚፈልጉ ጠላቶች ፊት ትልቅ እንሆናለን።

"የሠላሞን ዕፅ ነሽ ፣ የቅዱሳን ዕንባ ፣ያበቀለሽ ቅጠል
ዛሬ አዲስ አይደለም ፣በለኮሰው እሳት፣ የነካሽ ሲቃጠል
ሳይወሰን ዝናሽ በቅርሶችሽ ድርሳን ፣ ባድባራት ታሪኩ

ነብይ አይተው ከሩቅ ፣ያሉልሽ በመፅሀፍ ፣ኢትዮጲያን አትንኩ"

No comments