Ethiopianism

የለውጥ ባቡሩ የፈጠረብኝ ተስፋ እና ድብታ (ሌሊሳ ግርማ)

የለውጥ ባቡሩ የፈጠረብኝ ተስፋ እና ድብታ (ሌሊሳ ግርማ)

“ተደመሩ ወይ ተመርመሩ” ይላል የባቡሩ ትኬት …
· “እንደ ጥይት በሚምዘገዘግ፣ ሁሉንም የሚያድን ባቡር ላይ ተሳፍረናል…”


የሚካሄደው ነገር በጣም ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ እንደ አንድ ተመልካች ሂደቱን ሁሉ መገንዘብ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን ተስፋ አስቆራጭ ሳይሆን ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ የዶ/ር አብይን የአሜሪካ ጉዞ ልቅም አድርጌ ስከታተል ከቆየሁበት ቅዳሜና እሁድ ወጥቼ ሰኞ ላይ ነቃሁኝ፡፡ ነቃሁኝና ወደ ከተማ ወጣሁኝ፡፡ 

ቴሌቪዥን የሌለበት ቦታ ላይ ተቀምጬ መፃፍ ፈልጌአለሁኝ፡፡ ግን ምን እንደምፅፍ ፈፅሞ አላውቅም፡፡ የምጠቁመውም ይሁን የምጨምረው ሀሳብ የለኝም፡፡ ደግም የተሰማኝን ስሜት ሁሉ ብፅፍ ስሜቱ ቀጥሎ በሚመጣው አዲስ ክስተት የድሮ ስሜት ይሆናል፡፡ መፃፍ እፈልጋለሁ፤ ግን ባልረጋ የክስተት ዝብርቅርቅ ውስጥ ዘላቂ ፅሁፍ ማርቀቅ አልቻልኩም፡፡ አይቻልምም፡፡  

ፌስ ቡኩን በአንድ እጄ ይዤ፣ በአይኔ ከቴሌቪዥኑና ከስልክ እስክሪኑ መሀል ስመላለስ ነው ቅዳሜና እሁድን ያሳለፍኩት፡፡ አርቆ ለማስተዋል፣ የሚስተዋለው ነገር አንድ ቦታ ረግቶ መቆም አለበት፡፡ ወይንም ከሂደቱ የተነጠለ አስተዋይ፣ ራሱ ሳይንቀሳቀስ የሚንቀሳቀሰውን ነገር መመልከት መቻል ያስፈልገዋል፡፡ 

ሰው ሁለት ነገር በአንድ ጊዜ ማከናወን አይችልም፡፡ እኔ ደግሞ ሰው ነኝ፡፡ እየተራመድኩ፤ አረማመዴን አቃቂር ማውጣት እንድችል ቆም ማለት ያስፈልጋል። እየፃፍኩ አፃፃፌን እና ብዕር አያያዜን በአንድ ላይ ማስተዋል አልችልም፡፡ ሰው ነኝ፡፡ ሀገሪቷ እያመራች ያለችበት አቅጣጫ ወደ ጥሩ እንደሆነ በተስፋ ደረጃ ተቀብያለሁኝ፡፡

ተደምሬአለሁኝ። ሀገሪቱ ህክምና ውስጥ ናት፡፡ ባቡሩ ወደ ፈውስ ህዝቡን ይዞ እየገሰገሰ ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሀኪሞቹ አሜሪካ ሆነው ፈውሱን ሲያከናውኑ፣ እኔ ቤቴ ሆኜ ታድሜአለሁኝ፡፡ በጣም በፍጥነት ነው እየሰሩ ያሉት፡፡ እርግጠኛ ነኝ እነሱ ከሂደቱ ውጭ ሆነው ጠቅላላውን ጉዞ መከታተልና መተንበይ እንደሚችሉ፡፡ እርግጠኛ ነኝ እነሱ ከእኔ የተሻለ ሂደቱንና ውጤቱን ማስተዋል እንደሚችሉ፡፡ … እርግጠኛ ብሆን ይሻላል፡፡  

ስሜታዊ የሆነውን የህዝብ የደም ከፍታና ዝቅታ አደጋ በማያደርስ መለኪያ እየመዘኑ በጎውን እያቀረቡ፣ አደጋውን እያራቁ ለውጡን ከፊት ሆነው እየመሩ እንዳሉ እተማመናለሁ፡፡ ከተስፋ ውጭ መተማመኛ የለኝም፡፡ እኔ ተጓዥ ነኝ፡፡ ባቡሩ ውስጥ ነኝ፡፡ ከፍጥነቱ አንፃር ጉም በሸፈነው መስኮት ወደ ውጭ አሻግሬ ሳይ ዘላቂ ነገር አይታየኝም፡፡ ውልብ እያሉ የሚያልፉ ክስተቶች አሉ፡፡ ውልብታቸውን ዘላቂያዊ አድርጌ ማግዘፍ አልፈለግሁም፡፡  

ብፈልግም አልችልም፡፡ ህመም አለብኝ፡፡ እየተንቀሳቀስኩ፣ በተለይ በፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ ሆኜ ስለ ጉዞው መናገር አልችልም፡፡ “Motion Sickness” አለብኝ፡፡ ከመነሻ ለመራቅና ወደ መዳረሻው ገብቶ እፎይ ለማለት የሚፈልግ ሁሉ መናጥ አለበት፡፡ መጓጓዣው በጉዞው ውስጥ ሲያልፍ የሚገጥመውን ሁሉ መቀበል አለበት፡፡
እንዲያውም፤ … ከህመም አይነት ሁሉ መልካሙ ህመም “የእንቅስቃሴ ህመም” (“Motion Sickness”) መሆን አለበት … እላለሁኝ። በዙሪያዬ ያለውን ተጓዥ እመለከታለሁኝ፡፡  

ህዝቡ በሙሉ ተጓዥ ሆኗል፡፡ ተደምሯል፡፡ ከፍሎ አይደለም የሚጓዘው፡፡ ጉዞው እንደ ህክምና ነው። ሁሉም ህክምና በባህሪው ተስፋን እንጂ መቶ በመቶ ማረጋገጫ አይሰጥም፡፡ በሽተኛው ስለ መታመሙና ፈውስ ስለ መሻቱ እርግጠኛ መሆን አለበት፡፡ ለፈውስ ሲል ሀኪሙ በሚወስደው “ፕሮሰስ” ውስጥ ማለፍ - መፈረም አለበት፡፡ ከዛ ግን ሀኪሙ ስራውን ሰርቶ እስኪጨርስ መታገስ ይገደዳል፡፡ ሀኪሙ እንደ ባቡሩ ሾፌር ሆኖ፣ የሀገሩን ህዝብ ደምሮ፣ አጭቆ እየከነፈ ነው፡፡ ሁሉም ተጓዥ ህመም ውስጥ እንደነበር የበለጠ የገባው ጉዞው ከመጀመሩ በፊት ቢሆንም የፈውስ ሂደቱ ሲጀምር ግን የበለጠ የተደበቁ የህመም አይነቶች ሁሉ መገንፈል ጀምረዋል፡፡

ዶ/ር አብይ የጉዞው መሪ ነው፡፡ የለውጥ ጉዞ እንደ መደበኛ ትራንስፖርት ሄዶ መመለስ ብቻ አይደለም - መገለጫው፡፡ አይነተኛው ለውጥ ከሄደ ሄደ ነው፡፡ ወደ ኋላ አይመለስም፡፡ መሪው ራሱ ከዚህ በፊት ወጥቶ ወደማያውቅበት ከፍታ ነው ህዝቡን ጭኖ የሚከንፈው፡፡ ግን ከዚህ በፊት ደርሶበት ብቻ ሳይሆን ኖሮበት እንደሚያውቅ ሁሉ … መዳረሻ ተስፋውን ተጨባጭ በሚባል ደረጃ እውን አድርጎ ማበርከት ስለመቻሉ ተጓዡንም ሆነ ራሱን ማሳመን አለበት፡፡ ካርታ እጁ ላይ መኖር አለበት፡፡

የቀዶ ጥገና ሀኪም ሁለት የተጣበቁ ህፃናትን ለመለያየት ከዚህ በፊት አከናውኖ የማያውቀውን ውስብስብ የህክምና ሂደት በልበ ሙሉነትና በብቃት እንደሚያከናውነው እንደ ማለት፡፡ የቀዶ ጥገናው ውጤት 50 በመቶ የመዳንና ሀምሳ በመቶ የመሞት ነው ብሎ ፈፅሞ ሊጠራጠር አይችልም፡፡ እርግጠኛ መሆን ይኖርባታል፡፡ የህዝብን ጥርጣሬ በሚያሸንፍ እርግጠኝነትና ትኩረት ነው የለውጥ ባቡሩን መሾፈር ያለበት፡፡  

ሀገርን ሙሉ ሊገድል አይችልም፡፡ ደግሞ ቀዶ ጥገናው ሲጠናቀቅ፤ ሁለት ተጣብቀው የተወለዱ ህፃናትን መለያየት ሳይሆን … ተለያይቶ የነበረን መቶ ሚሊዮን ህዝብ አንድ አድርጎ መስፋት ነው፡፡ መቶ ሚሊዮን ህዝብን መልሶ ለመስፋት መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኖ፣ እጁን ሰብስቦ ስራ ውስጥ ለመግባት ከፍተኛ ጀግንነት ይጠይቃል፡፡ የሚያስፈራ ቢሆንም ለመፍራት ጊዜ የለም፡፡ ህዝቡ በለውጡ ባቡር ተሳፍሯል፡፡ መሪው የተሳፈረውን ህዝብ ማሳፈር (“ሳ” ሲነበብ ይላላል) የለበትም፡፡  

ደግሞም … ደግሜ ሳስተውል .. የተሳፈርኩበት መጓጓዣ ባቡር እንዳይደለም ተገነዘብኩኝ፡፡ ባቡር ቀድሞ በተዘረጋ ሀዲድ ላይ ነው በፍጥነት የሚገሰግሰው፡፡ ቀድሞ ባልተዘረጋ ሀዲድ ላይ በአንድ ላይ እየከነፉ መገስገስ የሚችሉ መሪዎች ከዚህ ቀደም በምናውቀው የመጓጓዣ ስርዓት መዝገበ ቃላት ልንገልፃቸው የሚችሉ አይደሉም፡፡ 

ታዲያ ለዚህ እኮ ነው … ነገሩ ሁሉ የከበደኝ፡፡ ለዚህ ነው ፍጥነቱ ውስጥ ሆኜ ርቀቱንና አቅጣጫውን መለካት ያቃተኝ፡፡ … መሪን ማመን ያስፈልጋል። የእንቅስቃሴው ፍጥነት አያጥወለወለኝም … ግን በመቀመጫዬ ላይ ጋለል ብዬ ቴሌቪቪኑን እየተመለትኩ በተስፋ መጠበቅ አለብኝ፡፡ ፈጣን ጉዞ ነው እንጂ አዝጋሚ ጉዞ አያጥወለውልም። ግን ፈጣን ጉዞ ብቻ ነው እውነተኛ ለውጥ ላይ የሚያደርሰው።  

አንድ ቦታ ላይ ተቁሞ ስለ ለውጥ ፈጣንነትም ሲሰበክ አውቃለሁኝ። … ባለፉት 40 ዓመታት ህዝቡ ላልተጓዘበት ጉዞ ሲከፍል ኖሯል። በነፃ ወደ ነፃነትና እኩልነት መጓዝ አይቻልም፡፡ ድሮ የከፈለው አዲሱን ለውጥ ለመሳፈሪያ ከበቂ በላይ ተመን ነው። በቂ መስዋዕትነት ለውጥን በመጠበቅ ከፍሏል። ግን መጓጓዣው ሲመጣ በዚህ ዓይነት ፍጥነት እንደሚፈተለክ የገመተ የለም፡፡ እኔም አልገመትኩም። ስላልገመትኩም አዲስ አይነት ህመም ታመምኩኝ፡፡ “Motion Sickness” ሊባል ይችላል። በሽተኛ ከህመም ወደ ፈውስ በሰርጅኑ የቀዶ ጥገና ማደንዘዣ ውስጥ ሆኖ የሚያሳልፈው ሁኔታ ‹ድብታ› ሊባል ይችላል፡፡

ግን ይሻላል፡፡ የሚሰራውን በሚያውቅና ቅን በሆነ ሀኪም እርዳታ እጅ ላይ ሆኖ መሞት ይሻላል። … መታመምን እንደ ጤንነት ቆጥሮ በሽታን ሲያወርሱና ሲያራቡ ኖሮ ረዘም ባለ የስቃይ ሂደት ከመሞት ይሻላል፡፡
ስለዚህ፤ ቅዳሜና እሁድ ቤቴ አሳልፌ ሰኞ ሲሆን ብቅ አልኩኝ፡፡ መገናኛ አደባባዩ ላይ ህዝብ ምን አይነት ስሜት ላይ እንዳለ ለመመልከት ሞከርኩኝ። መገናኛ አዲስ አበባ ውስጥ እንደምትገኝ ትዝ አለኝ። አዲስ አበባ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በፍጥነት ወደ ለውጥ እየተምዘገዘገ ባለው ጥይት ባቡር ውስጥ።  

ጥይት ሆኖ ማንንም ሳይገድል ሁሉንም ለማዳን በሚሞክሩ መሪዎች የተንቀሳቀሰው ባቡር ውስጥ ነን፡፡ ገና ተጨባጭ የሆነ ለውጥ የለም። መገናኛ ላይ የሚታየኝ ነገር በፊት የነበረው ነው። ቴሌቪዥን ላይ ያየሁት ጉዞ በአደባባዩ ዙሪያ ያለውንም የሚጨምር አይመስልም፡፡ 

ባቡር ውስጥ ሆኖም ሰዉ የረጋ፣ የማይንቀሳቀስ ምድር ላይ ያለ ይመስል የሚሸጥ ነገር ተሸክሞ ያዞራል። አንዱ ሌላው ኪስ ውስጥ ሁሉ ይገባል። ምድር የማትዞር ይመስል ናላ የሚያዞር ጩኸት ኮስሞቲክስ ከሚሸጡ ሰዎች በሞንታርቦ አካባቢውን ይበጠብጣሉ። … “ደም ለግሱ” እያሉ ልክ ሳንቲም እንደ መለገስ ቀላል በሚመስል ማግባቢያ አደባባይ ላይ ድንኳን ዘርግተው ሰው የሚያጠምዱ ወጣት ሴቶች ተሰማርተዋል፡፡  

በእግሩ መዶሻ ይዞ በመምታት ሰውን የሚያስደንቀው አናጢ ሰውዬም እንደዚህ ቀደሙ በተመልካችና አድናቂዎቹ ተከቦ የተለመደውን ተግባሩን እያከናወነ ነው፡፡ … የለውጡ ሂደት መገናኛ አደባባይ ላይ በተጨባጭ የሚታይ ደረጃ የሚደርሰው መቼ ነው? ብዬ ራሴን ከጠየቅሁ በኋላ በራሴ ቂልነት መልሼ ፈገግ አልኩኝ፡፡ መዳረሻው መቼም ህልም አይሆንም፡፡ የሆነ ተጨባጭ ነገር መታየት አለበት፡፡ 

“በውጫዊው ዓለም ላይ ሳይሆን በራሴ ህይወት ላይ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ማየት አለብኝ” ብዬ ሀሳቤን ከውጫዊው ዓለም ወደ ራሴ አዞርኩት። እኔ በስራዬ ፀሐፊ ነኝ፡፡ የተዘጉ ጋዜጦች ተከፍተው … ፅፌ መኖር ስችል ጉዞው ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል … ማለት እንደምችል አሰብኩ። ... ለእኔ ስራዬ ፀሐፊነት እንደሆነ ሁሉ ሌላውም ሰርቶ የሚኖርበት … የማይፈረጅበት … አላግባብ እንዲሸማቀቅም ሆነ በማያውቀው አሻጥር ሰለባ ሆኖ መስራትም ሆነ መኖር የማይችልበት ደረጃ ደርሶ በድጋሚ እንዳይወድቅ የሚከላከል ጊዜ ከመጣ የባቡሩ ተጓዦች መድረሻው ላይ ደርሰዋል። … በሰላምም ደርሰን ወርደናል ማለት ነው አልኩኝ፡፡ እያልኩ ለማሰብም ሞከርኩኝ፡፡ 

ግን ሀሳቤ እየተከሰተ ስላለውም ሆነ ክስተቱ ሲያልቅ ስለሚጠበቀው ውጤት ተጨባጭ ምስል ይስጠኝ ወይንም ያጭበርብረኝ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ 

ተስፋ አለኝ፡፡ ተስፋ አድሮብኛል፡፡ ጉዞው ጀምሯል። ፍጥነቱም ከተጠበቀው በላይ ነው፡፡ እነዚህ ነጥቦች ላይ ምንም ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ትዕግስት ማድረግና መጠበቅ ብቻ ነው የሚጠብቀኝ፡፡ ወይንስ ተልዕኮ ይጠብቀኛል። እንደ አንድ ተራ ተሳፋሪ ለጉዞው የማደርገው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ይኖር ይሆን?  

መልሼ መፃፍ የምጀምርበት … የተረጋጋ ዘመን ይመጣል፡፡ ስለሆነው … እየሆነ ስላለውና ወደፊት ስለሚሆነው በጥቅሉ ተመልክቼ በጥሞና የማስብበትና የምፅፍበት ዘመን ይመጣል፡፡ ተስፋ አብዝቻለሁ፡፡ ድሮ ጨለምተኛነት አበዛ እንደነበረው፡፡ ተስፋ ይሻላል። ሞትን የሙጥኝ ከማለት ህይወትንና መጪውን በተስፋ ማድረግ ይሻላል፡፡ እርግጥ ግራ ይገባኛል፤ የነገሮች በፍጥነት መለዋወጥ ባመጣው ጣጣ ግራ መጋባት፣ ያለ እና የሚጠበቅ ነው፡፡  

የጉዞ በሽታ ነው። ጉዞው ትክክለኛ ቦታ ላይ ደርሶ ሲረጋጋ በሽታው፣ ማቅለሽለሹ፣ ጥሞና ማጣቱ ይለወጣል፡፡ የባቡሩ ስም መደመር ነው፡፡ “ተደመሩ ወይ ተመርመሩ” ይላል - የባቡሩ ጉዞ ላይ የቆረጥነው ትኬት። ተመርምሮ በሽታን አውቆ መሳፈር ያዋጣል። አሁን በ“Motion Sickness” እና በተለዋዋጭ የእንቅስቃሴ ብዥታ ውስጥ በመሆኑ ምክኒያት ተሳፋሪው ግራ የሚያጋባ አቋም አልፎ አልፎ ቢያንፀባርቅም መጨረሻ ላይ ሁሉም ነገር የሚዳኘው ከውጤቱ አንፃር መሆኑ አይቀርም፡፡

No comments