Ethiopianism

ያዘንክ መስለህ ሌላ ሞት አትጥራ ! (አሌክስ አብርሃም)

ያዘንክ መስለህ ሌላ ሞት አትጥራ ! (አሌክስ አብርሃም)

ፌስ ቡክ ዛሬ ተዘቅዝቆ በተሰቀለ ሰው ፎቶና በካርቶን ታሽጎ በሚቃጠል ጫት ፎቶ ተሞልቷል ! ሁሉም በሚባል ሁኔታ <<ህግ የለም ፣ አገር በመንጋ ሰሜታዊ ፍርድ እየተመራች ነው እየተበታተንን ነው >> የሚል ኡአኡታውን እያቀለጠው ነው !!  


ይህ አዛኝ መሰሎ በዘር በሃይማኖት የሚነሱ ግጭቶችን ባንዴ ከተለያዩ ቦታዎች አሟሙቆ ማራገብ ውጤቱ ፍትህ ሳይሆን ሌላ ሞት መጥራት ነው ! በህዝቡ ስነልቦና ውሰጥ ፍትህ የለም፣ ዋሰትና የለም ፣የሚጠብቅህ የመንግስት አካል የለም የሚል በሽተኛ የመፍረስ ዝንባሌን በመዝራት እሰካሁን የተደከመበተን አብሮነት አልፎ አልፎ በሚከሰቱ የዚህ አይነት ሁነቶች ለመሸፈነ መሞከር ሌላ ሞት መጥራት ነው ! መፍረስን ሰው አእምሮ ውስጥ ከዘራህ ሁሉም የየራሱን እቃና ነብስ ማትረፍ ላይ እንጅ አንድ ላይ በአንድ ልብ ተሰብስቦ አገር መገንባትን አያስብም !

አብዝሃኛው የፌስቡክ ማህበረሰብም ለወሬ ምራቁን የሚውጥ ችግር የሚያነፈነፍ ወደቀ ሲሉት ተሰበረ የሚል የግለሰቦችን ድርጊት ታኮ ዘርን ሃይማኖትንና ህዝብን ለመዝለፍና ለማንቋሸሽ የሚቸኩል በግር በፈረስ ህዝብን ለእልቂት ቀሰቅሶ መልሶ እየየ የሚል ፣ ከሚመጣው ውጤት ይልቅ የሚሰበስበው ለምንም የማይጠቅም ላይክና ኮሜንት የሚያረካው መሆኑ የታወቀ ነው !  

(አሁን ያለው እውነታ ማንኛውንም ከውስጥም ይሁን ከውጭ የሚሰነዘር ጥቃት አለመረጋጋት እንዲሁም ህዝብ ሕይዎትም ላይ ሆነ ንብረት ላይ የሚደርስ ችግርን በበቂ ሁኔታ መቋቋም የሚችል አቅም ያለው የመከላከያ ሃይል አለን!!) የቱንም ያህል የመከላከል አቅም ቢኖረን ግን ህዝብ መሃል ዛሬም ነገም ምን ጊዜም ችገሮች ይኖራሉ !! በሃይል ብቻ ሳይሆን በሂደት ብቻ የሚፈቱ !!

ለማንኛውም አገራችን ላይ መዓት የወረደ አስመስለን አናስበው ፣ የሆነው ነገር ያሳዝናል ተገቢም አይደለም የፍትህ አካላት በተጠና መልኩ አስፈላጊውን ርምጃ መውሰድና የዚህ አይነቱን ችግር ማስቆም አለባቸው ! መንግስት ሰራውን ባግባቡ ያልሰራ ካልመሰለን በተደራጀና በሀጋዊ መንገድ ግፊት ማድረግ የወግ ነው !! 

በተረፈ እርስ በእርስ በገጀራ ስንጨፋጨፍ፣ ሰው በእሳት ስናቃጥል ፣በድንጋይ ጨፍጭፈን ሰንገድል፣ በጥይት ስንረሻሸን፣ ሌላም ተነገሮ የማያልቅ ብዙ አሰቃቂ ግፍ ሰንፈጽም የኖርን ህዝቦች ነን ! ግን አልፈረስንም ! ዛሬም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ይህ ክፉ አስተሳሰብ አንድና ሁለት አካባቢዎች ላይ ውጤቱ ሲታይ በቃ አገር አበቃላት ወደሚል ተሰፋ አስቆራጭ ሮሮ መሄድ እንዲሁ ሙሾ በማውረድ ላይክ የመለቃቀም አባዜ የፈጠረው በሽታ ነው !

አንተ ስለፍትህ የጮህክ አስመስለህ <<ይሄው ዘርህ ሲጨፈጨፍ>> እያልክ በፎቶና ቪዲዮ ጭምር ያቀበለከው ህዝብ ነገ በበቀል ጥቃት ሲፈጽም መልሰህ ወሬህን ከማድመቅ ውጭ ምን ትፈይድለታለህ ? እውነቱን ለመናገር በማይረባ ወሬኝነታችን የአጥፊዎችን የቤት ሰራ እያቃለልንላቸው ነው !  

እኛ ጭካኔውን በፎቶ ቃል እያሳመርን እንለፈለፋለን ህዝብ ይቆጣል ያዝናል ከዛስ? በቃ አጥፊዎቻችን ዘና ብለው አንድ አረፍተ ነገር መወረወር ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው <<ሰሞኑን በፌስቡክ ያያችሁትና መላውን አገር ያስቆጣው አሰቃቂ ግድያ የተፈጸመበት የእከሌ ብሔር ተወላጅ ወይም የምንትስ ሃይማኖት ተከታይ ነው>> ይሉሃል አንተ እና እኔ ከሽነን በሰራንላቸው የእልቂት ወጥ ላይ የፍጅት ቅመም ነስንሰው ለራሳችን ህዝብ ያቀርቡልናል !!

No comments