Ethiopianism

የውሃ መጠኑ የሞላው የተከዜ የሀይል ማመንጫ ግድብ ከነገ በስቲያ ጀምሮ ውሃ የሚለቅ በመሆኑ ህብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ ተገለፀ

በግድቡ በላይኛውና በታችኛው ክፍል የሚገኙ የትግራይና አማራ ክልላዊ አስተደሮች ልዩ ትኩረት እንዲያደርጉ ነው ያሳሰበው


የተከዜ የሀይል ማመንጫ

የተከዜ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የውሃ መጠን በመሙላቱ ለግድቡ ደህንነት ሲባል የውሃ መጠኑ ከነሃሴ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ስለሚቀነስ በአካባቢው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በደራሽ ውሃ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አሳሰበ።

ተቋሙ ለፋና ብርድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቀው፥ በግድቡ በላይኛውና በታችኛው ክፍል የሚገኙ የትግራይና አማራ ክልላዊ አስተደሮች ልዩ ትኩረት እንዲያደርጉ ነው ያሳሰበው።

በዚህም በትግራይ ክልል በጣንቋ አበርገሌ፣ በቆላ ተንቤን፣ በላዕላይ ማይጨው፣ በታህታይ ማይጨው፣ በመረብ ለሄ በተመሳሳይ በሰሜን በምዕራባዊ ዞን በአሰገደ ጺምበላ፣ በላዕላይ አዲያቦ፣ በመደባይ ዛና፣ በታህታይ አዲያቦ፣ በታህታይ ኾራሮ፣ በፀለምቲ እንዲሁም በምዕራባዊ ዞን በካፍታ ሁመራ፣ በፀገዴ እና በወልቃይት አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተቋሙ አስታውቋል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል በዋግኽምራ ዞን ስር በአበርገሌ ወረዳ፣ በሰሜን ጎንደር ዞን በጠለምት ወረዳ በአጠቃላይ የተከዜ ወንዝ አዋሳኝ ቀበሌዎች እና በአካባቢው ነዋሪው ከወዲሁ ይህንኑ በመገንዘብ በሰውም ሆነ በእንሰሳት ላይ የሚለቀቀው ደራሽ ውሃ ጉዳት እንዳይደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል።

No comments