Ethiopianism

የነሀሴ16፣ 2ዐ1ዐ የተመረጡና አጫጭር ወሬዎች

የነሀሴ16፣ 2ዐ1ዐ የተመረጡና አጫጭር ወሬዎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በክፍለ ከተማ ደረጃ ያሉ ዋና ዋና አመራሮች እንደአዲስ ሊያደራጅ መሆኑን አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በዚህ ሳምንት በክፍለ ከተማ ደረጃ ያሉ ዋና ዋና አመራሮች በአዲስ መልክ ይዋቀራሉ ብለዋል።

በከተማ ደረጃ የተጀመረው የማሻሻያ ስራ እስከ ወረዳ እንደሚዘልቅ በተገለጸው መሰረት ከአዲስ አመት በፊት በወረዳ ደረጃ ያለው አመራር በአዲስ አደረጃጀት ተዋቅሮ እንደሚጠናቀቅም ገልፀዋል።

የተጀመረውን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ እና አሁን እየታየ ያለውን ሀገራዊ ተስፋ ለማደናቀፍ እንዲሁም የከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ እየታዩ ያሉ ምልክቶችን ህብረተሰቡ ከአስተዳደሩ ጎን በመቆም ድርጊቱን እንዲከላከልም ምክትል ከንቲባዋ ጠይቀዋል።

ሰሞኑን በርካታ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ሲዘዋወር በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋሉን ያስታውሱት ወ/ሮ ዳግማዊት፣ በቀጣይም ነዋሪው የሚያያቸውን አጠራጣሪ ነገሮች ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል።

ቤታቸውን የሚያከራዩ ነዋሪዎች የተከራዮችን ማንነት ሊያጣሩ እና ተገቢውን መረጃ ሊይዙ ይገባል ብለዋል።

ምንጭ፡የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት


ኢትዮ ቴሌኮም በድምፅ፣ በኢንተርኔትና በአጭር የፅሁፍ አገልግሎት ዘርፎቹ ላይ የታሪፍ ቅናሽ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ በቅናሽ ማሻሻያው መሰረት የስልክ ድምፅ ጥሪ 40 በመቶ ቅናሽ ተደርጎበታል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ባደረገው ማሻሻያ መሰረት የስልክ ኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የ43 ከመቶ ፣የብሮድባንድ ኢንተርኔት ላይ ደግሞ የ54 ከመቶ የአገልግሎት ቅናሽ ተደርጎበታል፡፡

የሞባይል አጭር የፅሁፍ መልዕክት (SMS) ደግሞ የ43 ከመቶ ቅናሽ እንደተደረገበት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግርዋል ፡፡

የታሪፍ ቅናሽ ማሻሻያው ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡



የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ደቡብ አፍሪካን ሊጎበኙ ነው፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኤስ .ኤ.ቢ.ሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደናገሩት ዶ/ር ዐቢይ ከቀጠናው ሀገራት ውጭ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት የመጀመሪያው በደቡብ አፍሪካ እንዲሆን ፍላጎት አላቸው፡፡

በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥ እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኃይለማርያም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተላከ መልዕክት ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሰርል ራማ ፖሳ አድርሰዋል፡፡

በፀረ አፓርታይድም ይሁን በነጻነት ትግል ወቅት ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ወንድሞቿ አለኝታ ነበረች ያሉት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ለአፍሪካ መልካም ትሩፋት እንዳለውም ገልፀዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚዲያውን ምህዳር ለማስፋት የሚያስችል ማዕቀፍ ለህዝብ ውይይት ቀረበ

በሀገሪቱ ያለውን የኮሙኒኬሽንና የሚዲያውን ዘርፍ ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የብሮድካስትና የሚዲያ ህግን ብሎም ፖሊሲን ለማሻሻል የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተካሄዷል፡፡
በጥናቱ በዋናነት ከሚዲያ ነፃነትና ምህዳር መስፋት፣ ከሚዲያ ተቋማት ፍቃድ አሰጣጥና በፌዴራል እንዲሁም በክልል የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ጋር የተያያዙ ችግሮች በጥናቱ ተዳሰዋል፡፡

በተለይ የጋዜጠኞች ማህበራት፣የባለሙያዎችንና የሚዲያ ተቋማትን አቅም ማጠናክር እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል፡፡

በውይይቱ የተገኙት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚንስትር አቶ አህመድ ሺዴ ሚዲያው በሀገሪቱ ልማትና ዲሞክራሲ ግንባታ የተሻለ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የዘርፉን ምህዳር ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በሀገሪቱ ያለውን የኮሙኒኬሽንና የሚዲያውን ዘርፍ ለማሻሻል ያለመ ማዕቀፍ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘርፉ የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የተሻለ ጥበቃ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ ከየትኛውም አካል ነፃ ወይም ገለልተኛ የሆነ ሚዲያ ሊፈጠር እንደሚገባ በመድረኩ ላይ ተመልክቷል፡፡

ሪፖርተር፦አልዓዛር ተረፈ

No comments