Ethiopianism

የጅግጅጋ ተፈናቃዮች በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ ወድቀዋል - ቢቢሲ

የጅግጅጋ ተፈናቃዮች በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ ወድቀዋል

ከሁለት ሳምንታት በፊት በሶማሌ ክልል በተከሰተው ግጭት ጥቃት የደረሰባቸው ስደተኞች በአዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ ኦሮሚያ የባህል ማዕከል ፊት ለፊት ተጠልለዋል።

እስከመቶ የሚደርሱት እነዚህ ስደተኞች በዚሁ ጎዳና ላይ በሸራ በተከለለችው ስፍራ ከማረፍ ውጪ ምንም አይነት አማራጭ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከስድስት ወር ህጻን ጀምሮ ሴቶች፤ አዛውንቶችና በጥቃቱ ድብደባ የደረሰባቸው ደካሞች ለአራት ቀናት በዚሁ ቦታ ላይ እየዋሉም እያደሩም ነው።

ቤት ንብረታቸውም ሙሉ በሙሉ በጥቃቱ በመውደሙ የሚለበስም ሆነ እንዲህ ላሉ ክፉ ቀን የሚሆን ጥሪት አለመቋጠራቸውን ተናግረዋል።


እስካሁን የዕለት ጉርሳቸውንም እዛው አካባቢው ያሉ ወጣቶች ከመንገደኞች እየሰበሰቡ ከሚያቀርቡላቸው ምግብ እያገኙ ቢሆንም ከዚህ ውጭ ምንም አይነት የመንግስት ድጋፍ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በዓመቱ መጀመሪያ በተመሳሳይ ጥቃት ሙሉ ቤተሰቡን እንዳጣ የሚናገረው አደም አህመድ በጅጅጋ 03 በሚባለው አካባቢ ነበር ኑሮውን ያደረገው።

አሁን ሁኔታዎች ተቀይረው ሥምምነት ተፈጥሯል መባሉን ተከትሎ ወደጅግጅጋ ከተመለሰ ሰባት ወሩ ነው።

"ባለፈው መስከረም ግርግሩ ሲፈጠር ሱቅ ውስጥ ነበርኩኝ፤ በበር በኩል ሲገቡብኝ በመስኮት ዘልዬ መኖሪያ ቤቴ ስሮጥ ሁለት ልጆቼ ፣ ሶስት እህቶቼና እናቴ ተገድለው ነበር ያገኋቸው፤ ተመልሼ ስሄድም ይኸው ግርግሩ ተፈጥሮ አሁንም ውጡልን ተባልን ፤ ወዲዚሁ መጣሁ፤ ግን ቤተሰቦቼ በሙሉ እንዳለቁ ስነግራቸው አንድም የተረዳኝ ሰው የለም።" ይላል።

"እሰከዛሬ ድረስ ወደዛም ወደዚህም ስንል፣እኛ ጎዳና ተዳዳሪ ስንሆን አንድ ቀን መጥቶ አይዟችሁ እኛ አለን ያለን ሚዲያም የለም ህዝብ ነው እየተባበረን እሰከዛሬ እንድቆይ ያደረገን እንጂ የመንግስት አካል ሁሉ ወደእዚያው ተመለሱ እያሉን ነው፤ እኛ ለምንድነው እንደዚህ የምንሆነው ኢትዮጵያዊ አይደለንም አንዴ?"

ቢቢሲና እንድ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንም ተፈናቃዯችን ለማናገር ሲሞክሩ በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አባላት እንዳይቀርጹ በመከልከላቸው ተፈናቃዮቹ ከፖሊሶቹ ጋር የቃላት እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው ነበር።

ከቆይታ በኋላ ግን የጋዜጠኞቹን መታወቂያዎችን አረጋግጠው ክልከላውን አንስተዋል።

በጅግጅጋ ከመርሲን አካባቢ የመጣችው በቀሉ ቶሎሳ በጥቃቱ ከ 80ሺ ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት እንደተዘረፈባት ተናግራለች።

"ይኸው አስራ አምስት ቀናችን ምንም መፍትሄ አላገኘንም፤ የወደቅነው ጎዳና ላይ ነው። አሁን እዚህ ተኝተን ደካማ አሉ፤ ልጆች የያዙ እናቶች አሉ ፤በሽተኞች አሉ፤ ምንም መፍትሄ አላገኘንም። " ብላለች

በቀሉ ጉዳያቸውን አቤት ለማለት ወደተለያዩ የመንግስት አካላት ቢሮ ቢቀርቡም ሰሚ ጆሮ እንዳላገኙ ነው የምትናገረው።

"ወደ አስራ ምናምን ቦታ ጠየቅን፤ ያልገባንበትቢሮ የለም ፤ መፍትሔ አላገኘንም ይኸው ጎዳና ላይ ወደቅን፤ እሰከዛሬ እኔ የመንግስት ያለህ እያልኩኝ ነው። "

በዕለቱ ጥቃት የተሰነዘረባቸው አይነስውሩ ባህታዊ ታምሩ ዘለቀም ከጉዳታቸው ሳያገግሙ በዚሁ ጎዳና ላይ ተመጽዋች ሆነዋል።

" ኪዳነምህረት አስቀድሼ ወደሚካኤል ስመጣ ነዋይ ቅድሳት እየተቃጠለ ነበር፤ ተመልሼ ወደኪዳነምህረት ስንሄድ ለካ ኪዳነምህረትንም አቃጥለው ጨርሰዋታል ፤ ተመልሰን ወደ ሚካዔል ስንመጣ ጥርሴን አረገፉኝ፤ ወገቤንም መቱኝ"

ለዚህ ህመማቸው በቂ የህክምና አግልግሎትት ባያገኙም ከአስተባባሪ ወጣቶች ባገኙት መድኃኒቶች ህመማቸውን ያስታግሳሉ።

ከተፈናቃዮቹ ውስጥ 30 የሚሆኑት ከሁለት ቀናት በፊት ነበር ነፍሳችውን ለማዳን ከመሸጉባት ሃረር ወደ አዲስ አበባ የመጡት።


ለአምስት ቀን የሃረር ህዝብ እየረዳን ቆየን፤ ልጆች አሉ፤ ደካማ አለ፤ አይነስውራን፤ የተደበደበ፤ በጥይት የተመታ ሁሉ ነበረ፤ እኛ እንዴት ነው የምንሆነው ? እንዳንመለስ ንብረታችን ተዘርፏል፤የመመለስም ህልውና የለንም ስንላቸው ወደ አዲስ አበባ ሂዱ ፤ መንግስትም ይረዳችኋል ሲሉን መጣን፤ ከእነዚህ ግማሹ ሴቶች ናቸው" ብሏል የተፈናቃዮችን ስም ሲመዘግብ ቢቢሲ ያገኘው ሞላ የተባለው ተፈናቃይ።

" የሌሊቱ ብርድ ራሱ እኔ ከዱላው በላይ አድርጌ ነው የማየው፤ በጣም ነው የሚሰቃዩት፤ የሚለብሰው አጥቶ በብርድ የሚሰቃይ ሞልቷል።"

ስታዲየም አካባቢ የሚሰራው ጋሻው ተወዳጅ ተፈናቃዮቹን ለመርዳት ከተሰባሰቡት ወጣቶች አንዱ ነው።

ካለፈው አርብ ጀምሮ ጎዳናው ላይ የወደቁትን ተፈናቃዮች የማገዙ ሂደት አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ይገልጻል።

"እኛ ብቻ ነን አሁን እየረዳናቸው ያለነው ፤ መንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እስካሁን የረዳቸው የለም፤ ህጻናት አሉ ፤የሚያጠቡ እናቶች አሉ፤ ሽማግሌዎችም አሉ፤ ብርድ ላይ ነው ያሉት ትንሽ ቢቀንሰውብለን ሸራ ገዝተን አጠርንላቸው።ምግብ አንዳንድ ሰው ይዞ ይመጣል፤ ካልሆነ ደግሞ አስተባብረን በምናገኘው ገንዘብ ምግብ ቤት ሄደን ገዝተን ነው የምናበላቸው፤ ጠዋት ጠዋት ደግሞ በየቦታው የሚያፈሉትን እያፈላለግን በፔርሙሶች እየሰበሰብን በቁርስ እናበላቸዋለን" ብሏል።

ወጣቶቹ መንግሥትም ሆነ ድርጅቶች ተፈናቃዮቹን በመጎብኘት ለጊዜው ምግብና መኝታ የሚያገኙበትን መንገድ እንድሚያመቻቹ ጠይቀዋል።

ተመልሶ ወደጅግጅጋ መሄዱ የዘላቂ መፍትሄው አካል እንደሆነ የተጠየቀችው በቀሉ ይህን ብላለች።

"መመለስ አለልፈልግም፤ መንግሥት እዚህ ቢገድለኝ ሁሉ ይሻለኛል፤ በቃ እዚሁ ብሞት እመርጣለሁ፤ የዛሬ ዓመትም ሁለት ዓመትም እንደዚሁ ስለሆነ ወደዚያ የሚያስብ ቤተሰብ የለም"

አስተባባሪ ወጣቶችም ችግሩ ከአቅማቸው በላይ እየሆነ በመምጣቱ መንግስትም ሆነ ለጋሾች እጃቸውን እንዲዘረጉላቸው ጠይቀዋል።

No comments