Ethiopianism

የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን የ80.1 ሚሊዮን ብር ክስ ቀረበበት - ታምሩ ጽጌ

የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን

በአማራ ክልል በጎንደር አካባቢ በሚገኘው የመገጭ ወንዝ ግድብ ውኃ መቆጣጠሪያ ማማ የመሠረት ምሰሶ ጉድጓድ ቁፋሮ ግንባታ ለማሠራት፣ ከተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የፈጸመውን ውል ያቋረጠው፣ የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የ80.1 ሚሊዮን ብር የፍትሐ ብሔር ክስ ተመሠረተበት፡፡

ክሱን የመሠረተው ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ሲሆን፣ ያለበቂ ምክንያት ከኮንትራት ውሉና ከሕጉ ውጪ የሥራ ውሉን ድርጅቱ ማቋረጡን በመጥቀስ ነው፡፡ ክሱ እንደሚያስረዳው ሁለቱ ተቋማት ጥር 10 ቀን 2008 ዓ.ም. የግንባታ ሥራ ውል ተፈራርመዋል፡፡ 


የተስማሙበት የግንባታ ዋጋ 57,500,920 ብር ነበር፡፡ በውላቸው መሠረት ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ሲገጥምና ሥራ መሥራት ካልተቻለ፣ ሊቋረጥ እንደሚችል በውላቸው ላይ ሠፍሯል፡፡ በመሆኑም ሕዝባዊ አመፅ በመከሰቱና ለ79 ቀናት የቆየ በመሆኑ፣ መንግሥት ኅዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ በክሱ ተገልጿል፡፡

በውላቸው መሠረት ኮንትራክተሩ ውሉን ለማቋረጥ በቂ ምክንያት ያለው ቢሆንም፣ አንድ አገራዊ ኃላፊነት እንደሚሰማው ሥራ ተቋራጭ የግንባታ ውሉን ሳያቋርጥ መቆየቱን በክሱ ጠቅሷል፡፡ ኮንትራክተሩ በሚሠራበት ሳይት (የሥራ ቦታ) አካባቢ አመፁ ከፍተኛ ሽፋን የነበረው ለመሆኑም፣ አማካሪ መሐንዲሱ ሥራው ከአራት እስከ አምስት ወራት መቋረጡን ለውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት በደብዳቤም እንዳሳወቀው አክሏል፡፡ 

ይኼ የሚያሳየውም ለኮንትራክተሩ ተጨማሪ የግንባታ ማራዘሚያ ጊዜ የሚያስፈልገው መሆኑን እንደሆነ ኮንትራክተሩ ጠቁሞ፣ ከሕግና ከውል የመነጨ ምክንያታዊ ማብራሪያ ገልጾ፣ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠውም መጠየቁን አክሏል፡፡

ነገር ግን ድርጅቱ ደብዳቤ በደረሰው በ21 ቀናት ውስጥ ምላሽ መስጠት ቢገባውም ባለመስጠቱ፣ የግንባታ ሥራ ማስረከቢያ ጊዜውን በውል ለይቶ እንዳይወስን እንዳደረገውም በክሱ ጠቅሷል፡፡ 

ኮንትራክተሩ በመጀመርያው የውል ጊዜ ማስረክብ የማይችል መሆኑ ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት የታወቀ መሆኑን ጠቁሞ፣ በአዕምሮ ግምት በቂ የማስረከቢያ ጊዜ ከሚሰጠው በስተቀር በውሉ ላይ የተመለከተው የማስረከቢያ ጊዜ ከሕግና የውል ምክንያታዊነት አንፃር ተፈጻሚነት ስለማይኖረው፣ ለግንባታ ሥራው መዘግየትና ውሉ በአግባቡ ላለመፈጸሙ፣ ተጠያቂነትም ሆነ ኃላፊነት እንደሌለበት ማሳወቁንም ገልጿል፡፡

ከአቅምና ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ምክንያት ሥራው መስተጓጉሉ እየታወቀ፣ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ከ60 ቀናት ያላነሰ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ውሉን ማቋረጥ እንደሚገባው በውሉ ላይ ተቀምጦ ሳለ፣ ያንን በማለፍ ነሐሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ውሉን ማቋረጡን በክሱ ገልጿል፡፡ 

ውሉን ማቋረጡ ሳያንሰው በአጠቃላይ መቆፈር ከሚገባቸው 64 ጉድጓዶች ውስጥ 21 ጉድጓዶችን መቆፈሩን የሚያረጋግጥ ማረጋገጫ የተሰጠበትን 1,294,460 ብር መክፈል ሲገባው አለመክፈሉንም ጠቁሟል፡፡

በአጠቃላይ ድርጅቱ ክፍያ ከማስቀረቱም በተጨማሪ፣ የኮንስትራክተሩን የግንባታ ማሽኖች አግቶ በመያዝ፣ በወቅታዊ ዋጋ ቢከራዩ እንኳን ማግኘት የነበረበትን 59,136,000 ብር እንዲያጣ ማድረጉንም ገልጿል፡፡  

በአጠቃላይ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ከውል ውጪ በፈጸመው ሕግ ጥሰት ሕጋዊ ወለድ ዘጠኝ በመቶ ተጨምሮ 80,181,307 ብር ክፍያ እንዲፈጽምለት ኩባንያው ክስ አቅርቧል፡፡

No comments