Ethiopianism

በሃገራችን እውነተኛ ፖለቲካ መድረክ ለዓመታት የኮመኮምነው ትያትር መጋረጃ ሊዘጋ ይሆን ወይስ ?

በሃገራችን እውነተኛ ፖለቲካ መድረክ ለዓመታት  የኮመኮምነው ትያትር መጋረጃ ሊዘጋ ይሆን ወይስ ?


የሃገራችን ፖለቲካ ጉደኛ ነበር፡፡ ያለፈውን ግማሽ ክፍለ ዘመን ወደ ኋላ ተመልሶ ማስታወስ አጃይብ የሚያስብል ቢሆንም ዛሬም ቢሆን አጠቃላዩን ጉድ፣ ጥቂት የችግሩን ቁንጮወች በደቦ እንጅ ጉደኞችን በአጠቃላይ፣ በዝርዝር ከችግሮቻቸው ጋር መለየት አይቻልም፡፡ 


ይህ እውነታ ከነበረው ለመማር፣ ዛሬንና ቀጣዩን በትክክል ለማስተካከልና ለማረም ዕንቅፋት ሲሆን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በፖለቲከኞቻችንና መሪወቻችን መካከል ከነበሩት ልዩነቶች ይልቅ እጅግ በጣም የሚበዙ የጋራ ችግሮች ባለቤት ስለነበሩ ነው፡፡

የጋራ የሆኑትና በተለያየ መልክ የሚገለጡት ችግሮች ልዩነቶቻቸውን እያደበዘዙት፣ በእረጅም እርቀትና በልዩነት የብዙሃኑ አሸናፊ የሆኑ መሪወችን አልታዘብንም፡፡ መንግስትም ይሁኑ መሪ ተቃዋሚም ይሁኑ የነፃነት ተሟጋችና የለውጥ አቀንቃኞች እንደ ሃይሌና ፖልቴርጋት አንገተ ለአንገት ተናንቀው ቀጠሉ እንጅ እንደ ጥሩ ነሽና ቀነኒሳ የመጨረሻ ዙር አጨራረስ፣ በልዩነት አፈትልከው ካሜራው ብቻቸውን እንደሚቀርፃቸው ብርቅዮ ጀግኖች ተፎካካሪወቻቸውን አልደረቡም፣ ካሜራ የሆነውን ሰፊ ህዝብን ትኩረት ለዘለቄታው ይዘው መቀጠል አልቻሉም ነበር፡፡

በሃገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካ መድረክም ይሁን በእያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ተመሳሳይ ነበር፡፡ መጀመርያ ድርጅት ህብረት፣ ትግል ከዚያ በኋላ ህብረቱ ፋይዳ ቢስ ድርጅቶች የአንጃ፣ የቡድን የሰርጎ ገብ ሰለባ ይሆናሉ፡፡ በነገሩ ብዙሃኑ ህዝብ አንገቱን ደፍቷል፤ መሪወቹ ችግርን መሸፋፈን ማስታመም ስለሚመርጡ ግልፅ ልዩነቶችን ተረድቶ የተሻለውን ይዞ የሚጥለውን ለመጣል አልቻለም፡፡ 

ስለዚህ ምን በጫካ አብረው ለመሰዋት ቢታገሉ፣ ድርጅት ቢያቋቁሙ፣ ቢምሉ፣ ቢገዘቱ በፖለቲካ መድረካችን ብዥታ፣ ሰበብ ፣ጥር ጣሬ መወነጃጀል ፣ መፈራረጅ፣ በተቻለው መንገድ ተቀናቃኝን ማስወገድ ብርቅ አልነበሩም፡፡ በሁሉም ማለት ይቻላል፡፡

ከዚህም በላይ ሴራና ተንኮል አብይ የማሸነፊያ ዘዴወች ነበሩ፡፡ እንኳን በሃገራችን እውነታ የትም ቢሆን በመላ ምት (ይሆናል) ካልሆነ ሴራንና ሴረኞችን በትክክል በማስረጃ መግለፅ ከባድ ነው፤ መላ ምት ስህተት የመሆን ዕድል አለው፤ ግን ስህተትም ቢሆን ትክክል ከሁለቱም መማር፣ ከሴራው ከፍ የሚለውን ሴራ ለመረዳት፣ ዝቅ የሚሉ አሻጥሮችንና ሸፍጦችን ለመገንዘብ ይረዳል፡፡
 

ስለዚህ የፖለቲካውን መድረክ ፈርጥ ፣ ባለ ብዙ ስሙን አቶ ልደቱ አያሌውን ከሃገራችን የሴራ ፖለቲካ ጋር በመመልከት የመላ ምት (ይሆናል) ግብዣ በዚህ ፅሁፍ አቀርባለሁ፡፡ አቶ ልደቱ የኢትዮጵያው ማንዴላ ነበሩ፤ አቶ ክህደቱ ወይም የተንሸራታቹ ሞባይል ቀፎ መጠርያ ስም ልደቱ ነበር፤ ዛሬ ከእጃቸው ሲወጣ ይመስላል ኢዴፓ ፈርሷል፣ ከእንግዲህ ፖለቲካ በቃኝ ቢሉም በሁለቱም ሁኔታወች ውስጥ እስከ ዛሬ በምርጫ ቦርድ የተመዘገበ የሚመሩት የህዝብ (የግለሰብ ፓርቲ ስለለ) ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ነበራቸው፡፡

ግለሰቡ ከመንግስትም ይሁን ከሌሎች ተቃዋሚወች የተለየ ባህሪ፣ ስልትና፣ ችሎታ ነበራቸው፤ ከዚህ ጋር ዲታ ሃብታምም ናቸው፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ በአደባባይና በሚዲያ ስለ አቶ ልደቱ የሰማሁትን ከሌሎች ግለሰቦችና ፖለቲከኞች ጋር በማነፃፀር፣ የግለሰቡን የሃያ ሰባት አመታቱን የፖለቲካ ተሳትፎ፣ መጨረሻቸውን እና የነበረውን ስርዓት አጠቃላይ ባህሪ በመዳሰስ አንባቢው የእራሱን መላ እንዲመታ በመጋበዝ አንባቢም ይሁን አቶ ልደቱ ግለሰቡን ለማንሳት የተገደድኩት ፖለቲካችንን ለማጠየቅ ብቻ እንደሆነ ይረዱኛል የሚል ግምት አለኝ፡፡

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት መንግስት እውነተኛ ተፎካካሪና ተቃዋሚን አይፈልግም ነበር፤ በተለይ ወጣት፣ ተዋቂ (ስመ-ጥር) ፣ የተወሰነ ሃብትና የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው የሃገሪቱ ዜጎች ተቃዋሚወች ብቻ ሳይሆን ሂስ ካደረጉትና ከተቹት ትዕግስት የሚባል አልነበረውም፡፡ ቴዲ አፍሮን፣ ፋሲል ደመወዝን የተለያዩ ባለሃብቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ከነዚህ የተለዩት ልደቱ አያሌው ብቻ ይመስሉኛል፡፡

ፖለቲከኞቻችን ከሃገር ውጭ ባፈሩት ሃብት፣ በጡረታና በመንግስት ስራ ኑሯቸውን የሚገፉ፣ ስራቸው የሚስተጓጎልባቸው፣ ከስራ የሚታገዱ፣ የሚዋከቡ፤ ገለልተኞች ደግሞ የሚፈረጁና የሚጠቁ ቢሆንም ከ 1983 ዓ.ም በኋላ አዲስ አበባ የገቡት ወጣት በ1997 ዓ.ም ከአስር ሚሊዮኖች በላይ ባለቤት መሆናቸውን፣ በአስመጭነት ስራ ሃብት እንዳፈሩ ሰምተናል፤ ማን አስመጭ እንደሚሆን መገመት አይከብድም ፡፡
 

አረሱት ብሎ የዘፈነው ፋሲል ደመወዝ አማራ ክልል ጎንደር ንፋስ መውጫ ላይ የተሰጠው ቦታ ታጥሮ ተቀምጧል፣ ቦታውን የሰጡት የንፋስ መውጫ ከተማ ሹማምንት ተገምግመው ተባረዋል፤ በተመሳሳይ ወቅት አቶ ልደቱ ግን ላሊበላ ላይ ዘመናዊ ሎጅ ለመገንባት ቦታ አግኝተዋል፤ በብዙ ሚሊዮኖች ወጭ ሎጁን በመገንባት ላይ ናቸው፡፡

በፖለቲካ ህይወታቸው አቶ ልደቱ በ1983 ዓ.ም በለውጡ ማግስት ወደ መዲናዋ የገቡ፣ መአህድ የተባለውን የተቃዋሚ ድርጅት ተቀላቅለው የወጣቶች ክንፍ አለቃ የነበሩ፣ ከዚሁ ድርጅት አንጃ ይዘው ኢዴፓ የተሰኘውን ፓርተ የመሰረቱ፣ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ቅንጅትን የመሰረቱ፣ በምርጫው ዋዜማ ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሰሩ ድንገት በተፈጠረው የለውጥ ፍላጎት በማንዴላ ስም የተሞካሹ ነበሩ፡፡
 

ከምርጫው በኋላ የድርጅታቸውን የኢዴፓን ህልውና በጓዶቻቸው ድጋፍ ሳይሆን በእጃቸው በነበረው ማህተም ብቻ ያስጠበቁ፣ የቅንጅትን ውህደት ደግሞ ያሰናከሉ ነበሩ፡፡ ክህደቱ የሚለውን ስምና የፓርቲ ሰርተፍኬት ይዘው እስከ ወቅታዊው የህዝብ እንቅስቃሴ ጠፍተው የቆዩት አቶ ልደቱ እንደገና ብቅ ለማለት ችለዋል፡፡ በሚፈለገው መንገድ ኢህአዴግን ተችቶ፣ የህዝብን ብሶት ለመቀነስ ብቸኛና አስፈላጊ ሁነው ስለታሰቡ ይመስላል አቶ ልደቱ ስርዓቱ የደገሳቸው የውይይት መድረኮች ዋና ተዋናይ ነበሩ፡፡

በቅንጀት አብረዋቸው የታገሉ ጓዶችን “ፓርላማ አንገባም፣ የምርጫውን ውጤት አንቀበልም የሚሉ ሽማግሌወችና እስከ 2002 ምርጫ የመቆየት ዕድል ስለለላቸው ነው፣ እኛ አየታሰርን እየተፈታን እዚህ ባደረስነው ትግል ትላንት መጥተው ገነኑበት፣” ብለው ባደባባይ የቅንጅትን ውህደት ያልተቀበሉት ፖለቲከኛ በቅርቡ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ “አብሮን መስራት የሚፈልግ የፖለቲካ ድርጅት ቢኖር ኢዴፓ ህልውናውን ሁሉ መስዋት ለማድረግ ዝግጁ ነው፤” ብለው ነበር፤ ምርጫ 97ንና ቅንጅትን ረስተው ማለት ነው፡፡ 

እንደገና ይህንን ረስተው ሰሞኑን ኢዴፓ ፈርሷል ሲሉ ደግሞ አንድ ዓመት አልፈጀባቸውም፡፡ የሚፈለገው ትልቅ ሁኖ የሚዘጋጅና ወደ ፊት የሚፈርስ ህብረት፣ ምንም ቢሆን ቀጣይ አንጃ፣ መፈራራስ ብቻ እንደ ግብ ካልተያዘ እንዴት የማይፈለገውንና አሳፋሪውን ትላንት ለመድገም ዛሬም ሞራሉና ፍላጎቱ ሊኖር ይችላል፤ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡

አቶ ልደቱ ንግግራቸውና ፖለቲካቸው የተመጠነ ፣ በጥላቻ ስሜታቸው ምክንያት ለመናገር፣ሃሳባቸውን ለማስረዳት እንደሚተናነቃቸው፣ የመንግስትም ይሁን የተቃዋሚ ድርጅቶች ፖለቲከኞቻችን ቃላትን ለመደርደር የማይቸገሩ ናቸው፡፡ ፖለቲከኛው ሁል ጊዜ በቅፅበት በመሃል ቦታ አያጡም፤ ቢኖርም ባይኖርም፡፡ 

አቶ ልደቱ ሲፈልጉ ሃይል፣ ጉልበትና ጥቅም የጠረነፈውን ኢህአዴግ አብሮ በመስራት የተሻለ ድርጅት ነው የሚሉ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ ሲፈለግ ጥላ ሸት ለመቃባትም ይችሉበታል፡፡ ሲፈለግ በኢኮኖሚና በፖለቲካ መካከል አጥር ያለ አስመስለው፣ ኢህአዴግ በቁሳዊ መሰረተ ልማትና በኢኮኖሚ ውጤት ቢያስመዘግብም ሰውና ፖለቲካው ላይ አልሰራም ይላሉ አቶ ልደቱ፤ በብቃት የተባ አንደበትና የተመረጡ ቃላትን ይጠቀማሉ፡፡

አቶ ልደቱ ትንፍሽ ባይሉም አቶ በረከት ግን ልደቱን ደሴ ላይ በ 1983 ዓ.ም እንደሚያውቋቸው ደጋግመው ያስታውሳሉ፤ ኢህአዴግ ሃገሪቱን ተቆጣጥሮ ህዝብ ሰብስቦ ሲያወያይ በወቅቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው በከተማዋ የሚኖሩት ወጣት ጥያቄ መጠየቃቸውን ይጨምራሉ፡፡ 

የአንድ ቀን፣ የሰዓታት ውይይት፣ አንድ ወይም ሁለት መሪ አወያዮችና ተሰብሳቢ ህዝብንና ጠያቂወችን መያዝ ጥሩ ነው፡፡ ከብዙወች አንዱ የነበሩት አቶ ልደቱ አቶ በረከትን ቢያስታውሷቸው ተገቢ ነበር፤ አቶ ልደቱ ግን ስለዚህ ተንፍሰው አያውቁም፡፡ አቶ በረከት ደግሞ በመፅሃፋቸው ላይ፣ በምርጫ ዘጠና ሰባት ዶ.ር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ ሶስቱ ስለምርጫ ቅስቀሳ ለመነጋገር ሲገናኙ የሁለቱን የመጀመርያ ትውውቅ ደጋግመው ያነሱታል፡፡ እንዴትና ለምን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ሲሆን አቶ በረከት እያመለጣቸው ይመስላል፡፡

ሁኔታው በእውነተኛው የፖለቲካ መድረክ ላይ ለሃያ ሰባት ዓመት የተተወነ ተከታታይ ትያትርም ይሁን የግለሰብና የቡድን ጭፍን የስልጣን ጥም የሚገፋው እውነታ የፖለቲካ መድረካችን ክስተት ነበር፡፡ ፖለቲከኛው ከጉምቱ ፖለቲከኞቻችን ጋር በተፎካካሪነትም ይሁን በጓድነት መስራታቸውን ማጥበቅ ግዴታ ነው፡፡ 


በህዝብ ፊት እየወደቁም፣ እየተነሱም ነበር፡፡ ሁለቱንም የጋበዘን የሁሉም መሪወቻችን ልዩነት የሚያንሰው ባህል፣ ባህሪና ቁመና ነው፡፡ አሁን ለውጥ ያለ ይመስላል፤ ስለዚህ እጅግ በጣም ቢዘገይም፣ በግለሰቡ ብልህ ውሳኔ ቢደመደምም ትክክለኛ ጊዜው ነው፡፡ ቢያንስ በመጨረሻ የሚያጣጥረውን ኢዴፓ ንቀው በመተው መጨረሻቸውን የተሻለ ማድረግ ግን ይችሉ ነበር፡፡ የያዘ በቀላሉ የሚለቅ ቢሆን ኑሮ፡፡

No comments