Ethiopianism

አብዴፓ ከአብዓላ ጉባኤ እስከ አዲስ አበባ ቤተ መንግስት ግምገማ (በአካደር ኢብራሂም አኩ)

የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አብዴፓ

የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አብዴፓ ማለት የአፋር ክልልን በታማኝነት እንዲያስተዳድር ተብሎ በህወሓት ተጠፍጥፎ የተመሰረተ ፓርቲ ነው።

የፓርቲው አመሰራረት፣ የአፋር ህዝብ ተሳትፎ ምን ይመስል እንደነበረ፣ ህወሓት በአብዴፓ ምስረታ ላይ እንዴት እንደተሳተፈ የራሱ የሆነ በጣም ረጅም ታሪክ ያለው ሰለሆነ በዚህ ጽሁፍ ወደዛ አልገባም።

የዚህ ጽሁፍ አላማ በአፋር ክልል አሁን ካለው ፖለቲካዊ ችግር በመነሳት በፓርቲው ውስጥ ያለው ሽኩቻ መነሻው ምን እንደሆነ፣ ፓርቲው ካለፉት 25 አመታት በተለየ በመጨረሻዎቹ 3 አመታት የወደቀበት ቀውስና አሁን የቆመበት ቁመና ለመተንተን እሞክራለሁ።

ክልሉን ለረጅም ጊዜ የመሩት የቀድሞው የህወሓት ተጋይ አቶ ኢስማኢል አሊ ሲሮ በስልጣን ለረጅም ጊዜ በመቆየት የህዝብ ትኩረት ሰለሳቡና በኢትዮጺያም ብቸኛው ከ 20 አመታት በላይ በክልል ፕሬዚደንትነት የቆዩ በመሆናቸው የአፋር ህዝብን በተወሰነ ደረጃ ለማረጋጋት ታስቦ ከምርጫ 2007 በኃላ እንዲነሱ ተደረገ።

በሁሉም ጉዳዮች ፈላጭ ቆራጭ የሆነው ህወሀት አቶ ኢስማኢል አሊ ሲሮን ከክልል መሪነት አንስቶ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዲመረጡ አደረገ።

አቶ ኢስማኢል አሊ ሲሮ የተነሱት በአፋር ክልል መተካካት ተደርጓል ለማስባል ታስቦ ቢሆንም እሳቸው ተነስተው ሌላ ባለ ረጅም ዕድሜ የህወሓት ተጋይ ተኳዋቸው።

አቶ ኢስማኢል ከለቀቁ በኃላ ግን በጊዜው የክልሉ ጸጥታ ዘርፍ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት የነበሩት ሀጂ ስዩም ይህንን ወንበር ለመያዝ በፓርቲው ዉስጥ ከነበሩት ምሁራን ወጣቶች ጋር ከፍተኛ ትግል ዉስጥ መግባት ነበረባቸው።

ሀጂ ስዩም አወል ማለት በትምህርት ዝግጅት፣ ማንበብም ሆነ መፃፋ የማይችሉ፣ ግን ደግሞ በድፍረት ከራሳቸው በላይ ምንም ነገር እንደማያዩ ይነገርላቸዋል።

አቶ ኢስማኢል የክልሉ ፕሬዚደንት እያሉ ሀጂ ሱዩም አወል የክልሉ የጥጸታ መዋቅር በእጃቸው ሰለነበረ ኢስማኢል የሚፈሯቸው ብቸኛ ሰው ነበሩ።

እማኢል ተነስቶ አዲስ ፕሬዚደንት ለመምረጥ ግን ሀጂ ስዩም አወል የፓርቲውን ህገ ደንብ እስከ መጣስ ሄደው የፓርቲው ሊቀመንበር የነበረ አቶ ጣሃ አህመድ የፕሬዝደንቱ ምክትል የነበረ አቶ አወል አርባና ሌሎች ሆነው ለሁለት ተከፋፍለው ለስድት ወር የክልሉ መንግስት ሳይመሰረት ሊቆይ ችሏል።

ልክ እንደ አሁንም እስከ አዲስ አበባም ለሽምግልና የሄዱበት ሁኔታ ሁላ ነበር።

ይሁን እንጂ የዛሬን አያርገውና የዛኔ ሀጂ ስዩም የሚተማመኑበት የወያኔ መንግስት 100% ምርጫ ማሸነፉን ለኢትዮጲያ ህዝብ በትዕቢት ያወጀበት ጊዜ ሰለነበረ ለሀጂ ስዩምና ቡድናቸው ከህግም ከህዝብም በላይ መተማመኛ የነበረው መጨረሻ ላይ በህወሓት የሚሰጠው ውሳኔ ነበረ።

ከብዙ ሰብሰባዎችና ግምገማዎች በኃላ ከህወሓት የመጣው አንድ ተወልደ ዕዉር የተባለ ሰው በፈረንጆች አቆጣጠር 28/09/2015 ሰመራ ላይ ጣልቃ በመግባት በወሰኑት መሰረት የሀጂ ስዩም አወል ቡድንበህግ ወጥ መንገድ ሊያሸንፍ ችሏል።

የሀጂ ስዩም አወል ቡድን ኢስማኢል አሊ ስሮ ከተነሳ በኃላ ሀጂ ስዩም የክልሉ ፕሬዚደንት ለመሆን የፓርቲ ሊቀመንበር የነበረው ጣሃ አህመድ ከፓርቲው ጉባኤ በፊት ማንሳት ነበረባቸው።

ጣሃ አህመድ ደግሞ በብዙ መመዘኛዎች ቀጣዩ ፕሬዚደንት የመሆን ዕድል ነበረው።

የፓርቲው ሊቀመንበር በመሆኑ፣ በጊዜው ክልሉ ላይ ብዙ ድጋፍ እያገኘ የነበረ፣ ሁለተኛ ዲግሪ ያለው ወጣት መሪ በመሆኑ ወዘተ……

ይሁን እንጂ ጣሃ አህመድም ቢሆን በስልጣን ቆይታው የእነ ኢስማኢልና የእነ ስዩም አወል ተቀጽላ ሆኖ አያውቅም ማለት አይደለም።

ሀጂ ስዩም አወል የፓርቲው ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት በሰበብ አስባቡ አቶ ጣሃን ከፓርቲ ሊቀመንበርነት አንስተው ጉባኤዉን በፈለጉት መንገድ እንዲያመቹቻ በጀመሩት ትግል ጣሃ አህመድም የራሱ የሆነ ቡድን አደራጅቶ ሽኩቻው ለስድስት ወራት ከቀጠለ በኃላ መጨረሻው አቶ ስዩም አወል በህገ ደንብ ሳይሆን ከህግ በላይ በሆነው የህወሓት ይሁንታ አሸነፉ ተባለ።

የመጨረሻ ውሳኔ በተወልደ ዕዉር ጣልቃ ገብነት ሲተላለፍ ጣሃ አህመድና አንዳንድ የእሱ ቡድን አባላት የነበሩ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሰብሰባዉን ረግጠው ወጥተው ነበር።

በጊዜው የነበረው የፓርቲው ሽኩቻ በፓርቲው በራሱ ህገ ደንብ እንኳን ሲታይ የፓርቲው ሊቀመንበር ለማባረር ወይም ከስራ ለማገድ 2/3ተኛው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ድምጽ መግኘት አለበት ይላል።

የሀጂ ቡድን ግን አንድ ድምጽ እንኳን አብላጫ ድምጽ እስካለን ድረስ ጣሃ መውረድ አለበት ብለው 21 ለ 20 በሆነ ድምጽ ነበረ ጣሃን ለማውረድ ሲከራከሩ የነበሩት።

በመጨረሻም የህወሓቱ ሰውዬም የወሰነው በዚህ መንገድ ብቻ እንደነበረ ይታወቃል።

በዚህ ሁኔታ ጣሃ አመድ ከስልጣን ከወረደ በኃላ የፓቲው ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ሀሳን አብዱልካዲር አንድ ጊዜ ሰለ ህገ ደንቡ ተጠይቀው ፓርቲው ያንን አንቀጽ አሻሽሏል ብለው እንደነበረ አስታውሳለሁ።

መቼም በአፍሪካ ስልጣን ላይ ለመቆየት ህገ መንግስትን፣ ህግ ደንብን መቀየር የተለመደ ነገር ነውና አይገርምም።

ግን ፓርቲው ህገ ደንቡን ለመቀየር ራሱ የሚያስፈልገው ህጋዊ አካሄድ ይኖራል ብዬ አስባለሁ።

ያም ሆነ ይህ የሀጂ ስዩም ቡድን በዚህ ሁኔታ በህገ ወጥ መንገድ ወይም ደግሞ በህወሓት እገዛ ድል አድርጎ በሽኩቻው ምክንያት ከ 6 ወራት በላይ የዘገየው የፓርቲው 6ተኛ ጉባኤ ወደ ማዘጋጀት ገቡ።

ጣሃ አህመድ በዚህ ሁኔታ ከተወገደ በኃላ ጊዜያዊ የፓርቲው ሊቀመንበር የሆኑት ሀጂ ስዩም አወል ጉባኤውን በአብዓላ ከተማ ከጥቅምት 30 / እስከ ሕዳር 03/ 2008 ዓ.ም አካሄዱ።

አሁን በአብዓላ በተደረገው ጉባኤ የተከሰተው ህገ ወጥ የሆነ ምርጫና አሁንም በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጣልቃ ገብነት ለማዕከላዊ ኮሚቴ እጩ ሆነው ከቀረቡት ሰዎች መሃል ሀጂ ስዩም አወል፣ አቶ ኢስማኢል አሊ ስሮ፣ አምባሳደር ሀሳን አቡልካዲር፣ ሙሀመድ ከድር ( አንበጣ )ና አቶ ደረሳ አሊ ያላለፉ የነበሩ ቢሆንም ከለፉት ውስጥ አምስት ሰዎች በማስቀረት እነዚህ ሰዎች እንዲያልፉ የተደረገበት ሁኔታ እንደነበረ ይታወቃል።

ለዚህ ማሳያ ከሚሆኑ ነገሮች አንዱ አስመራጭ ኮሚቴ የነበሩት ሰዎች ውጤቱን ለማሳወቅ ከሁለት ቀን በላይ ጊዜ ወስዶባቸው እንደነበረ አስታውሳለሁ።

ከዛ በኃላም አስመራጭ ኮሚቴ ከነበሩት ሰዎች መሃል አንዳንዶቹም እንዳረጋገጡልኝ በመጨረሻው ሌሊት በጊዜው የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት የነበሩት በአቶ አባይ ወልዱ የሚመራ የህወሀት ቡድን ወደ አብዓላ በመምጣት ወጤቱን እንዳስቀየሩ ነግሮውኛል።

እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ከአቶ ኢስማኢል አሊ ሲሮ በኃላ ሌላ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው የተሾሙት የሓጂ ስዩም አወል ያለፉት 3 አመታት ቆይታ “ ሀ ” ብሎ ይጀምራል ማለት ነው።

ሁላችንም እንደሚናውቀው በኢትዮጲያ ባለፉት 28 አመታት በሰመ ፌዴራሊዝም ህዝቦች ራሳቸውን በራስ ማስተዳደር ይችላሉ ተብሎ እውነታው ግን ህወሓት በየክልሎቹ የራሱን አደራ ጠባቂዎች ቁጭ አድርጎ ሲያዛቸው እንደነበረ ከማንም የተሰወረ አይደለም።

በተለይ ደግሞ የአፋር ክልል በተመለከተ ህወሓት ቀጥታ ከትግራይ ክልል ቀጥሎ የሚያሽከረከረው ሁለተኛ ክልል ስለሆነ ሁኔታው ለየት ይላል።

ይህም የአፋር ህዝብን መሰረት ያደረገ ሳይሆን ህወሓትን የሚያስደስት ስራ ብቻ ለመስራት የሚለፋ አመራሮች በአጋሮች ስም በመያዝ የአፋር ህዝብን ወደ ኃላ ለማስቀረት፣ ከሌሎች ጋር በማጋጨት፣ የተፈጥሮ ሃብቱን በመዝረፍ፣ የሚቃወም ካለም በመግደል፣ በማሰር፣ በመሰወር ብዙ ይቅር እንኳን የማይባሉ በደሎችን ስርቷል።

ይሁን እንጂ ላለፉት ሃያ አመታት አስፈጻሚ ሆነው የቆዩት አቶ ኢስማኢል ተነስተው ሀጂ ስዩም አወል በዚህ ሁኔታ ሲሾሙ ከነበሩት ችግሮች ለየት ባለ መልኩ የአፋር ክልል ፖለቲካ የጎሳኝነት መልክ ይዟል።

ለዚህ ዋናው ተጠያቂዎችም ሀጂ ስዩምና አማካሪዎቻቸው እንደሆኑ የብዙዎች እምነት ነው።

ሀጂ ስዩም ከወታደራዊ ልምዳቸው መጥተው በሃይል በያዙት ስልጣን በአብዓላ ጉባኤ ለፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካስመረጡት ሰዎች 7ቱ የራሳቸው ጎሳ አባላት በመሆናቸው ብዙዎችን ያስገረመ አዲስ ነገር ነበረ ማለት ይቻላል።

ሀጂ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ እያሉም ቢሆን ልዩ ኃይል መሪዎች በወንድም ልጆች፣ በ አጎት ልጆች፣ በቅርብ ቤተሰቦች ከመሬት ተንስተው የኮማንደር ማዕረግ በመስጠት አደራጅተዋል።

የአፍዴራ ጨው አምራቾች ማህበር ዋና የቦርድ ሰብሳቢም የውንድማቸው ልጅ እንዲሆን ያደረጉ፣ በመሆናቸው ወደ ፓርቲውና መንግስት ደግሞ ይህንን የ አንድ ቤተሰብ የበላይነትና ስልጣንን በመጠቀም ለራሳቸው ቤተሰቦች ብቻ ያደሉ በሚል ከኢስማኢል አሊ ሲሮ በተለየ መልኩ ይወቀሳሉ።

አሁንም ቢሆን በፓርቲው ውስጥ ያለው ሽኩቻ ሀጂ ስዩም በአብዓላ እንዲያሸንፉ ከጎናቸው የነበሩ ሰዎችም ጭምር ተቃዉሞ እየገጠማቸው እንደሆነ ይታያል።

አሁን በፓርቲው ውስጥ ያላቸው ድጋፍም የጎሳ መልክ የያዘ ሲሆን፣ አብዛኛው ሀጂ ስዩምን የሚደግፉት የራሳቸው ጎሳ ሰለሆኑ ከፖለቲካም በላይ አደገኛ አካሄድ እንደሆነ ልብ ልንለው ይገባል።

ኢስማኢል አሊ ሲሮ በራሱ ጊዜ የለየለት አደርባይ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም በዚህ ደረጃ ግን ጎሳን መነሻ ያደረገ ፖለቲካ አልነበረውም።

አሁን የሀጂ ስዩም ይህንን አካሄድ ከተቃወሙት አንዱም አቶ ኢስማኢል አሊ ሲሮ እንደሆነ ይታያል።

ኢስማኢል አሊ ሲሮ እራሱ ስልጣን ሲለቅ ሀጂ ስዩም እንዲያሽንፍ ወሳኝ ሚና የተጫውተ ቢሆንም አሁን ዶር አብይ ከተመረጡ በኃላ በይፋ የሀጂ ስዩምን ኔትዎርክ ከተቃዉሙት ውስጥ ይገኛል።

ኢስማኢል አሊ ሲሮ እራሱ ከስዩም በላይ ሊጠየቅበት የሚገባ ብዙ ወንጀሎች አሉት፣ በተጨማሪም ወጣቶቹ ተሸንፈው ሀጂ ስዩም እንዲመጣ ያደረገው ራሱ ኢስማኢል ነው ብለን የሚናምን ሰዎች እኔን ጨምሮ እንዳለን ሁሉ፣ ኢስማኢል ያኔ ህወሓት እያለ ሌላ አማራጭ አልነበረዉም ዋናው ነገር አሁን በመደመር ባቡር መሳፈሩ ነው የሚሉም አሉ።

ለማንኛውም ይሄ ለውይይት ልተወውና አሁን ፓርቲው ወደ የት እያመራ እንደሆነ እንመልከት።

አብዴፓ አሁን የደረሰበት ሁኔታ በጣም አደገኛ ሁኔታ ነው።

እንደ ሌሎች ክልሎች በዲሞክራሲ መምጣት አለመምጣት፣ በፍትህ፣ በለውጥና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ሳይሆን በጎሰኝነት ላይ የተምሰረተ፣ አደገኛ አካሄድ፣ የፓርቲው መርዝ እስከ ህዝብ ድረስ ወርዶ ህዝቡ በያለበት በጎሰኝነት እንዲጋጭ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።

አሁንም ሀጂ ስዩም ቢቀጥሉ ደስ ይላቸዋል፣ ካልቻሉ ግን ሌጋሲያቸውን ለማስቀጠል በራሳቸው እጅ የመለመሉዋቸው አልፎል ተርፎም በስጋ ከሌሎች አፋሮች ይቀርቡኛል ብለው የሚያስቡ ሰዎችን ለመተካት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

ዋናው የፓርቲው የችግሩ መነሻ፣ የሽኩቻ ማባባሻ የሄው ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶር አብይ አህመድ በ አዲስ አበባ የፓርቲው አመራሮችን ካነጋገሩ በኃላም ወደ ክልል ተመልሰው እየተዘጋጁ ያሉት ለዚህ ነው።

ፓርቲው በሚቀጥለው ሳምንት ጉባኤ ያካሄዳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከዛ በፊት ከሁሉም ወረዳዎች የተወጣጡ ሰዎች የተሳተፉበት ኮፈረንስ ለሁለት ቀናት ማለትም ከኃዳር 16-17/ 2011 ሰመራ ላይ አካህዷል።

ከሰብሰባው በኃላ አምስት ነጥቦችን የያዘ የአቋም መግለጫ የተሰጠ ሲሆን፣ አንዱን ቡድን ለሌላኛው ቡድን ያስተላለፈው የተለመደ የማስፈራራት የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ጎጠኝነትና ሌሎችም በኢትዮጲያ ከሌሎች አከባቢ የጠፉ ቃላት የተሞሉበት መግለጫ ነበረ።

ነገስ? አሁን ከጉባኤ በኃላ ምን አይነት ሂደት እንደሚኖር የሚታይ ይሆናል።

አንዳንድ በህጂ ስዩም ደጋፊዎች ተመርጠው የመጡ ሴቶች በትናንቱ ሰብሰባ ላይ ሀጂ ስዩም መውረድ የለበትም፣ ሀጂ ከወረደ ሶሪያ እንሆናለን እያሉ ነበረ ተብሏል።

እንግዲህ ሶሪያ፣ ወይስ ጂጅጋ ወይም ደግሞ መቀሌ መሆናችን አይቀርም በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ።

የነገ ሰው ይበለን።

ቻው።

No comments