Ethiopianism

የጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በጀርመን ያደረጉት ንግግር

የጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በጀርመን ያደረጉት ንግግር

አይነን ሾነን ጉተን ታግ!
ኤይቶፒሼ ዲያስፖራስ ኢን ዶችላንድ ኡንት ኤይሮፓ!
ክቡራትና ክቡራን!


ከመላው አውሮፓ የተሰበሳባችሁ የሀገሬ ልጆች ሆይ፣ የማይንን ወንዝ ተገን አድርጋ በተቆረቆረችው፣ የገንዘብና የኢንዱስትሪ ማዕከል በሆነችው ፍራንክፈርት ተናኝተን በአይነ ሥጋ መተያየታችንንን እንደ ታላቅ እድል እቆጥረዋለሁ።


ከሀገር የወጣችሁበት ዘመንና ምክንያት እንደ ቁጥራችሁ ብዙ፣ እንደየመጣችሁበት ሀገር ለየቅል መሆኑ ግልፅ ነው። ለትምህርትም ይሁን ለሥራ፣ በፖለቲካም ይሁን በኢኮኖሚ የተሰደዳችሁ ወገኖቼ… ከምንወዳት ሀገራችን እና ሁሌም ከምትናፍቁት ህዝባችን እጅግ የከበረ ሰላምታ ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።


ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደዛሬው ከኋለኛው ተርታ ተመድባ በችግሯ ከመታወቋ በፊት ከአውሮፓ አገራት ጋር ታሪካዊ የሆነ ግንኙነት ነበራት። ከእንግሊዝ ጋር በትምህርት፣ ከፈረንሳይ ጋር በባቡር ሀዲድ፣ ከፖርቱጋል- በጦር ትብብር፣ ከቱርክና ከግሪክ በንግድ፣ ከስዊድን በጤናና በአየር ሀይል፣ ከሩሲያና ከሌሎች የምስራቅ አውሮጳ ሀገራት ጋር በተለያዩ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የነበረን ታሪካዊ ተዛምዶ እስከዛሬም የቀጠለ የወዳጅነታችን መሠረት ነው። ከጀርመንም ጋር ቢሆን ጠንካራ ትስስር ነበረን።


አምስተኛዋ ግዙፍ የጀርመን ከተማ ፍራንክፈርት፣ የታዋቂው ደራሲ ዮሐን ዎልፍ ጋንግ ቮን ጎይተ ከተማ ናት። በዚህ ታላቅ የጥበብ ሰው ስም የተቋቋመ ስመ ጥር ኢንስቲቲዩት በአገራችን ከመኖሩ በተጨማሪ የጀርመን የባህል ማዕከልና ትምህርት ቤት መቋቋሙ ጠንካራ ትስስርና ወዳጅነት ስለመኖሩ አንዱ ማሳያ ነው። እንደ አገር ከጀርመን ጋር፣ እንደ አጠቃላይ ደግሞ ከአውሮፓ ጋር ወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ተመሳስሎም አለን።


እንደምታውቁት፣ ለእኛ የቅርብ ጊዜ እውነታ በሆነው ጦርነትና ግጭት ውስጥ ያላለፈ የአውሮፓ ሀገር የለም። ለምሳሌ ያህል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በእጅጉ ከተጎዱት የአውሮፓ ከተሞች መካከል አንዷ ፍራንክፈርት ናት። ብዙ ሕዝብ አልቆባታል፤ መኖሪያ ቤቶቿ የሙታን መንደሮች መስለው ነበር፤ አያሌ የንግድና የገበያ ሥፍራዎቿ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል። 


ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ታዋቂ የነበረውና በወቅቱ ከጀርመን በታላቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ዋናው የንግድ መናኸሪያዋ ወድሟል። ሆኖም ግን፣ የማይበገሩትና ለችግር የማይረቱት ፍራንክፈርቶች ከተማቸውን እንደገና ገንብተው የአውሮፓ የፋይናንስ ማዕከል ለማድረግ ዐርባ ዓመት እንኳ አልፈጀባቸውም። ይህ ለእኛ ትልቅ ትምህርት ነው።

ሃያ ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የዓለማችን ታላላቅ ጦርነቶች የማስተናገድ ክፉ ዕጣ በላያቸው ላይ የተጫነባቸው አውሮፓውያን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦቻቸውን አጥተዋል፤ ለዘመናት የተገነባ ታሪካቸው አመድ ሆኗል፤ የልዩነት ግንብ በመካከላቸው ተገንብቶ ቆይቷል። 


በዘመኑ፣ አውሮፓውያን እንኳንስ ለሌሎች ሕዝቦች መጠጊያ ሊሆኑ ይቅርና በገዛ ሀገራቸው ተስፋ ቆርጠው ስደትን የመረጡ ዜጎች ቁጥር ቀላል አልነበረም። ያ ሁሉ አበሳ የመጣው በጥቂቶች፣ ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ በግል ጥቅማቸው በታወሩ መሪዎች እና የእኛ ዘር ከሁሉም ይበልጣል ባይ ደመ-ነፍሳውያን ቅዠት መሆኑ በጸጸት የሚታወስ ክፉ የጦርነቱ ጠባሳ ነው።  

የዚህ አሰቃቂ ጥፋት የፍጻሜ ትርፉ ድህነት፣ ጉስቁልና፣ ስደት፣ ወረርሽኝና እልቂት ብቻ ነበረ። ሆኖም ግን፣ ጠንካሮቹ አውሮፓውያን ከአንደኛውና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት እጅግ በፈጠነ ጊዜ አገግመው፣ ዛሬ ላይ እናንተን ጨምሮ ከመላው አለም ሚሊዮኖችን እስከማስጠለል ደርሰዋል። እርስበርስ መሸናነፍን ትተው አለምን ማሸነፍ ችለዋል። 

ይሄን ያሳኩት በአጋጣሚ አይደለም። ወገባቸውን አሥረው፣ ተስፋ መቁረጥን አባርረው፣ የደረሰባቸውን መከራ ሁሉ ለነገ ሲሉ ታግሠው፣ ለአገራቸው አንድ ሆነው በትጋት ስለሠሩ ብቻ ነው። እዚህ ቦታ በፊታችሁ ስቆም ሀገራችን በኢኮኖሚ በልጽጋ፣ ሰላማችን ሙሉ በሙሉ ተሟልቶ፤ ግጭት ጠፍቶ፣ ዴሞክራሲ ጎልብቶ፣ ሰብአዊ መብት በላቀ ሁኔታ ተከብሮ ቢሆን ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር። ግን አይደለም።  

አሁን በእጃችን ያሉን ሁለት ነገሮች ናቸው። ነጻነትና ተስፋ። እነዚህን ሁለቱን ይዘን በትብብርና በአንድነት ከሰራን የምንሻት ኢትዮጵያን ከመፍጠር የሚያግደን የለም። ከጦርነቱ ማግስት አውሮፓውያን ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ ከመገፈታተር ይልቅ ትብብርን የመረጡት ጥቅሙ ስለገባቸው ነው። ሕዝቡ ጦርነትን አምርሮ ቢጠላ ገፈት ቀማሽ ሆኖ ስላየው ነው። ዘረኝነትንና የበላይነት አባዜን አምርሮ የተዋጋው ካደረሰበት ውድመትና ጥፋት ስለተረዳው ነው።

ይህ፣ እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ፣ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠን ትምህርት ከፍተኛ ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ብዙዎቹ የለውጥ ጅምሮች በመሳሪያና በአመጽ ተጀምረው፣ በማሸነፍና በመሸነፍ፣ በማሳደድና በመሰደድ የተደመደሙ መሆናቸው ለሁላችን ግልፅ ነው። 

አዲስ የሰላምና የእርቅ ምዕራፍ ከመሆን ይልቅ የሌላ ዙር ውጊያ እና አመጽ መጀመሪያ የሆኑበት አጋጣሚ ብዙ እንደነበር የትናንት ታሪካችን ምስክር ነው። አሁን፣ ያላየነውን የምናይበት፣ ያልሞከርነውን የምንሞክርበት ዘመን ነው።  

ምቾታችንን ተወት አድርገን፣ መከራዎቻችንን ታግሰን፣ ጥርሳችንን ነክሰን የምንሰራበት፤ ለአገራችን በተባበረ ክንድ የምንተጋበት ወቅት ነው። በየጎራው ያሉ ሀይሎች አሸናፊ የሚሆኑበትን የፖለቲካ ባህል ከአውሮፓ ተምረን እንደ አገር አሸናፊ የምንሆንበትን መንገድ መያዝ አለብን፤ ይገባናልም።

የተከበራችሁ ወገኖቼ!


ከሩቁ ሆናችሁ ስለ ሀገራችሁ ስትሰሙ በአንድ በኩል ትደሰታላችሁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ትከፋላችሁ። አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ታደርጋላችሁ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተስፋ ትቆርጣላችሁ። ግን ርግጠኛ መሆን ያለባችሁ አንድ ነገር፣ ኢትዮጵያ ማንም ተነስቶ በወደደው ልክና መልክ እንደቂጣ ጠፍጥፎ የሚጋግራት የግል ርስት ሳትሆን፣ ዘመናትን ያስቆጠረች፣ ታላቅ ሕዝብ የመሠረታት፣ ታላቅ ሀገር መሆናን ነው።  


‹እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው› እንደተባለው፣ አንቀላፍታ ይሆናል እንጂ አልሞተችም፤ ደክማ ይሆናል እንጂ አልተሸነፈችም፤ ቀጥና ይሆናል እንጂ አልተበጠሰችም። ተስፋ ሳንቆርጥ፣ ሳንከፋፈልና ጊዜያችንን የማይጠቅም ነገር ላይ ሳናባክን ወገባችን አጥብቀን ከሠራን አገራችንን ታላቅ ማድረግ የሚከብድ አይሆንም።

መቼም፣ ኢትጵያዊ ሆኖ የኢትዮጵያን ክፉ ማየት የሚመኝ ጤነኛ ሰው አለ ብዬ አላምንም። እዚህ ከተሰበሰባችሁ ያገሬ ልጆች መሀል የሀገሩ ነገር ሆዱን የማይበላው ውስጡን የማያንሰፈስፈው ሰው አይኖርም። ኢትዮጵያዊነትን ከቃላት በዘለለ እና ከስሜት በተሻገረ መልኩ በስራ የምናሳይበት ዘመን ላይ ስለሆንን ለጊዜው የማይጠቅመውን ትተን፣ የሚያስፈልገንን አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል።


ወደድንም ጠላንም እንደ ሀገር ልንሸሻቸው በማንችላቸው ሦስት መሰረታዊ የጊዜ ማዕዘኖች መካከል ላይ እንገኛለን። ከትናንት ስህተቶቻችን የምናስተካክለው፣ ዛሬ ተግተን ልንሠራው የሚገባን፣ ለነገ ደግሞ የምንገነባው ሁነኛ መሠረት አለ። እነዚህን ሦስቱን አጣጥመን ለመሄድ በምናደርገው ትግል አንዳንድ ጊዜ ወደ አንዱ መጎተታችን አይቀሬ ነው። 


ከትናንት አያሌ መልካም ነገሮችን እንደወረስን ሁሉ ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮችንም ወርሰናል። ፍትሕን፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን፣ የዳበረ የሥራ ባሕልን፣ በሕግና በሥርዓት መኖርን፣ ሐሳብን በነጻነት መግለጥን፣ ረሐብና ድህነትን ማስወገድን በተመለከተ ገና ብዙ የሚቀሩን ሥራዎች አሉ።

እነዚህን የምናሳካው በማንመልሰውና በማንቀይረው ትናንት ላይ እየተጨቃጨቅን፣ ወርቅ እድላችንንና ጊዜያችንን በማባከን ወይም ጥቂቶች በሚያዘጋጁልን አጀንዳዎች በመተራመስ ሳይሆን ልቦናችን የሚያውቀውን በጎ ሀሳብ ወደ ተግባር በመቀየር ነው። 


ጊዜውን መጣያ እንዳጣ ሰው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥደን ውድ እውቀታችንና ጉልበታችንን በማፍሰስ ሳይሆን ትርጉም ያለው ስራ ላይ በመሰማራት ጭምር ነው። ጨለማውን ለመግፈፍ ሻማ ማብራት እንጂ የጨለማውን ክብደትና ጽልመት መስበክ መፍትሄ አይሆንም።  

እኔ ለሀገሬ ምን ሠራሁ በማለት እንጂ እነ እገሌ አገሬን ጉድ ሰሯት እያልን መዓት ብናወራ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም። ይሄንን ማድረግ ካልቻልን ለሀገራችን ያለን ጥልቅ ፍቅር በግብር የሚገለጸው እምኑ ላይ ነው?
ክቡራንና ክቡራት
ፍትሕና ዴሞክራሲ ስለተፈለጉ ብቻ አይገኙም። በሰላማዊ ሰልፍና በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ጠዋት ተዘርተው ማታ የሚያፈሩ ዛፎችም አይደሉም። እነርሱን የሚያበቅሉ፣ አብቅለውም ማሳደግ የሚችሉ ተቋማትን ይፈልጋሉ። እነዚህ ተቋማት ባልተገነቡበት፣ ተገንብተውም ባልዳበሩበት ሁኔታ የምንመኘውን ፍትሕንና ዴሞክራሲን ሳይሆን የጠላነውንና የሸሸነውን ሥርዐት አልበኝነትና አፋኝነት አጭደን ምርቱን ማቀፋችን አይቀርም።  

እህሉን ስለፈለግነውና ስለዘራነው ብቻ አይበቅልም። መሬቱ እህሉን ለማብቀል የሚችል፣ ሰብሉም ተገቢው እንክብካቤ የሚደረግለት ከሆነ ብቻ ነው፣ ዛሬ ቡቃያ ሆኖ የሚያጓጓን የለውጥ ሰብል ነገ ሁላችንን ስንመኘው የኖርነውን የሥልጣኔና የብልጽግና ነዶ ሊያሳቅፈን የሚችለው።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተከለ ያለው አዲሱ የለውጥ እርምጃ አቅጣጫው በዚሁ የሚመራ ነው። ፍትሕንና ዴሞክራሲን ሊሸከሙ፣ ሊያሳልጡ፣ ሊያሰፍኑና ሊያስከብሩ የሚችሉ ተቋማትን በመገንባት ላይ እንገኛለን። በተጓዳኝም ለተቋማቱ የሚመጥን አመለካከት ያላቸው ባለሞያዎችንና ቢሮክራቶችን መምረጥ፣ ማሠልጠንና መመደብ የሳንቲሙ ሌላኛው ገፅታ ነው።  


ውጤታማነትና ቅልጣፌን የሚያረጋግጥ ተደርጎ ሰሞኑን ያዋቀርነው አዲስ ካቢኔም ከዚሁ ዓላማና ግብ በመነጨ ነው። ምርጫ ቦርድ ነጻ፣ ተአማኒና ገለልተኛ እንዲሆን ለማድረግ የሕግና የመዋቅር ማሻሻያ እየሠራን ነው። የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት በሠለጠነ መንገድ የዜጎችን መብትና ክብር ጠብቀው የሚፈለግባቸውን ሥራ እንዲሠሩ ጠንካራ ሪፎርም በማካሄድ ላይ እንገኛለን። 

መከላከያችን በሁሉም መልኩ ኢትዮጵያን የሚወክልና የሚመስል፤ የዘመነና ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት ሀገሪቱን ሊጠብቅ በሚችልበት ቁመና ላይ እንዲገኝ የበኩላችንን እየሰራን ነው። የፍትሕ ተቋማት ለዜጎች መብት መከበር የሚሠሩ፣ በገለልተኝነት፣ በሕግ-የበላይነትና በኅሊናቸው ልዕልና ብቻ እንዲዳኙ፣ በሕዝቡም ዘንድ የሚከበሩና የሚታፈሩ ተቋማት እንዲሆኑ ማድረግ የዚህ ዓመት አንዱና ዋናው ሥራችን ነው። በቅርቡም በፍትህ ዘርፉ ተከታታይ እርምጃዎች የሚወሰዱ ይሆናል።

የትምህርት ሂደቱን የተሻለና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶለት በሚመለከታቸውም አካላት እንዲታይ ሠፊ የተግባር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንገኛለን።


የትናንቱን ዝንፈት ከመጠገንና በጠንካራ መሰረት ላይ ከማነጽ ጎን ለጎን የዛሬው ግንባታ ከሥር ከሥሩ እንዲፋጠን፣ አሁን ላለው ትውልድ ሥራ መፍጠር፣ ኢኮኖሚው በሚገባ እንዲያንሠራራ ማድረግ፣ የኑሮ ውድነትን መቋቋም፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ማብረድና እንዳይከሠቱ ማድረግ፣ የውጭ ግንኙነታችንን ውጤታማ ማድረግ፣ ለነገ ፋታ የማይሰጡን ተግባራት ናቸው። ለነገው ትውልድ የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት ደግሞ ከፊታችን ተዘርግቷል።


የአገሬ ልጆች

በሶስት ግንባር ከከፈትነው ጦርነት ጋር የምናደርገው ትግል መደምደሚያው በድል እንደሚጠናቀቅ በፍጹም አልጠራጠርም።

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጄኔራል ፓርክ፣ በጀርመን ሀገር በነርስነትና በመአድን ቁፋሮ ሥራ ተሰማርተው ይኖሩ የነበሩ የዴያስፖራ ዜጎቻቸውን ደሞዝ በመያዣነት በመጠቀም ብድር መጠየቃቸው ይታወሳል። በሂደትም ተመፅዋች ሀገራቸውን ዛሬ ከእድገት ማማና ለጋሽ ሀገር ማድረግ ችለዋል።


የእኛ ትውልድ የምታኮራና አንጸባራቂ የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ግዙፍ ኃላፊነት ከፊታችን ተዘርግቷል። ምናልባትም የሚነሳው ቁልፍ ጥያቄ ይሄንን ማድረግ ይቻለናል ወይ? የሚል ነው። ያለጥርጥር አዎ! ይቻለናል! ነው መልሱ።


ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያን ያህል ታላቅ ሀገር፣ ባለ ክቡር ታሪክ፣ የጠቢባንና የሊቃውንት መፍለቂያ ምድርን፣ የማይበገርና የማይናወጥ ሕዝብ ይዞ መሸነፍ የማይታሰብ ነው። 


ከተባበርንና አንድ ከሆንን፤ በትንንሾቹ ጉዳዮች ላይ የተጣዱ ትኩረቶቻችንን ወደታላላቆቹ ቁምነገሮች መልሰን ትልቁ ሥዕል ላይ ካተኮርን፣ ዛሬን ለነገ ስንል ችለን፤ ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ለመገንባት ከቆረጥን፤ ጉልበታችንን በማይረቡ ነገሮች ላይ ካላፈሰስን፣ ምንጮቹን ጅረቶች፣ ጅረቶቹን ወንዞች፣ ወንዞችንም ባሕሮች ለማድረግ ቆፍጠን ብለን ከሠራን ድላችን ሩቅ አይሆንም፣ ይቻላል። የድል ነጋሪትም ይጎሠማል።

የተከበራችሁ የሀገሬ አምባሳደሮች


እኔ ዛሬ እዚህ የቆምኩት እናንተ በአውሮፓ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እንድሆናችሁ ከልቤ ስለማምን እና ከኮሪያውያን ስለተማርኩም ጭምር ነው። የሀገራችሁ ነገር ስለሚያሳስባችሁ ቀን በሥራ ብትደክሙም ሌሊቱን በሀሳብ ተጉዛችሁ ስለ ሀገራችሁ ስትብሰለሰሉና ላይ ታች ስትሉ እንደምታድሩ በሚገባ አውቃለሁ። 


እዚህ ማስናችሁ ከምታገኙትን፣ ሀገር ቤት ያለው ዘመዳችሁ እኩል ተካፋይና የወዛችሁ ተጠቃሚ መሆኑም ድንቅ ነው። ለራሳችሁ በኪራይ ቤት እየኖራችሁ የወላጆቻችሁን ቤት ትሠራላችሁ። እናንተ ለመማር ያላችሁን ዕድል አሳልፋችሁ ቀን ከሌት እየለፋችሁ ታናናሾቻችሁን ታስተምራላችሁ። ይህንን ሁሉ የምታደርጉት በእርግጥ ሀገራችሁን ስለምትወዱ ነው። ስለዚህም አምባሳደሮች ብላችሁ አይበዛባችሁም።

ኢትዮጵያውያን ከአውሮፓ ጋር ያላቸው ትውውቅ ከ 500 ዓመታት በላይ ዕድሜ ማስቆጠሩን የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። በዚህ ዕድሜ ውስጥ ኢትዮጵያውያን በተደራጀና በአሰራር በተደገፈ መልኩም ባይሆን ለሀገራቸው የሚሆን ብዙ ነገር እየቀሰሙ በነጠላና በቡድን በመሆን ወደሃገራቸው ተመልሰዋል። 


እናንተም እንደነርሱ ለሀገራችሁ የሚበጀውን ሥራ ሁሉ ለመስራት መትጋት ይኖርባችኋል። ዕውቀትን አሻግሩ። ለሀገራችሁ የገቢ ምንጭ ፍጠሩ። አዳዲስ አሠራሮችን አምጡ፤ እንዲሆን የምትመኙትን በጥልቅ መረዳት ጨብጣችሁ ወደሃገራችሁ ኑና ተግባራዊ አድርጉት። ከማንም አትጠብቁ።  

ኢትዮጵያ የእናንተ ናት። ማንም ቢሆን የእናትና የአባቱን ቤት በማገዝ እንጂ በማማረር ለውጦ አያውቅም። ኢትዮጵያም ይሄንኑ ትፈልጋለች። ማን ለማን ቅሬታ ያቀርባል? ሁላችንም እኛው ነን። ማን ማንን ያማርራል? ሁላችንም እኛው ነን። ማን ለማን ሥራውን ይተወዋል? ሁላችንም እኛው ነን። አንድ ቤተሰቦች ነን።

አምባሳደሮቼ ሆይ!


አሁን በአውሮፓ ቅዝቃዜው እየጀመረ ነው። ከክፍለ ዘመናት በፊት በድፍን አውሮፓ በቅዝቃዜው ጦስ ብዙ ሕዝብ ያልቅ ነበር። የሕልውና ጉዳይ ነውና በችግሩ ከመረታት ይልቅ፣ ችግሩ ወደ ብልሃት መራቸው። የበረዶውን ወቅት በማሞቂያና በበረዶ መጥረጊያ የሚያልፉበትን ብልሃት ቀየሱ። የሀሩሩንም ግለት ለማብረድ የአየር ማቀዝቀዢያን ፈለሰፉ።  


በችግር መቆዘምና ማማረር ሳይሆን ችግርን እንደ ዕድገት መሰላልና ድልድይ በማየት ጉዞን በፍጥነት ወደ ላይና ወደ ፊት ማድረጉ ይበጃል። ስለዚህ፣አንድ ሆነን ዛሬ እንነሣ! የምንተኛበት ሳይሆን የምንነቃበት… የምንከፋፈልበት ሳይሆን ያለንንና የሆነውን ሁሉ በአንድነት አጣምረን የምንነሳበት ጊዜ ነው። ትናንት ከኛ ውጭ ነው። 

ቆርጠን ከተነሳንና ከተጠቀምንበት ያለንም ያለነውም ዛሬ ላይ ነው። የማግለል ሳይሆን የማቀፍ፣ የመንቀፍ ሳይሆን የማበረታታት፣ ሁሉን ለኔ የሚል ሳይሆን የመተሳሰብ ባህል ከፈጠርን ደግሞ ገና ያልተነካው ነገም አንጡራ ሀብትና ወርቃማ ዕድል ሆኖ ከፊታችን ይጠብቀናል። ዛሬ ላይ በርትተን በመሥራት የነገን የሰለጠነ ማህበረሰብና የበለጸገች ውብ ኢትዮጵያን አብረን እንገንባ።

ከዐሥር ዓመት በኋላ ችግሮቿን ሁሉ ትዝታ ያደረገች፣ የማትፈርስ፣ የማትቀለበስና ወደ ኋላ የማትመለስ… ለሁላችንም የምትበቃ፣ ለሌሎች የምትተርፍ፣ የአፍሪካ ኩራት፣ የዓለም ፈርጥ የሆነች ኢትዮጵያን አያለሁ።

ተስፋ አደርጋለሁ። በስደትና በተለያዩ ምክንያቶች ሀገርና ቀያቸውን ጥለው በየሰዉ ሀገር የተበተኑ ህዝቦቿ በሀገራቸው በፈቀዱበት ቦታና መንገድ በፍቅርና በመልካም ጉርብትና በሀገራቸው ዘና ብለው የሚኖሩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።  

ተስፋ አደርጋለሁ። የኢትዮጵያ ወጣቶች አውሮፓ መጥተው ለማግኘት ለሚያልሙት ያልርተረጋገጠ ቀቢጸ ተስፋ የሰሀራን በርሃ አቋርጠው፣ የሜዲትራኒያንን ባህር ከፍለው የሚነጉዱበት ዘመን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያከትማል። ፍሰቱ ወደ አውሮፓ መሆኑ ቀርቶ ወደ ኢትዮጵያ ይቀለበሳል። ልጆቻችን ወደ አውሮፓ ለጉብኝት እንጂ ለስደት የሚመጡበት ጊዜ ያበቃል።

ተስፋ አድርጋለሁ። ዛሬ በመረጥነው በጎ ጎዳናና በፈጸምነው ሰናይ ምግባር ልጆቻችንም በክብር ስማችንን እንደሚያነሡ አምናለሁ።

ተስፋ አደርጋለሁ። ይሄ ሁሉ ውጣ ውረድ አልፎ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በእግራችን እየተራመድን የዛሬዋን ቀን በደስታ አስታውሰን እንኳንም ለዚህች ታላቅ ሀገር ደከምን ብለን ደስ የሚለን ቀን ይመጣል።
ተስፋ አደርጋለሁ። ሁላችንም ወደ ልቡናችን ተመልሰን፣ የትናንቱን በዕርቅና በይቅርታ ዘግተን፣ የነገውን በተስፋና በፍቅር ሰንቀን፣ የምንኮራባትን ልዩ ሀገር እንገነባለን።
ተስፋ አደርጋለሁ። አምናለሁም።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
አመሠግናለሁ
ኢሽ ዳንከ ኢኔን


ምንጭ - ኤፍ.ቢ.ሲ

No comments