Ethiopianism

ጥቂት የመጀመርያ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት ስለሆኑት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ

ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ነው።

አራት ሴት ልጆች ለነበሯቸው ወላጆቻቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገና በ17 ዓመታቸው ነጻ የትምህርት ዕደል አግኝተው ወደ ፈረንሳይ በማቅናት ሞንትፔልየር (Montpellier) በምትባለው የፈረንሳይ ከተማ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሞንትፔልየር (University of Montpellier) የተፈጥሮ ሳይንስን አጥንተዋል። 

በሀገረ ፈረንሳይ ለዘጠኝ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ክፍልን ማገልገል ጀመሩ። ቆይተውም የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን በበላይነት መርተዋል። 

ከዚያም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዘዋወር በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል። በመቀጠል አምባሳደር ሆነው በመሾም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል።  

በአምባሳደርነት ሴኔጋል ዳካር 4 ዓመት ፣ ጅቡቲ 9 ዓመት ፣ ፈረንሳይ 4 ዓመታት አገልግለዋል። በአፍሪካ ህብረት በሰላምና ፀጥታ በሰሯቸው ጥሩ ስራዎች እውቅናን አትርፈዋል። በተባበሩት መንግስታት የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ፣ የምስራቅ አፍሪካ ብቸኛዋ ሴት የተመድ ቋሚ ተጠሪ ሆነው በሃላፊነት ሰርተዋል።

በቅርቡ በአፍሪካ ህብረት የተመድ ዋና ፀሐፊ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በዲፕሎማሲ ዘርፍ በአፍሪካ ከሚጠቀሱ መካከል ቀዳሚ እንስት ናቸው።

እኝህን ስንት ታሪክ የሰሩና ወደፊትም መስራት የሚችሉ ታላቅ ምሁር ዛሬ የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል።

መልካም የስራ ዘመን!

No comments