Ethiopianism

ለውጡ እና እኔ (ግዛው ለገሰ)

ለውጡ እና እኔ (ግዛው ለገሰ)

የለውጡ ደጋፊ ነኝ፡፡ ለውጡ እንዲሳካ ድርሻዬ ለመወጣ እፈልጋለሁ። ይህ እንዲሳካ የሚቀጥሉትን ጥያቄዎች ለራሴ ለመመልስ ጥሬያለሁ።

አንደኛ፦ ለውጡ የማነው? 

ይህ ጥያቄ ለውጡን ማን አመጣው ለማለት አይደለም፣ ለውጡን ማንም ያምጣው ታሪክ ካሳውን ይክፈለው። ጥያቄው ለለውጡ ስኬታማነት፣ ውድቀት፣ ጤንነትና ችግሮች ሃላፊው፣ ባለቤቱ ማነው ነው የሚለውን ለመዳሰስና የእኔን ቦታ ለማወቅ ነው። የለውጡ ብቸኛ ባለቤቶች አብይ ወይንም ኦዴፕ፣ ወይንም ቲም ለማ አይደሉም። 

እኔ እራሴም የለውጡ ባለቤት ነኝ፣ ስለዚህ የሚነሱት ችግሮች የኔም ችግሮች ናቸው፣ መፍትሄ መፈለገ የኔም ድርሻ ነው። እርግጥ ስልጣን ያላቸው ሰዎች ከኔ በተሻለ ለለውጡ ቅርብ ናቸው፣ ስልጣንና መሳሪያ - (ጦር መሳሪያ ማለቴ አይደለም) መገናኛ ብዙሃን፣ ድርጅቶች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ገንዘብ … - አላቸው፡፡  

ስለሆነም ከኔ የበለጠ ይጠበቅባቸዋል። ግን ችግር በተፈጠረ ቁጥር እኔ እንደ ነጻ ዜጋ ከደሙ የለሁበትም እያልኩ እነሱን እንደ ችሎታ ቢሶች፣ እንደደካሞች፣ እንደ ተንኮለኞች .. አድርጎ ማቅረብ አይገባም፣ ውጤት አልባም አፍራሽም ነው። 

እንደመሪዎች ሊተቹ ይገባል ግን እኔም እንደ ባልድርሻ፣ እንደ ለውጡ ባለቤት ትችቶችን ለመገንባት፣ ከዛም ባላፈ ከአማራጭ ሃሳቦች ጋር ማቅረብ እንደ አለብኝ ይሰማኛል።

ሁለተኛ፦ ለውጡ ቀላላ ነው? በአጭር ግዜ ይመጣል? 

ይህን ጥያቄ የምንመለስበት መንገድ ብዙ ነገሮችን ይጠቁማል። ለእኔ ለውጡ የተወሳሰብ፣ ሁለት እርምጃ ወደፊት አንድ እርምጃ ወደኋላ የሚጓዛበት፣ አልፎ አልፎ የፍትህና የሰላም እጦት የሚታይበት፣ ረጅም ግዜ የሚወስድ ማናችንም የምንፈለገውን ሙሉ በሙሉ የማናገኝበት ሂደት ነው። 

ለውጡ ብዙ ፍርጆች አለቱ፣ አንዳንዶቹ ቀላል ናቸው፣ ለምሳሌ የባለስጣኖች መለዋወጥ፣ አንዳዶቹ በጣም ከባዶች ናቸው፣ ለምሳሌ የፖለቲካ ባህላችንን፣ የመግስት ተቋማትን መቀየር፣ ከተንሰራፋው የማንነት ፖለቲካ ወደ ነጻነት ፖለቲካ መሸጋገር የብዙ አመቶች የተወሳሰበ ጉዞ ነው፡፡ የለውጡ ሂደት ለመለካት የእኔን መለወጥ ማየት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ሶስተኛ ፦ አገራችን ያልችበት ሁኔታ ምን ይመስላል? 

በእኔ ግምት - ከአራት መንግስታት ትዝብት አንጻር ሲታይ - አገራችን ቋፍ ላይ ነች። እንደ አፄ ሃይለስላሴ ግዜ ግብግቡ በተማሪዎችና በመንግስት መካከል አይደለም፣ እንደደርግ ግዜ ጦርነቱ በድርጅቶችና በመንግስት መካካል አይደለም፣ እድሜ ለህወሃትና መልሰ ዜናዊ ዛሬ ችግሩ በህዝብ ለህዝብ መካከል ነው። 

ለአመታት የተገነባው ማንነትን የተሻገረ አብሮነት በሃያ ሰባት አመቶች የጥላቻ ፖለቲካ ተበጥሶ፣ ዛሬ ሁሉም በየቋንቋው ጎረቤቱን በጎሪጥ የሚያይበት ግዜ ነው። ይህ ማለት የለውጥ ፈላጊዎች የምንወስዳቸው እርምጃዎችና፣ የምንመኘው ለውጥ ፍጥነት የተዳፈነውን ፍም እንዳያቀጣጥለው መጠንቀቅ አለብን።  

የለውጡ አንዱ እጅግ አስፈላጊ መለኪያ የምንወስዳቸው እርምጃዎች የማህበርሰቡ አብሮነት የበለጣ የሚያከር መሆን የለበትም። ሲጠቃለል ለስህተት ያለን ክፍተት እጅግ ጠባብ ስለሆነ በሽተኛውን ላለመግደል መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
አራተኛ ፦ ለውጡ ወደፊት ለመግፋታ አውጭ የሆኑ ምን አማራጮች አሉን? 

የዶር አቢይ ቡድን ዛሬ በወገድ ወይንም አልፈልግም ቢል አማራጮቻችን ምንድናቸው? ይህ ሌል እጅግ አስፈላጊ ጥያቄ ነው። ፈረንጆች እንደሚሉት ፍጹም የጥሩ ጠላት (“Don’t let the perfect be the enemy of the good”.) እንዲሆን መፍቀድ የለብንም። 

ዛሬ በየሰበቡ በለውጡ ተስፋ መቁረጥ ገንቢ አይደለም፣ መፍትሄም አይሆንም። የሚነሱ ችግሮች እንዲያውም የበለጠ ለመሰራት መነሳሻ መሆን አለባቸው።

አምስተኛ ፦ የለውጡ ፍጥነትና የቀለባሾች ጉዞ ፍጥነት ምን ይመስላል? 

ይህ ለእኔ በጣም የሚያሳስበኝ ነገር ነው፡፡ ዶር አብይና ቡድኑ ለውጡን የሚያካሂዱበት ፍጥነት በቀልባሾች ስራ እንዳይቀደም በጣም እፈራለሁ። 

የለውጡ ዝገምተኝነትና የማይቀራው የሃያል አሰላለፍ ለውጥ ፈር አለመያዝ ብዙ የለውጥ ወዳጆችን ከጫዋታው አስወጥቶ ለቀልባሹ ሃይል መንገድ እንዳይከፍት ስራዎች መሰራታ አለባቸው፡፡ 

ይህ ደግሞ የሚሆነው እንደ እኔ የለውጥ ደጋፊ የሆነው በጽናት ስንቆምና የመፍትሄው አካል ስንሆን ነው።

No comments