Ethiopianism

‹‹ማታ ማታ›› ከሕይወት እምሻው

ሕይወት እምሻው

ለጥቅምት ወር የሚሞቅ ምሽት ነበር፡፡ ክረምቱ ገበያችንን ዜሮ አስገብቶት ስለነበር መስከረም ሲጠባ ከድፍን ሃገር በላይ የምንደሰተው እኛ ነን፡፡ መስከረም ግን ድርቃም ወር ነው፡፡ ብዙ ሰው አይመጣም፡፡ አዳሜ ለእንቁጣጣሽ በግ፣ ለአዲስ መጋረጃ እና ለልጆች ደብተርና ለዩኒፎርም እንጂ ለእኛ ገንዘብ ስለሌለው ወደዚህ ዝር አይልም፡፡ ጥቅምት ሲጀምር ግን ጎዳናው በመኪናዎች ይሞላል፡፡ በእግረኞች ይደምቃል፡፡

የሰውነቴን ያህል ተለጥጦ ዳሌዬን የሚያወጣውን ደማቅ ሮዝ ቀሚስ ነው የለበስኩት፡፡ ደማቅ ሮዝ እንደኔ ላሉ ለጥቁረት ለሚቀርቡ ጠይም ሴቶች ጥሩ ቀለም ነው፡፡ አጉልቶ ያሳያል፡፡ ታኮው ቀጭንም ረጅምም የሆነ በፍፁም የማይመች ጫማ አድርጌያለሁ፡፡ ተለይቼ ለመታየት ከምከፍለው መስዋእትነት አንዱ ነው፡፡ እዚህ ስቆም ለምቾት አይደለም፡፡ ታይቼ ለመወሰድ፣ ተወስጄ አገልግሎት ለመስጠት፣ ሰጥቼ የእንጀራዬን ገንዘብ ለመቀበል ነው፡፡

ቀሚሴን የሚመስል ሊፕስቲክ አድምቄ የተቀባሁዋቸው ከንፈሮቼ ቤቱ ለመሄድ ያሰበ ባለትዳርን ከሩቅ ጠልፈው እንዲያስቀሩ፣ ወንድነቱ የፈተነውን ወጠምሻ እንቅፋት ሆነው እንዲጥሉ አድርጌ አሞጥሙጫቸው፣ ረጅምና ቀጭን እግሮቼን ፈርከክ አድርጌ ቆሜ የማታ እንጀራዬን እጠብቃለሁ፡፡

አጥር የሚጋሩ ኤምባሲዎችና የውጭ ድርጅቶች እንደ እንጉዳይ ከበዙበት ሰፈር ነው የምሰራው፡፡ ብዙ ተወዳዳሪዎቼ የሆኑ ሴቶች ፈንጠር ፈንጠር ብለው ቆመው የእድላቸውን ይጠብቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ በመሰላቸት ወዲህ ወዲያ ሲውረገረጉ፣ የደከማቸው ስልክ እንጨት ተደግፈው ይናውዛሉ፡፡  

የመንገድ መብራት የሌለበት ቦታን መርጠን ስለምንቆም አጠገባችን ያልደረሰ አያየንም፡፡ ገበያ መምጣቱን የምናውቀው እግረኛው ኮቴው ሲቀርበን፣ ባለ መኪናው ደግሞ ረጅም መብራቱን ሲረጭብን ነው፡፡ ያኔ ወደ ዳር ወጥተን የቱ ይሻልሃል እንላለን፡፡ ጎንበስ ብለን ናሙና እናሳያለን፡፡ አኔን ምረጠኝ…እኔን ውሰደኝ በሚል እየተወዛወዝን እናባብላለን፡፡

ረጅም መብራት በራብኝ፡፡

እንደ ልማዴ እግሮቼን ከቅድሙ የበለጠ ፈርከክ አድርጌ፣ ፈገግ አልኩና መላ ሰውነቴን በ‹እንዳያመልጥህ› አሳየሁት፡፡ ደስ ሳይለኝ ፈገግ ማለት የለመድኩት በዚህ ስራ ነው፡፡ ፈርከክ፣ ፈገግ፣ ጠጋ፡፡ የሁልጊዜም ሶስቱ ጥበቦቼ ናቸው፡፡

መኪናውን በደንብ አየሁት፡፡ ራቫ ፎር፡፡ አሪፍ…ከወሰደኝ ለዛሬ በዚህ ሊበቃኝ ይችላል ማለት ነው፡፡

አጠገቤ መጥቶ ቆመ፡፡ በከፊል የተከፈተው የፊት መስታወት ጋር ሄድኩና ጎንበስ ብዬ ውስጥ ያለውን ሰው ለማየት ሞከርኩ፡፡ ብልጭ ብልጭ የሚሉ አይኖችና ብዙ ነጫጭ ጥርሶች ብቻ ታዩኝ፡፡ ከሰል ጥቁር ነው፡፡ አፍሪካዊ ነው?

በቀበቶ እንደታሰረ ተንጠራርቶ በሩን ሲከፍትልኝ በደንብ ላየው ሞከርኩ፡፡
- ካም ኢን! አለ በወፍራም ድምፅ፡፡ አፍሪካዊ ነው፡፡ ቢንጎ! ዛሬ በቀላሉ ልገላገል ነው፡፡ ገባሁና ቁጭ አልኩ፡፡
እንደነገሩ አየኝና መኪናውን ሲያስነሳ ቶሎ ብዬ
- ሾርት ኦር ኦል ናይት? አልኩት
- ሾርት…ሃው ማች? አለኝ በቀላዋጭ አይኖቹ ከላይ እስከታች እንደገና እያየኝ፡፡

ራቫ ፎር፡፡ ጥቁር አፍሪካዊ፡፡

- ዋን ታውዘንድ…አልኩ
- ፋይን…ሌትስ ጎ….! አለና መኪናውን አስነሳ፡፡

የት እንደምንሄድ አላውቅም፡፡ ሰአቴን አየሁት፡፡ ለአራት ሃያ አምስት ጉዳይ፡፡ የአዲሳባ ግርግር እና የመኪና ጭንቅንቅ ግን አልበረደም፡፡ አፍሪካዊው መኪኖችን እያጠፈ፣ በጥድፊያ ይነዳል፡፡
እኔ ውጭ ውጪውን፣ መንገድ መንገዱን አያለሁ፡፡

አቧሬ እንደራሴ ሆቴል አካባቢ ስንደርስ የሆነች ከክር የቀጠነች የኮብልስቶን መንገድ ይዞ መንዳት ጀመረ፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ስጨርስ ለመመለስ ብዙ ገንዘብ አይፈጅብኝም፡፡ ግን የጥምዝምዙ ብዛት፡፡ የመንገዱ መጥበብ፡፡
ትልቅ አረንጓዴ በር ያለው ፎቅ ቤት ጋር እንደርስ በትእግስት ማጣት ብዙ ጊዜ ክላክስ አደረገ፡፡
ብዙ ሳይቆይ በሩ ተከፈተ፡፡ 

መኪናውን ግቢ ውስጥ ሲያስገባ ፔንሲዮን መሆኑን ግንቡን ተደግፎ በተቀመጠ ማስታወቂያ አወቅኩ፡፡ ‹‹ጨረቃ ጉዞ ፔንሲዮን› ይላል፡፡ አዲስ መሆኑ ነው..ወይ ደግሞ ስምና የንግድ ምልክት እየቀየሩ ይሆናል፡፡
ለመውረድ ስዘጋጅ ወደኔ ዞር አለና
- ዩ ጋት ኮንዶም? አለኝ
- የስ ብዬ ቦርሳዬን ‹‹እዚህ ውስጥ አለኝ›› በሚል ደብደብ አድርጌ አሳየሁትና ወረድኩ፡፡

እሱ በፍጥነት ወደ ቤቱ ውስጥ ሲገባ እኔ ደግሞ በማይመች ጫማዬ እየተሰቃየሁና እንደ ተረሳች ውሻ ቱስ ቱስ እያልኩ እከተለዋለሁ፡፡ ከዚህ ሰራ የሚያስጠላኝ ይሄ ነው፡፡ ሰለተገዛሁ የመኪና በር አይከፈትልኝም፡፡ ስለተገዛሁ እጄን ተይዤ፣ ትከሻዬን ታቅፌ አልገባም፡፡ ስለተገዛሁ እንደ ሰው ጎን ለጎን አልራመድም፡፡

ክፍሉ ውስጥ እንደገባን ደቂቃ እንኳን ሳያባክን ልብሱን አወላልቆ ብርድ ልብሱ ውስጥ ገባ፡፡ በብርሃን አየሁት፡፡ ፊቱ የእንቁራሪት ሰውነቱ ደግሞ የእንሽላሊት ይመስላል፡፡ ከዚህ ስራ የሚያስጠላኝ ሁለተኛው ነገር ይሄ ነው፡፡ ስለተገዛሁ እንቁራሪት እስማለሁ፡፡ ስለተገዛሁ ለእንሽላሊት ጭኖቼን እከፍታለሁ፡፡

ፔኒሲዮኑ ከውጪ እንደሚታየው አያስደንቅም፡፡ ከተለያየ ቦታ በልመና የመጡ የሚመስሉ ምናቸውም የማይመሳሰል እቃዎች ተፋፍገው የቆሙበት አስቀያሚ ክፍል ነው፡፡

ብርድልብሱ ውስጥ ሆኖ የእንሽላሊት ሰውነቱን እየነካካ ‹‹በምን ታፈጫለሽ…ነይና የሂሳቤን ስጪኝ እንጂ› በሚል አይን ያየኛል፡፡ ከዚህ ስራ የሚያስጠላኝ ሶስተኛው ነገር ይሄ ነው፡፡ ስለተገዛሁ ዛሬ ደብሮኛል ልተኛ ማለት አልችልም፡፡ ስለተገዛሁ ራሴን አሞኛል..ነገ ብናደርግስ ብዬ ጥቅልል ብዬ ማደር አይፈቀድልኝም፡፡

ቀሚሴን አውልቄ በውስጥ ሱሪዬ ብቻ አልጋው ውስጥ ገባሁ፡፡ ይሄን ሾርት ስራ እንዴት አድርጌ ይበልጥ እንደማሳጥረው እያሰብኩ ወደ አልጋው ውስጥ ገባሁ፡፡
- ዩ ቢ ኦን ቶፕ…ቶፕ…!አለኝ….

ታዘዝኩና እንሽላሊቱን ተፈናጥጬ ጀመርን፡፡ በተንቀሳቀስን ቁጥር ይሄ ደባሪ አልጋ ይንቋቋል፡፡ በከፊል የተገለጠው አሮጌና ቆሻሻ ፍራሽ ሲጥ ሲጥ ይላል፡፡ የጎረቤት አልጋዎችም እንደኛው ሲንቋቁ፣ ልክ እንደዚህኛው ፍራሽ ሲጥ ሲጥ ሲሉ ይሰማኛል፡፡ ፊቱን አየሁት፡፡ 

ከፍተኛ ህመም ውስጥ እንዳለ ሰው ጭምድድ…ኩምትር ብሏል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ረጅምና በጣም ቀይ ምላሱን ጎለጉሎ ያወጣል፡፡ ከልምዴ በመነሳት፣ እያስደሰትኩት መሆኔን ገመትኩ፡፡

ምላሱን ምን ያስጎለጉለዋል? እሱን ላለማየት በብዙ ስእሎች የተጨናነቀውን ግድግዳ በአይኔ ማሰስ ጀመርኩ፡፡ አንዱ ላይ ፏፏቴና ተራራ፣ ሌላው ላይ የቡና ስኒ ውስጥ ያለ ኤርትራ ያልተገነጠለችበት የኢትዮጵያ ካርታ፣ ሶስተኛው ላይ የፈረስ ፊት የምትደባብስ ራቁቷን ያለች ልጃገረድ…..አልጋው ይንቋቋል…ፍራሹ ሲጥ ሲጥ ይላል….እንቁራሪቱ ቁና ቁና ይተነፍሳል….ምላሱን ጎልጉሎ ያለከልካል....በዚያኛው ግድግዳ ላይ ደግሞ አበባ ማስቀመጫ ውስጥ የተቀመጠች የፈካች ፅጌረዳ….. መጨረሻውን ለማቅረብና ለመገላገል ፍጥነቴን ጨምሬ መስገር ጀመርኩ፡፡ ማርሽ ቀይሬ መጋለብ ጀመርኩ። ቼ! ቼ እንቁራሪት ወ እንሽላሊቴ! ቼ! ቼ!

ያልገባኝን ነገር ጮኸና ተጠናቀቀ፡፡ ግልግል፡፡ በፍጥነት ወርጄ

- ኦኬ…መኒ ፕሊስ…. አልኩት ቀሚሴን መልሼ እየለበስኩ፡፡ አልጋው ውስጥ ሆኖ እያለከለከ ነው፡፡
- በት ዩ አር ኤክስፔንሲቭ ማይ ሌዲ…አለ አይኑን እያስለመለመ እያየኝ፡፡

አዎ፡፡ ሲያልቅ ሁሌም ውድ ነው፡፡ እንሽላሊት!

- ፕሊስ ፔይ ናው…አልኩ ኮስተር ብዬ

ከአልጋው ውስጥ ፈንጠር ብሎ ተነስቶ ለብሶት የነበረው ኮቱን አነሳና ከኪሱ ብሮች አውጥቶ መቁጠር ጀመረ፡፡
ተቀብዬው ቆጠርኩት፡፡

አንድ ሺህ አንድ መቶ ነው፡፡

ተሳስቶ ነው፡፡ የራሱ ጉዳይ፡፡
ገንዘቤን ቦርሳዬ ውስጥ ከተትኩና ቀጥ ብዬ ወጣሁ፡፡

በር ላይ ስደርስ ፕላስቲክ ወንበር ላይ የተቀመጠው ወጣቱ ዘበኛ ልክ ቀጠሮ እንዳለን እና ከዚህ በፊት በየቀኑ ተገናኝተን ይሄንኑ ትእይንት እንደ ደጋገምን ሁሉ ነቃ ብሎ
- እ …ሲስቱ…ላዳ ልጥራልሽ? አለኝ፡፡
- አዎ…አልኩና ግምቡን ተደግፌ ቆምኩ፡፡
- ነይ እዚህ ቁጭ በይ….ብሎ ወንበሩን ለቀቀልኝ፡፡
አስር ከማይሞላ ደቂቃ በሁዋላ ታክሲው መጥቶ ጡሩምባ ሲያሰማ ለዘበኛው አስራ አምሰት ብር ሰጥቼው ወደ ላዳው ገባሁ፡፡

- የት ነሽ…አለኝ ሹፌሩ በተሰላቸ ደምፅ
- ስድስት ኪሎ…ስድስት ኪሎ ዮኒቨርስቲ…አልኩት እኔም በመታከት፡፡

ዛሬ እድል ቀንቶኝ ጣጣዬን በጊዜ መጨረሴ ጥሩ ነው፡፡ ገብቼ ጥቅልል ልል ነው፡፡ በዚያ ላይ ነገ ስርፕራይዝ ቴስት ይኖር ይሆናል።

No comments