Ethiopianism

ኦብነግ መገንጠል እንደሚችል ከዐቢይ አገዛዝ ይሁንታ አግኝቷል! አቻምየለህ ታምሩ


ኦብነግ መገንጠል እንደሚችል ከዐቢይ አገዛዝ ይሁንታ አግኝቷል

የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ኦብነግ «ሶማሌ ክልል»ን ከኢትዮጵያ መገልጠል እንደሚችል አስመራ ላይ ስምምነት ላይ ደርሷል! የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ዳር ድንበር የማይጠብቅ ስምምነት ከኦብነግ ጋር በማድረግ ኦብነግ ሶማሌ ክልልን መገንጠል እንደሚችል ስምምነት ላይ የደረሰው የዐቢይ አገዛዝ ትናንትና ካራማራ ላይ ኢትዮጵያውያን ሞተው መሬቱን ኢትዮጵዊ አድርገውታል ያለውን ምድር ነው። ድንቅም አገር ግንባታ!

ኦብነግ እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም. በሶማሊያ በወቅቱ ሞቃዲሾን ይዞ የነበረው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት የሽግግር መንግሥት አካል ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ (1724/2006) እንዳሳወቀው ሞቃዲሾን ይዞ ለነበረው ለእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ጊዜያዊ መንግሥት ድጋፍ ይሰጡ ከነበሩ አገሮች መካከል ግብፅና ሳዑዲ ዓረቢያ ተጠቃሾች ነበሩ።

የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት አባል የነበረው ኦብነግ አላማው የዚያድ ባሬን ባለ አምስት ኮከብ ታላቋን ሶማሊያን መፍጠር ነው። በሌላ አነጋገር የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ አስመራ ላይ ከኦብነግ ጋር የደረሰው ስምምነት በሳዑዲ ይደገፍ የነበረው የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት አባል የሆነው ኦብነግ የዚያድ ባሬን ህልም እንዲያሳካ ነው።

እንደሚታወቀው የኦብነግ ራዕይ ቀያሽ የሆነው ዚያድ ባሬ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የከፈተው ባሌን፣ ሐረርጌንና አርሲን ጨምሮ እስከ ናዝሬት ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ግዛት የታላቋ ሶማሊያ አካል ናቸው የሚል ትርክት ፈጥሮ ነው። የዚህ ራዕይ ውሉድ የሆነው ኦብነግም አላማው ያው ተመሳሳይ ነው።

ጥያቄው ዐቢይ አሕመድ አስመራ ላይ ከኦብነግ ጋር ሶማሌ ክልል መገንጠል እንደሚችል የተስማማው ኦብነግ የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት አባል በነበረበት ወቅት ትረዳ የነበረችዋንና ለዐቢይ አገዛዝም ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሰጡትን አረቦች ለማስደሰት ነው? ወይንስ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ? ለዚህስ ቀብድ ይሆን አረቦቹ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ለዐቢይ አገዛዝ ሰጡ የተባለው?

የዐቢይና የኦብነግ የአስመራው ስምምነት የኦብነግ ደጋፊው ሻዕብያና የኦብነግ ደጋፊ የሆነችው ሳዑዲ ያስማማችው የሳዑዲው የኢሳያስና የዐቢይ አሕመድ ስምምነት አካል ይሆን?

የቢቢሲን ዘገባ እነሆ



በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል አማጺ ቡድን የሆነው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር እዚህ እንዴት ደረሰ?

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት እሁድ ዕለት ከአሥመራ አሳውቀዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንደገለጹት የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባርና የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ያደረጉትን ድርድር ተከትሎ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የግንባሩ የውጭ ግንኙነት ፀሐፊ አቶ አህመድ ያሲን ሼክ ኢብራሂም ከኢትዮጵያ መንግሥት ስለደረሱበት ስምምነት አስመልክቶ ለቢቢሲ ሶማልኛ እንደገለፁት፤ የሶማሌ ህዝብ ዕጣ ፈንታውን በነፃነት ራሳቸው መወሰን እንዳለባቸው ከስምምነት ላይ መደረሱን ነው።

ህዝቡ መብቱን በመጠቀም የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን መብት በተጨማሪ ግንባሩም የሚታገልለትን አላማም በሰላም እንዲያስቀጥል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የራስን ዕድል በራስ መብትን ለመወሰን ህዝበ- ውሳኔ እንዲካሄድና ህዝቡ ከኢትዮጵያ መገንጠል ከፈለገ ያ መብት እንዲከበር፤ መቆየትም ከፈለገ ያ ውሳኔ እንዲከበርለት ውሳኔ ላይ ደርሰናል ብለዋል።

ህዝበ ውሳኔውንም ለማስፈፀምም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሁለትዮሽ ኮሚቴ እንደሚመሰረትም አስታውቀዋል።

ለበርካታ ዓመታት በምሥራቃዊው የሃገሪቱ አካባቢ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ወደ ሃገር ቤት ተመልሶ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ለመሳተፍ መወሰኑ ለሃገሪቱ ሰላም በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ ለሶማሌ ክልል ሰላም ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ኦብነግ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ትግል ያደርጉ ከነበሩ አማፂ ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1984 ነበር የተመሰረተው። ቡድኑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ተብለው ከተሰየሙ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ሦስት የፖለቲካ ቡድኖች ከሽብር ቡድን ዝርዝር ውስጥ በፓርላማው ውሳኔ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ በውጪ የሚገኙ የታጠቁ ተቃዋሚዎች ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል።

አማፂው አብነግ የኦጋዴን ሕዝብ ብሎ የሚጠራውን በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው የሶማሌ ሕዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለማስከበር በፖለቲካዊና ወታደራዊ መስኮች ትግል ሲያደርግ ቆይቷል።

ኦብነግ ከምስረታው አስራ አራት ዓመታት በኋላ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ሊግ ጋር በመዋሃድ የሶማሊ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን መስርተው ነበር።

ምን መቼ ሆነ?

ሚያዚያ 1996 ዓ.ም፡ የተቃዋሚ የሆነው ሬዲዮ ነፃነት ኦብነግ በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች ላይ በፈፀመው ጥቃት በርካታ ወታደሮችን መግደሉን ዘገበ።

መጋቢት 1998 ዓ.ም፡ የኦብነግ መሪዎች ከዴንማርክ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ያሉ ሶማሌዎች ላይ በመንግሥት ይፈፀማል ያሉትን የሰብዓዊ መብት ረገጣ አስረድተዋል። የዴንምርክ ባለስልጣናትም ያለው አስተዳደር ዴሞክራሲን የማይተገብር በመሆኑ ለኢትዮጵያ የሚሰጡትን እርዳታ አቋርጠዋል።

ጥር 2001 ዓ.ም፡ ኦብነግ ሼክ ሸሪፍ ሼክ አህመድ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ አልዎ መልዕክት አስተላለፈ።

ጥቅምት 2002 ዓ.ም፡ የኦብነግ ኮምኒኬሽን ሃላፊ ሁሴን ኑር የፑንትላንድና ሶማሊላንድ አስተዳደሮች ከኢትዮጵያ ሸሽተው የሄዱ ሶማሌዎችን አሳልፈው ለኢትዯጵያ መንግሥት ይሰጣሉ ሲል ከሰሰ።

ነሐሴ 2002 ዓ.ም፡ ኦብነግ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ተቃርቧል የሚለውን ዘገባ አስተባበለ።

ጥር 2003 ዓ.ም፡ ከ400 የሚበልጡ የግንባሩ አመራሮችና አባላት ከእስር ተለቀቁ።

ሰኔ 2003 ዓ.ም፡ ኦብነግ ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ በኢትዮጵያ መንግሥት ተፈረጀ።

ጥር 2004 ዓ.ም፡ ግንባሩ እንግሊዝ ውስጥ ባወጣው መግለጫ መንግሥት አጠቃላይ የሆነና በሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት በገለልተኛ ስፍራ ላይ ለመደራደር ፈቃደኛ ከሆነ ኦብነግ ዝግጁ መሆኑን ገለፀ።

ጥቅምት 2005 ዓ.ም፡ ኦብነግ መስከረም ላይ በኬንያው የመከላከያ ሚኒስትር ሞሃመድ ዩሱፍ ሃጂ አደራዳሪነት ናይሮቢ ውስጥ ከመንግሥት ጋር ሲያደርገው የነበረው የሰላም ድርድር ተቋረጠ።

ጥር 2008 ዓ.ም፡ ኦብነግ በሶማሌ ክልል በሚካሄደው የነዳጅ ዘይት ፍለጋ የክልሉን ህዝብ ያላሳተፈ በመሆኑ የህዝቡን ጥቅም የሚያስከብር እርምጃ እንደሚወስድ በፍለጋው ላይ የተሰማሩን የውጪ ኩባንያዎችን አስጠነቀቀ።

ግንቦት 2009 ዓ.ም፡ ኦብነግ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር በጋራ ለመስራት መስማማቱን ቡድኖቹ ባወጡት መግለጫ አሳወቁ። ሁለቱ ቡድኖች ጀርመን ፍራንክፈርት ውስጥ ለሦስት ቀናት ያካሄዱትን ስብሰባ ተከትሎ ነው ውሳኔያቸውን ያሳወቁት።

ነሐሴ 2009 ዓ.ም ፡ የሶማሊያ መንግሥት የኦብነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አብዲካሪም ሼክ ሙሴን (ቀልቢ ደጋ) በሰሜን ሶማሊያዋ ከተማ አዳዶ ውስጥ ይዞ ለኢትዮጵያ መንግሥት መስጠቱን አረጋገጠ።

ሰኔ 2010 ዓ.ም ፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ባለስልጣናት ውይይት መጀመራቸውን ተከትሎ የኦብነግ ምክትል ሊቀመንበርና ቃል አቀባይ ሙሃመድ ኦስማን አዳኒ ግንባራቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ንግግር ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን ተናገሩ።

ሰኔ 2010 ዓ.ም ፡ በአወዛጋቢ እርምጃ በፕሬዝዳንት ፎርማጆ መንግሥት ለኢትዮጵያ ተላልፎ የተሰጠው የኦብነግ የጦር አዛዥ አብዲካሪም ሙሴ (ቀልቢ ደጋ) ተለቀቀ።

ሰኔ 2010 ዓ.ም ፡ የኢትዮጵያ ካቢኔ አርበኞች ግንቦት 7ን እና ኦነግን ጨምሮ ኦብነግን የሃገሪቱ ፓርላማ ከሽብርተኝነት መዝገብ እንዲያስወጣ የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ አቀረበ።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ ኦብነግ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ግንባሩን የሽብር ቡድን ነው የሚለውን ውሳኔውን ውድቅ እንዲያደርግና ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ ስለሰጠው የጦር አዛዡ በይፋ ይቅርታ እንዲጠየቅ ሃሳብ አቀረበ።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ ኦብነግ ጅግጅጋ ውስጥ የተከሰተውን ግጭት አውግዞ ሁሉም ወገኖች ከኃይል ድርጊት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን የሰላም ጥሪን ተከትሎ ወዲያውኑ ተግባራዊ የሚሆን የተናጠል ተኩስ አቁም አወጀ።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ አስር የሚደርሱ የኦብነግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በማዕከላዊ ሶማሊያ ጋልሙዱግ በሚባለው ስፍራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ ኦብነግ ሙስጠፋ ኦማር የሶማሌ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸውን ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀበለው ገልጾ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በክልሉ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ አስጠንቅቋል።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ሞሃመድ ኦማር በቁጥጥር ስር መዋል እንደሚደግፍና ይህም ፍትህን ለማስፈን የተጀመረ ትክክለኛ እርምጃ ሲል ገልጾታል።
የኦብነግ መሪዎች

ሊቀመንበር፡ ኡትማን አድም ሙሃመድ ኡማር (ከጥቅምት 2002 ጀምሮ)

ምክትል ሊቀመናብርት፡ አዳኒ ሙሃማድ ኦስማን፣ ኦማር ሙሃመድ ኢስማኤል

የኮምኒኬሽን ኃላፊ፡ ኑር ሁሴን

No comments