Ethiopianism

የአክቲቪስቱ የፍቅር ደብዳቤ (አሳዬ ደርቤ)

የአክቲቪስቱ የፍቅር ደብዳቤ (አሳዬ ደርቤ)

ለምወድሽ……. እንዴት ነሽ? እኔ አንቺን ካፈቀርኩበትና አክቲቪስት ከሆንኩበት ጊዜ አንስቶ ደህና ሆኜ አላውቅም፡፡

በአገሬ ፍቅር ላይ ያንቺ ፍቅር ተጨምሮ እያቅበዘበዘኝ ነው፡፡ አሁን አሁንማ… ምግብ መብላትም ሆነ መንግስትን መተቸት አቅቶኛል፡፡ የማገኘው የላይክ ቁጥርም በእጅጉ ቀንሷል፡፡ 


የኔ ውድ፡- ለባለፉት ዓመታት የፖሊስ ኮሚሽነር እንጂ ፍቅር ይይዘኛል ብዬ አላስብም ነበር፡፡ ከአገሬ ተርፎ ለሴት የሚበቃ ፍቅር ይኖረኛል የሚል ግምትም አልነበረኝም፡፡ የሆነው ግን እንደዚያ ነበር!!

ባልታሰበ ቀን ከዐይኔ ገብተሽ እንቢተኛውን ልቤን እንደ ሜቴክ ዘረፍሽው፡፡ በመላ አካላቴ ላይ በመሰራጬት እንደ ህውኃት የመሬት ወረራ አካሄድሽብኝ፡፡ በፍቅርሽ ቦርቡረሽ በመግባት ጭንቅላቴ ውስጥ ኮማንድ-ፖስት አዋቀርሽብኝ፡፡ በማንነቴ ላይ ጥቃት ፈጸምሽብኝ፡፡ ከአብዲ ኢሌ በባሰ ወህኒ-ቤት ውስጥ አስገባሽኝ፡፡

የኔ አብዮት፡- ከወራት በፊት መንገድ ላይ አየሁሽ፡፡ እናም በአክቲቪስትነቴ በምታወቅበት አካውንቴ ላይ… ‹‹ይች አገር ወዴ'ት እየሄደች ነው?›› በማለት ፈንታ ‹‹ይች ልጅ ወዴ'ት እየሄደች ነው?›› የሚል ጥያቄ በመለጠፍ… ከኋላ ከኋላ እከተልሽ ጀመር፡፡ ያላንቺ እውቅና ዘይኑ ጀማልን በመሆን መዳረሻሽን መጣራቴን ተያያዝኩት፡፡ 

ሆኖም ግን በመጨረሻ ያየሁት ነገር እንደ ዶክተር አቢይ ስልጣን ‹‹ምነው በቀረብኝ›› የሚያስብል ነበር፡፡ ታከለ ኡማን ይመስል ቦሌ ላይ ከአንድ የባሌ ወጣት ጋር አፍ-ላፍ ገጥመሽ ስታወሪ እጅ-ከፍንጅ ያዝኩሽ፡፡ መቼስ በጊዜው እንዴት እንደተናደድኩ አትጠይቂኝ፡፡  

ከአቶ ታዬ ደንድኣ በላይ በጣም ስሜታዊ ሆኜ ነበር፡፡ ይሄም ሆኖ ግን …አፍቃሪሽ እንጂ ባልሽ ባለመሆኔ ‹‹እንዴት በኔ ላይ ይሄን ታደርጋለች?›› ብዬ ልወቅስሽ አልቻልኩም፡፡ ይልቅስ ሲጋብዝሽ ያየሁት ልጅ እንደ ኮሚሽነር ደግፌ በዲ አፍሶ ወደ ቤቱ ሳያስገባሽ በፊት ፈጠን ብዬ ከእጄ ላስገባሽ እንደሚገባ አመንኩኝ፡፡

እናም በአንዱ ምሽት በቻት ስጀነጅንሽ ከቆዬሁኝ በኋላ ‹‹ነገ አገኝሃለሁ›› የሚል ቀጠሮ ሰጠሽኝ፡፡ አዳሬንም አንጀትሽን የሚበሉ ቃላቶችን ሳሰባስብ አደርኩኝ፡፡ በማግስቱ ተገናኝተን ከፊትሽ ስቀመጥ ግን እንደ ዶክተር ደሳለኝና በቀለ ገርባ ልነግርሽ ያሰብኩት ሁሉ ጠፍቶኝ አረፈ፡፡  

ከዚያን ቀን በኋላም አንቺን ማግኘትና ኢትዮጵያን ማረጋጋት ህልም ሆኖ ቀረ፡፡ ምክንያቱም በድጋሜ ላገኝሽ ብዙ ጥረት ያደረኩ ቢሆንም… እንደ ፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ-ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ‹‹ቀጠሮ›› ከመስጠት ባለፈ በአካል አግኝቼሽ የልቤን ህመም እንዲነግርሽ አልፈቀድሽልኝም፡፡

የኔ ዉድ፡- አንቺን ካፈቀርኩበት ጊዜ አንስቶ ሃገራችን ላይ ስንት ክስተት እንደተፈራረቀ ታውቂያለሽ?
እኔ ከልብሽ ውስጥ መግባት አቅቶኝ ስፍገመገም ግንቦት ሰባትና ኦነግ ወደ ሃገር ቤት ገብተዋል፡፡ የኦሮማራ ጥምረት ተቀዛቅዟል። አዴፓና ህውኃት ጦር መማዘዝ ጀምረዋል፡፡ አንዱአለም ቡኬቶ የአንድ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ሁኗል፡፡ ዘውዳለም ታደሰ ታፍሷል፡፡ (….ብቻ ምን አለፋሽ ብዙ ነገሮች ተከስተዋል፡፡)

እኔ ግን የፌስቡክ ተከታዮቼን ትቼ አሁንም ድረስ አንቺን እየተከተልኩ እገኛለሁ፡፡ መንታ መንገድ ላይ ያለች አገሬን ችላ ብዬ ጥላሽ በመሆን አብሬሽ እነጉድ ይዣለሁ፡፡ በፌክ አካውንቴ መንግስትን እንዳልርበደበድኩኝ በእውነተኛ ማንነቴ አንቺን ማሸነፍ አቅቶኝ እየተንገበገብኩ አገኛለሁ፡፡ የማፈቅራትን ሴት ማግኘት አብዮት ከማስነሳት በላይ ከባድ ሆኖብኝ እንደ ራያ ምድር እየታመስኩ እገኛለሁ፡፡ እንደ ሐረር ከተማ በጥም እቃትታለሁ፡፡
.
አንዳንድ ጊዜ ‹ከዚህ በላይ ላለመሰቃየት› እወስንና የለከፈኝን ፍቅር ዲአክቲቬት በማድረግ ወደ ቀድሞ አክቲቪስትነቴ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡ ሆኖም ግን ላፕቶፕ ከፍቼ መጻፍ ስጀምር መንግስትን በሚተች ርዕስ ስር አንቺን ሳወድስ እገኛለሁ፡፡ በዚህም የተነሳ የቀድሞ ማንነቴን መመለሱ ሕውኃትን ወደ ስልጣን ከመመለስ በላይ ከባድ ሆኖብኝ እገኛለሁ፡፡

የኔ ንግስት፡- የሆነ ጊዜ ወንድ አይተሸ የማታውቂ ‹‹ልጃ-ገረድ›› መሆንሽን አጫውተሽኛል፡፡ እናም ልታገኝኝ የማትፈልጊው በዚህ የተነሳ ከሆነ… እስክንጋባ ድረስ እንደ ኦነግ ሰራዊት ትጥቄን የመፍታት ፍላጎት ስለሌለኝ የሚያሳስብሽ ነገር አይኖርም፡፡ በህገ-መንግስቱ ላይ ያደበርኩትን ሰፊ ልምድ ክብረ-ንጽህናሽ ላይ በማዋል ልደረምስሽ የምፈልገው ከጋብቻ እለታችን በኋላ ነው፡፡

በማስከተል ደግሞ ስለ ኑሮ ደረጃዬ ልነግርሽ የምፈልገው ነገር ለሚስትነት ስመኝሽ የምትኖሪበት ቪላና የምትነጅው መኪና በጥሎሽ መልክ ላበረክትልሽ ባልችልም መሰረታዊ ፍላጎታችንን ሊሸፍን የሚችል ከአባይ ጸሐዬና ከበረከት ስምኦን የተሻለ ገንዘብ እንዳለኝ ግን ልነግርሽ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ ላንች ያለኝ ፍቅር እንደ ስኳር ፋብሪካችንና እንደ አባይ ግድባችን የማያልቅ መሆኑን እንዲታውቂልኝ እሻለሁ፡፡  

ስለዚህም የአገራችን ህልውና ዶክተር አቢይ እጅ ላይ እንደወደቀው ሁሉ… የኔም ህልውና መዳፍሽ ውስጥ መግባቱን አውቀሽ የፍቅር ጥያቄዬን ትቀበይኝ ዘንድ እማጸንሻለሁ፡፡

በመጨረሻም… ‹‹አረሱት›› የሚለውን የፋሲል ደሞዝን ሙዚቃ በመጋበዝ በዚች የስንኝ ቋጠሮ እሰናበትሻለሁ፡፡

ወልቃይት የአማራ ራያ የወሎ
‹‹ይሁን›› ካለ ወዲያ በድንበር ከልሎ
አምላክ አንቺን ሰራ ‹‹የእሱ ሁኝ›› ብሎ፡፡ 

No comments