Ethiopianism

መረጃ በአሰቦት ገዳም ጉዳይ - ሃብታሙ አያሌው



መረጃ በአሰቦት ገዳም ጉዳይ - ሃብታሙ አያሌው

ከአንድ ሳምንት በፊት አመሻሽ ላይ ወደ ገዳሙ የመጡት ማንነታቸው ያልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች መነኮሳቱ ገዳሙን ለቀው እንዲሄዱ በማስፈራራታቸው ደውል ተደውሎ ምዕመናን ሲሰባሰቡ ታጣቂዎቹ ሸሽተው ወደ ጫካው መግባታቸው እና በቀጣዩም ቀን ወደ መነኮሳቱ መኖሪያ ድንጋይ ሲወረወር ማምሸቱም ተነገረ።

የገዳሙ መነኮሳት ለወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ስጋታቸውን በፅሑፍ አስገቡ። ያንን ተከትሎ ወረዳው የመደባቸው ታጣቂ ሚኒሻዎች በቦታው ሲደርሱ ከገዳሙ ጠባቂዎች ጋለ አለመግባባት ተከሰተ። 


የወረዳው ፖሊስ ከአንድ ጋዜጠኛ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ መነኮሳቱ ስጋታቸውን እና የተፈጠረውን ሁኔታው በፅሑፍ ማቅረባቸውን አምኖ፤ ፖሊስ ድጋፍ ለመስጠት ከላካቸው ሚኒሻዎች ጋር የተፈጠረው አለመግባባት ግን ባለመተዋወቅ የተከሰተ እንደሆነ መፍትሄ እንደተሰጠው ተናግሯል። 

አያይዞም አሁን የገዳሙ ጠባቂዎች እና በወረዳው የተመደቡ ሚሊሻዎች በጋራ እየጠበቁ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ለአንድ ሳምንት የዘለቀው አስጨናቂ የገዳሙ ሁኔታ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ታዋቂ የሆነው "ሐራ ተዋህዶ" ዌብሳይትን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎች ሲዘግቡት ቆይተዋል። 

በተለይም ገዳሙ የሚገኘው የተደራጁ ኃይሎች የሐረርን ህዝብ በውሃ ጥም እየቀጡ እንዲሁም በጥቅሉ ከድሬዳዋ እስከ ሐረር መኪና እያስቆሙ እየዘረፉ ባለበት አካባቢ መሆኑ። ይህ ሁኔታም በመንግስት ሚዲያዎች እና በአካባቢው ጉዳተኞች እየተነገረ በመሆኑ ሁኔታው በእጅጉ ብዙዎችን አስጨንቋል።

ባለሁበት አገር ለሊቱ በመንጋት ላይ እስከሚገኝበት ሰዓት የገዳሙን ሁኔታ በመከታተል ያገኘሁት መረጃ ከላይ የተመለከተውን ነው። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የገዳሙ ነዋሪ የሚዲያውን ተፅዕኖ ተከትሎ መነኮሳቱ ምንም አልተፈጠረም እንዲሉ እና ስጋቱን አሳንሰው እንዲናገሩ እንደታዘዙ ሚዲያም ለዚሁ ጉዳይ ወደ ቦታው እንደሚላክ ጠቁመዋል።

ዋናው እና ተፈላጊው ነገር የፖለቲካ እሰጥ አገባው ሳይሆን የታሪክ አሻራ የሆነው ገዳም እና መነኮሳቱ ደህና መሆናቸው ነው። በቅርቡ በሶማሌ ክልል በርካታ አብያተ ክርስቲያናት የወደሙት እና መነኮሳት በቁም በእሳት አርረው እንዲከስሉ የተደረጉት ከሶስት ወራት በፊት የደረሰባቸውን ዛቻ ሲናገሩ ሰሚ በማጣታቸው እንደሆነ የተገለፀው ከጉዳቱ መድረስ በኋላ ነው።

የወረዳው ፖሊስ ሚሊሻ መመደቡን መግለፁ የሚያስመሰግን ነው። የክልሉ መንግስት ግን በየቦታው ሚሊሻ መድቦ እሳት በነደደበት ሁሉ እሩጦ መፍትሄ ለመስጠት መሞከር ብዙ እርቀት አይወስደውምና አሁንም በህግ የበላይነት መከበር በኩል የዜጎች ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠበቅ ሊያደርግ ይገባል።

ችግር እያድበሰበሱ እያቃለሉ እየሸፋፈኑ ማለፍ አይበጅምን የፖለቲካ ድራማው ቀርቶ እውነተኛ መፍትሄ ይሰጥ። ነገሩን መካድ ችግሩን አይፈታውም። 27 ዓመታት በዚህ መንገድ ኑረናል። እናትን በጥይት የደፉት ልጇን ታሞ ነው የሞተው ሲያሰኙ ሰምተናል።  

ደህንነት ቢሮ ሲደበድቡት የሞተው የሐረሩን ኑረዲንን አስከሬኑን በገመድ አንጠልጥለው ተፀፅቶ ሞተ ብለው በኢቲቪ አሳይተው ደም አስነብተውናል። እውነት የወጣው ዘግይቶ ነው እናም የአሰቦት ገዳምን ጉዳይ እንደ እንደዛ ለማድረግ ባትሞክሩ ጥሩ ይመስለኛል።
ቢያንስ ገዳሙ በጋራ እየተጠበቀ መሆኑ እፎይታ ነው። ምንም ያልተፈጠረ ለማስመሰል መሞከረ መተማመንን
የባሰ ገደል ይከታልና ተወት አድርጉት።

No comments