Ethiopianism

በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ከአንድ ታካሚ ሆድ 127 ሚስማር በቀዶ ህክምና ወጣ

127 ሚስማር በቀዶ ህክምና ወጣ

በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ትናንት ሌሊት በተደረገ የቀዶ ህክምና 127 ሚስማርና ሌላም ባዕድ ነገር ከአንድ ታካሚ ሆድ ውስጥ ማውጣት ተችሏል።

ከሚስማሮች በተጨማሪ መርፌ፣ የተሰባበሩ ብርጭቆዎችና የጥርስ ማጽጃ ስንጥሮች ከታካሚው ሆድ ተዋግደዋል ተብሏል።

የኢዜአ ሪፖርተር በስፍራው በመገኘት ከወጣቱ ሆድ በቀዶ ህክምናው የወጡትን ባእድ ነገሮች ተመልክቷል።

ቀዶ ጥገናውን የመሩት በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ዳዊት ተዓረ እንደገለጹት፤ የ33 አመት እድሜ ያለው ወጣት በሆስፒታሉ በተደረገለት የቀዶ ህክምና በርካታ ባዕድ ነገር ከሆዱ እንዲወጣ ተደርጓል።


2፡30 የፈጀው የቀዶ ህክምና ሰባት የህክምና ባለሙያዎች ተሳተትፈውበት የተካሄደና በስኬት የተጠናቀቀ እንደሆነ ተገልጿል።

ላለፉት አስር ዓመታት 'አኩፌጂያ' ከተባለ የአእምሮ ህመም ጋር የቆየው ታካሚው ለስምንተ ዓመታት የአእምሮ መድሃኒት ሲወስድ መቆየቱንም ዶክተር ዳዊት ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ዳዊት ገለጻ፤ ታካሚው ከቅርብ ቀናት በፊት ወደ ሆስፒታሉ ለውስጥ ደዌ ህክምና በመጣበት አጋጣሚ ለአጠቃላይ ምርመራ የራጅ ህክምና ሲደረግለት በሆዱ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ የባዕድ ነገር ምስል በመታየቱ ነው ቀዶ ህክምናው የተደረገለት።

በዚህም ከ120 በላይ ሚስማሮችን ጨምሮ መርፌ፣ ስቴኪኒና የተሰባበሩ ጠርሙሶች በህክምናው እንዲወገድለት ተደርጎ በአሁኑ ወቅትም ወጣቱ በማገገሚያ ክፍል ውስጥ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ወጣቱ ሚስማሩንና ሌላውንም ባዕድ ነገር የዋጠው ከወራት በፊት እንደሆነ በህክምናው መረጋገጡንም ዶክተር ዳዊት አክለዋል።

ምንጭ፡- ኢዜአ

No comments