Ethiopianism

የመታወቂያው ጉዳይ "ሚስተር ኤክስን ያያችሁ" (ያሬድ ሹመቴ)

የመታወቂያው ጉዳይ "ሚስተር ኤክስን ያያችሁ" (ያሬድ ሹመቴ)

መታወቂያዬ ላይ በግድ የተፃፈብኝን የብሔር ማንነት ዜግነት ኢትዮጵያዊ ለማስባል ጥረት ያደረግኩበትን የባለፈውን ሳምንት የሦስተኛ ቀን ሙከራዬን ትረካ ያበቃሁት ከክፍለ ከተማው (በዘልማድ እንደሚባለው አውራጃ) ፍርድ ቤት ወደ ፌደራል ፍርድ ቤት ጉዳዬን እንዳቀርብ መላኬን ገልጬ ነበር። 


የዛሬውን ሙከራዬን እነሆ፡-
ከሰሙኑን የበዓል ስራ ጫና በኋላ ዛሬ የመታወቂያዬን ጉዳይ ለመከታተል ወደ ፌደራል ፍርድ ቤት ማምራት ጀምሬያለሁ። ከስራ ቦታዬ በቀጥታ ኮንትራት ታክሲ በመያዝ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ ላይ ሳለሁ የታክሲውን ሾፌር የመጻህፍት መሸጫ መደብር ሲያዪ እንዲያቆሙልኝ ጠየቅኳቸው። ሾፌሩ በእድሜያቸው የሦስት መንግስት የስራ እና የህይወት ልምድ ያላቸው ሰው ናቸው።

ትንሽ ስንግባባ "ምን መጽሐፍ መግዛት ፈልገህ ነው?" አሉኝ

"ህገ መንግስት። እቤቴ ሔጄ ከማምጣት እዚሁ ልግዛ ብዬ ነው"

"ምነው በሰላም ነው"

"የምኖርበትን ወረዳ እና የአዲስ አበባ መስተዳድርን ለመክሰስ ፈልጌ ነው።" ሾፌሩ መሪውን ይዘው በሳቅ ፍርስ አሉ።

"ምነው?" አልኳቸው

"ደግሞ መንግስት ይከሰሳል እንዴ?" 
ያቋረጡትን ሳቅ ቀጠሉት። "ምን ብለህ ነው የምትከሳቸው ለመሆኑ?"

"መታወቂያዬ ላይ የብሔር መረጃ ያለፍቃዴ በማካተታቸው እና በህገ መንግስቱ የማንነት መረጃ ላይ ብሔር እንዲጠቀስ ስለማያስገድድ ለምን ያለፍቃዴ የብሔር መረጃ ይካተትብኛል ብዬ ነው የምከሰው። እና ብሔር ወይንም ዜግነት ኢትዮጵያዉ እንዲባልልኝ ነው የምፈልገው"

ሳቃቸውን ሳያቋርጡ "ድሮ የቀረውን"

ሾፌሩ ስለ ጉዳዩ ያላቸውን ቀና አመለካከት ገልፀውልኝ ነገር ግን ይሳካል ብለው እንደማያምኑ ነግረውኝ፥ ከፌደራል ፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት የሚገኝ የመጽሐፍት መደብር በሳቅ አጅበው አደረሱኝ።

ወደ መጻህፍት መደብሩ ገብቼ ህገ መንግስት ይገኝ እንደሆነ ጠየቅኳቸው። መጽሐፍ ሻጯ ሌላ ሰው ጠራች እና ጥያቄዬን ነገረችው። ሰውየው መጽሀፉ መኖሩን ዋጋው ግን ሶስት ሺህ ብር መሆኑን ነገረኝ። አለመግባባት መሆኑ ቢገባኝም መጀመሪያ ቁጥሩን ሲጠራው ደነገጥኩ መጽሐፉን ሲያሳየኝ ግን ተረጋጋው።

የአፄ ኃይለሥላሴ ምስል የታተመበት የንጉሰ ነገስቱ ህገ መንግስት እና ሌሎች መዛግብቶች ያሉበት በለ ብዙ ገጽ ጥራዝ ነው።

"አይ እኔ የምፈልገው የዘንድሮውን ነው። ዋጋው ስንት ነው?"

"እሱ እንኳን ከ 50 ብር አይበልጥም።"

"እሺ ይሁን ስጠኝ"

"የለንም ጨርሰናል"

"በአገልግሎት ላይ ያለው ህገ መንግስት ዋጋው 50 ብር ሆኖ የላችሁም። በአገልግሎት ላይ የሌለው ህገ መንግስት ደግሞ 3000 ብር እየተሸጠ እዚህ አለ ለምንድነው?" ስለው እየቀለድኩ መሆኑ ስለገባው ተሳስቀን ተለያየን።

ፍርድ ቤቱ ከመዝለቄ በፊት ማመልከቻ ለማዘጋጀት ከፌደራል ፍርድ ቤቱ ትይዩ የሚገኝ የህግ አማካሪ ቢሮ ውስጥ ገባሁ።

በዚህች አነስተኛ ጠባብ ክፍል ውስጥ የህግ አማካሪው እና ፀኃፊው በጋራ እንግዶቻቸውን ያስተናግዳሉ። ጠበቃው ከኔ በፊት የነበሩትን ሰዎች እያነጋገሩ ገብቼ ወንበር እንድይዝ ጋበዙኝ። የሰዎችን የክስ እና ሙግት ዝርዝር ያለፍላጎቴ እየሰማሁ ቆየሁ። በመሀል ሰዎቹን ይቅርታ ጠይቀው የመጣሁበትን ጉዳይ ጠየቁኝ።

"በመታወቂያዬ ላይ ብሔር ያለ ፍላጎቴ ተጽፎብኛል። ለዚህም ደግሞ በህገ መንግስቱ የሚያስገድድ አንዳችም አንቀጽ ሳይኖር በመመሪያ መረጃውን አስገዳጅ በማድረጋቸው እኔ የምኖርበትን ወረዳ እና መመሪያውን ያወጣውን የአዲስ አበባ መስተዳድር ለመክሰስ ነው የመጣሁት"

ገና አስረድቼ ሳልጨርስ ጥያቄዬ እንደገባቸው እና በፍትነት መልሱን ለመስጠት ቸኩለዋል።

"ይቅርታ ይህቺን ነገር ተመልከታት" ወደ ግርግዳው እየጠቆሙኝ።
"የህግ ምክር አገልግሎት ያስከፍላል" ትላለች።

"እሺ ችግር የለውም" አልኳቸው።

ቀጠሉ "ይሄማ አስተዳደራዊ ጥያቄ ነው። ወረዳውን ሄደህ ብሄር የሚለው ላይ አትፃፉብኝ ነው ማለት ያለብህ። እኔ እራሴ መታወቂያዬ ላይ ብሔር የሚለውን ሲጠይቁኝ ኦፕሽናል ነው ብላቸው ኖሮ ይሄኔ አለማጻፍ እችል ነበር። ስለዚህ 'ብሄር መጠቀስ አማራጭ እንጂ ግዴታ አይደለም' ብለህ አናግራቸው"

"እዚያማ ሄጄያለሁ። ወረዳው ክፍለ ከተማ ላከኝ። ክፍለ ከተማው ደግሞ የወረዳ ፍርድ ቤት ላከኝ። የወረዳው ፍርድ ቤት ወደ ክፍለ ከተማ ፍርድ ቤት ላከኝ። ክፍለ ከተማው ይህ ጉዳይ የዜግነት ጥያቄ ጉዳይ ስለሆነ የፌደራል ፍርድ ቤትን ነው የሚመለከተው ብሎኝ ነው እዚህ የመጣሁት"

"አይ ይህንን ጉዳይ መፍታት የሚችለው ፌደራል ሳይሆን እራሱ መስተዳድሩ ነው። አዋጅ ቁጥር 361/95 ላይ ለአዲስ አበባ መስተዳድር ስልጣኑ ተሰጥቶታል። ስለዚህ ፌደራል አይመለከተውም"

"ይሄንን አዋጅ ማግኘት እችላለሁ?"
"አውጪለት" ብለው ፀሀፊዋን አዘው እንዳነበው የፈለጉትን አንቀጽ አዘጋጅተው ወንበሬን ወደ ፀሀፊዋ እንድቀይር አደረጉኝ። እሳቸው ህገ መንግስት አንድ ቅጂ ሰጥተውኝ ከኔ በኋላ የመጡ ሌሎች ተስተናጋጆችን አስገብተው ካስቀመጡ በኋላ የጀመሩትን የክስ ዝርዝር 'ጠብቁኝ' ካሏቸው ሰዎች ጋር ጮክ ብለው ማውራት ጀመሩ።

የተባለው አዋጅ በኮምፕዩተሩ ላይ ተዘረገፎ፥ ከጫፍ እስከ ጫፍ በወፍ በረር መቃኘቱን ተያያዝኩት። ከኔ ጉዳይ ጋር ተዛማች የሆነ ምንም አንቀጽ ማግኘት አልቻልኩም። እንዲሁ ስዳክር ቆየሁ። ልጅቷ የመጠቆሚያ ቀስቱን ለኔ አቀብላኝ ዝም ብላ ቁጭ አለች። አዋጁ የአዲስ አበባ መስተዳድርን ስልጣንና ኃላፊነት የሚደነግግ ቢሆንም ከኔ ርዕስ ጋር ተቀራራቢነት ያለው ምንም ፍንጭ አላገኘሁም። ህገ መንግስትምን እያገላበጥኩ ቆየሁ።

ጠበቃው ብዙ ሰዎችን እያስተናገዱ ከቆዩ በኋላ ወደ እኔ እያዩ "ምን አገኘህ?"

"ስለ መታወቂያ ማንነት ጉዳይ ምንም የሚገልጽ አስገዳጅ አንቀጽ የለም"
"በቃ ተወው!"
"ማለት?"
"በቃ ተወው ይቅርብህ"
"ለምን?"
"ምንም መፍትሔ የለውም"
"እንዴት የለውም?"
"ጥያቄው የፖለቲካ ጉዳይ ነው። ሚስተር ኤክስ አውጥቶት ሄዷል! አሁን ላንተ ትርፉ ልፋት ብቻ ነው። ተወው"

ሚስተር ኤክስን ማን ይሆን የሚያገናኘኝ?

ማመልከቻ ሊፃፍልኝ እንደማይችል ስለገባኝ ወደ ፍርድ ቤቱ ኃላፊ ገብቼ ማናገር ሳይሻለኝ አይቀርም ብዬ ከጠበቃው ቢሮ ለመውጣት ተነሳሁ። ብድግ እንዳልኩ ጠበቃው በአይናቸው ግርግዳውን ዳግም አሳዩኝ።

ላገኘሁት "ተወው" የተሰኘ የህግ ምክር አገልግሎት መቶ ብር ከፍዬ ወጣሁ።

ወደ ፍርድ ቤቱ ገብቼ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ ቢሮ አንኳኳሁ። የሚከፍት የለም። አጠገብ ካለው ቢሮ የወጣች አንዲት ባለሙያ "እሳቸው ስልጠና ላይ ናቸው ምክትላቸውን አናግራቸው" ብላ ወደ ሌላ ቢሮ መራችኝ።

የመራችኝ ቢሮ ሳንኳኳ "ግቡ" ተባልኩ። ስገባ ምክትል ስራ አስኪያጁ ወንበራቸው ላይ የሉም ግን አንድ ልጅ እግር [ረዳታቸው ይመስለኛል] ፈንጠር ካለው ቦታ ላይ ተቀምጧል። የምክትሉን አለመኖር ነግሮኝ ወደ መረጃ ባለሙያ ይዞኝ ሄደ።

የመረጃ ባለሙያዋ ቢሮ ገባሁ። እዚያው ቢሮ ውስጥ አንድ እድሜው በአርባዎቹ መጀመሪያ የሚሆን ሰው በቢሮ ስልክ እያወራ ተቀምጧል። ጉዳዬን በዝርዝር አስረዳኋት። ባለ ስልኩን እንዳናግረው ጠቁማኝ እስኪጨርስ ጠበቅኩ።

ሰውየው ስልኩን እንደጨረሰ የመጣሁበትን ጉዳይ እንዳስረዳው ነገረችኝ። ጉዳዩን ከስር ከመሰረቱ አስረዳሁት። ሰውየው አንደበተ ርቱዕ ነው በዚያ ላይ ሲናገር እኔን አንቱ እያለ በታላቅ አክብሮት ነው።

"የእርስዎ ጥያቄ መስተዳድሩ ባወጣው መመሪያ መሰረት አልተስተናገድኩም ቢሆን ኖሮ ልክ ነዋት። ክስዎን እዚህ ሊያቀርቡ ይችሉ ነበር። ነገር ግን የእርስዎ ጥያቄ 'መመሪያው እራሱ ህገ መንግስቱን ይፃረራል' የሚል ስለሆነ 'መመሪያውን ያወጣው አካል ህገ መንግስቱን አላከበረም' በሚል ለህገ መንግስት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማለትም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው ክስዎን በማመልከቻ ማቅረብ ያለብዎ።"

ሰውዬው የህግ ባለሙያ እንዳማክር የግል ምክራቸውን በመስጠት መፍትሄውን ማግኘት የምችለው ፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን ከዚያ አስቀድሜ ግን ተዋረዱን ለመጠበቅ መመሪያውን ያወጣውን የአዲስ አበባ መስተዳድር የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ለፎርማሊቲው እንዳናግር መክረው በጥሩ መስተንግዶ አሰናበቱኝ።

መመሪያ ያወጣውን ኤጀንሲ ኃሳብ ሰምቼ የህግ ባለሙያም አማክሬ ክሴን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በማመልከቻ ለማቅረብ የሚቀጥለው ሳምንት አቅጄያለሁ።

እዚያ ሚስተር ኤክስን አገኛቸው ይሆን?
ኢትዮጵያዊነት ፍለጋ ይቀጣላል!!

ሠላም ለኢትዮጵያ!!

No comments