ኢትዮጵያዊቷ በግ! (ዘውድአለም ታደሠ)
ኮንዶሚኒየም መኖር ችግር ነው! ሁሉም ዶሮና በጉን በሩ ላይ አስሮ ብሎካችንን ኤልፎራ አስመስሏታል። እኔም ሚስቴ በግ ካልገዛህ እያለች ስትነተርከኝ ጥቂት ብር ይዤ በግ ልገዛ ብወጣ አንድ ቀውላላ በግ ነጋዴ ሁለት ፊታቸው ላይ ከባድ ድብርት የሚታይ ከሲታ በጎች ይዞ ቆሞ አገኘሁና ጠጋ ብዬ
«ልትሸጣቸው ነው?» አልኩት
«እና ሐገር ላስጎበኛቸው ነው ካገሬ ይዣቸው የወጣሁት?» አለኝ
«እንደው ኩነኔ አይሆንም እነዚህን መግደል?» ስለው ፈጠን ብሎ
«አንቀህ ነው እንዴ ምትገድላቸው?» አለኝ
«አይ ያው በቢላም ቢሆን ...» ብዬ ሳልጨርስ
«ወንድሜ ካሳዘኑህ ውሰድና በጉዲፈቻ አሳድጋቸው» አለኝ
«እሺ ስንት ነች እቺ?» አልኩት ወደ አንዷ እየጠቆምኩ
«እሺ ስንት ነች እቺ?» አልኩት ወደ አንዷ እየጠቆምኩ
«በግ ታውቃለህ ማለት ነው። በጣም አስተዋይ በግ ነች እሷ» ብሎ ጀርባዋን መታ መታ ሲያደርጋት ወደጎን ፍንግል አለችና አቧራዋን አራግፋ ተነሳች።
«እኔ አስተውሎቷ ምን ይሰራልኛል ላስተምራት አይደለም እኮ ምወስዳት» ስለው
«ሁለት ሺ ብር ክፈል» አለኝ
«ሁለት ሺ ብርማ አታወጣም»
«በርግጥ ላታወጣ ትችላለች ነገር ግን እኔ ሁለት ሺ ብር ነው የሚያስፈልገኝ»
«ቀንስና ልውሰድልህ» አልኩት
«አይ ወዳጄ በጓን ግን አይተሃታል? ውስጠ ወይራ እኮ ነች። መፍዘዟን አትይ። በዚያ ላይ በእንክብካቤ ነው ያደለብኳት»
«ጭራሽ ደልባ ነው እንዲህ የከሳችው?»
«አዎና! በርግጥ እኔ ስብእናዋ ላይ ነው የሰራሁት። በጥሩ ስነምግባር ነው ያሳደግኋት» አለኝ ቆፍጠን ብሎ። ሳቄን ለመቆጣጠር እየሞከርኩ
«አንድ ሺ ብር ትሸጥልኛለ ...?» ብዬ ሳልጨርስ
«ውሰዳት!» አለኝ በደስታ ተሞልቶ። ምነው ዝም ባልኩ ብዬ በይሉኝታ አንድ ሺ ብር ሰጥቼው በጓን ይዤ ልሄድ ስል መራመድ አቅቷት በቀስታ ስታዘግም
«ቃሬዛ ቢኖርኮ ደግ ነበር» አለኝ ሰውዬው በጉን በሃዘን እየሸኘ። ተበሳጭቼ ዝም ብዬው ስሄድ
«ወንድሜ እንደው ለነፍስ ትሆንሃለች መጀመሪያ የህክምና እርዳታ አርግላት» አለኝ
መንገድ ላይ በጓን ያየ ሁሉ ከንፈሩን እየመጠጠ ያልፋል። አንዳንዱ እኔን እያየ አንገቱን በሃዘን ይነቀንቃል። በግ ላርድ ሳይሆን እንደአብርሃም ልጄን ልሰዋ ይዤ እየሄድኩ ነው ያስመሰሉት። ሽምቅቅ እንዳልኩ ቤት ደረስኩ። ሚስቴ በጓን እንዳየቻት
መንገድ ላይ በጓን ያየ ሁሉ ከንፈሩን እየመጠጠ ያልፋል። አንዳንዱ እኔን እያየ አንገቱን በሃዘን ይነቀንቃል። በግ ላርድ ሳይሆን እንደአብርሃም ልጄን ልሰዋ ይዤ እየሄድኩ ነው ያስመሰሉት። ሽምቅቅ እንዳልኩ ቤት ደረስኩ። ሚስቴ በጓን እንዳየቻት
«ምንድነው ይዘህብኝ የመጣኸው?» ብላ ጮኸች። በጩኸቷ ከኔ ይልቅ የደነገጠችው በጓ ነች። አይኗን አስለምልማ መሬት ወደቀች! የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ላደርግላት ሞከርኩ። አልነቃ ስትለኝ በአፌ ትንፋሽ ልሰጣት ሳጎነብስ ሚስቴ
«በዚህ አፍህ እኔ ከንፈር ጋር ድርሽ እንደማትል እወቀው!» ስትለኝ ቀና ብዬ መጨረሻዋን ማየት ጀመርኩ ... ለብዙ ደቂቃዎች ስታጣጥር ቆይታ ኢትዮጵያዊ የነበረችው በግ በስተመጨረሻ ኢትዮጵያ ሆነች!
ነፍስ ይማር ... ብላችሁ ደሜን እንዳታፈሉት!
ነፍስ ይማር ... ብላችሁ ደሜን እንዳታፈሉት!
No comments