የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ (ኤፍ.ቢ.ሲ)
ተቀማጭነታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የበርካታ ሀገራት አምባሳደሮች ለ2011 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የደስታ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሜሪካው አምባሳደር ማይከል ራይነር፥ ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች መልካም አዲስ ዓመት አንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገለፅዋል።
አምባሳደሩ አክለውም አዲሱ የ2011 ዓመት ለኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም ከነበሩ አዲስ ዓመቶች በበለጠ ተስፋን ይዞ የመጣ ነው ያሉ ሲሆን፥ ይህ ተስፋ እውን እንዲሆንም ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ብለዋል።
አምባሳደሩ አክለውም፥ በአዲሱ ዓመት የህዝቡን አንድነት ለመከፋፈል እና ብጥብጥ ለማስነሳት የሚነዙ ሀሳቦችን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊከላከለው እና አንድነቱን በሚያጠባክሩ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር ይገባል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሁሉም የአሜሪካ ኤምባሲ ሰራተኞች በአዲሱ የ2011 ዓመት ለኢትዮጵያ እድገት የበኩላቸውን ለመወጣት ከምንጊዜውም በበለጠ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ኡሉሶይ፥ መጪው አዲስ ዓመት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የስኬት ዘመን እንዲሆን፣ የበለጠ ጠንካራ፣ የተረጋጋች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን የምናይበት ዘመን እንዲሆን እንመኛለን ብለዋል።
የህንድ አምባሳደር አኑራግ ስሪቫስታቫ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ የተጀመረው የይቅርታና የእርቅ ሂደት እንዲሁም በሀገሪቱ ብሎም በቀጠናው ተስፋ የፈነጠቁት ጥልቅ ማሻሻያዎች ከግብ የሚደርሱበት ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል።
የስዊድን አምባሳደር ቶርብጆርን ፔተርሰን በኢትዮጵያ የሚታየው የዴሞክራሲ ተስፋ እንዲሁም ፈርጀ ብዙ ማሻሻያዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጃመስ ሞርጋን፥ አዲሱ ዓመት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ በሀገራቸው እንዲሁም በቀጠናው ያመጡት የሰላምና ብልፅግና ጮራ ይበልጥ የሚያበራበት ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል።
የዴንማርክ፣ ፊንላንድ ፣ ኮሪያ እና አውስትራሊያ አምባሳዳሮችም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕከት ማስተላለፋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስታውቋል።
No comments