Ethiopianism

ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

መንግስት የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ህገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ይወጣል!

በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እጅግ ተስፋ ሰጪ ከመሆኑም በላይ ዘለቄታዊ ጠቀሜታው ከአገራችን አልፎ ለአጎራባችና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ትምህርትና ተምሳሌት እንደሆነ ዕውቅ የዓለም የፖለቲካ ተንታኞች እና ተቋማት እየመሰከሩለት ያለ አስደማሚ ሂደት ነው።

ይሁንና ግን ለውጡን ከለውጥ አመራሩ እና መላው ህዝብ ጎን በመሆን ከመረባረብ ባፈነገጠ መንገድ እንዲጓዝ የሚሹ ቡድኖች ሰሞኑን በቡራዩ እና በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ባስነሱት ግጭት ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት ጠፍቷል፣ የዜጎች ጥሪትም ወድሟል፡፡

በዚህ መንግስትና ህዝባችን የተሰማቸውን ሀዘን ሲገልጹ ድሪጊቱ የትኛውንም ብሄር የማይወክል ክስተቱም ለውጡን ሊያፋጥን እንጂ ሊያደበዝዝ እንደማይችል በማረጋገጥ ነው፡፡

የንፁሃን ዜጎቻችንን ደም በማፍሰስ፣ አካል በማጉደል እና ለዓመታት ለፍተው የቋጠሩትን ጥሪትና ሃብትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም ሃገር እንደሃገርና መላው ህዝብ የደገፈውንና የሚረባረብለትን የለውጥ ጉዞ ለማጠልሸት መሥራትም ሃፍረት እንጂ ለማንም ቢሆን ተጨማሪ ትርፍ የለውም፡፡

ሁኔታው ለጊዜው ዜጎቻችን ተረጋግተው የዕለት ተዕለት ሥራቸውን እንዳይሠሩ፣ መንግሥትም ከታላላቅ አገራዊ የለውጥ አጀንዳዎች ይልቅ በጸጥታ ጉዳዮች ላይ እንዲጠመድ ብሎም አገራችን በውጪው ዓለም ያላት ገጽታ እንዲኮስስ በማድረግ ረገድ ጉዳት እያስከተለብን መሆኑ አይካድም፡፡

በተደጋጋሚ በህዝብ አደባባይ ህዝቡና እሱን የወከለው አካል ሁሉ የኢትዮጵያን ሰላም፣ ልማት፣ እድገትና ብልጽግና እንጂ ብጥብጥና ሁከት፣ ወይም ድህነትና ኋላቀርነት የሚመኝ አለመሆኑን ገልጿል፡፡

ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ሁሉ በተጨባጭ እንደታየው ወንጀለኞችን እየለየ ለህግ በማቅረብ፣ የተዘረፉ ንብረቶችን ለባለንብረቶች በማስመለስ፣ የተፈናቀሉ ወገኖቹን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው በመመለስ ፈጣንና ርህራሄ የተሞላበት ድጋፉን ሲያደርግ ማየት ከምንም በላይ የሚያኮራና እኩይ ድርጊቶችንም እያወገዘ እንዳለ የሚያስገነዝብ ተግባር ነው፡፡

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ማሸነፍ እና ሥልጣን መያዝ የሚቻለው የተሻለ ሃሳብ በማመንጨት እና በሃሳብ ተወዳድሮ በማሸነፍ እንጂ በአመጽና በሃይል ሊሆን እንደማይችል መንግሥት በጥብቅ ለማስገንዘብ ይወዳል።

በተጨማሪም ከሰላማዊና ህጋዊ አካሄድ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ፖለቲካዊ አፍራሽ እንቅስቃሴ ቀዩን መስመር መተላለፍ መሆኑም እንዲታወቅ መንግሥት ያሳስባል።

የህግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ መላው ኢትዮጵያውያን የሚመኟቸው ሰላም፣ ልማት፣ እና ዴሞክራሲ ዘላቂ ህልውና ሊኖራቸው እንደማይችል አጥብቆ የሚገነዘበው የኢፌዴሪ መንግሥት የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ሃላፊነቱን ሳያወላዳ መወጣቱን እንደሚቀጥል ያረጋግጣል፡፡
መንግስት የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ህገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ይወጣል!

No comments