Ethiopianism

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጥቅም ለአሁኗና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ - ክፍል ~ ፩ (ከፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ )

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጥቅም ለአሁኗና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ - ክፍል ~ ፩ (ከፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ )

ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ 

“ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” ብለው አንድነታችንን የሚያጠናክር ንግግር ሲናገሩ የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ጥቅም በሚገባ እንደ ገለጹት ተረድተናል።

ቀጥለውም ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ መውሰድ ይቻላል! ነገር ግን ከኢትዮጵያዊ ልብ ኢትዮጵያ ዘላለም አትወጣም ትኖራለች! ብለው የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ጥቅም ደግመው አጉልተውታል። ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ተምሳሌት እንደመሆኗ በብዙ ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ኢትዮጵያ ልዩ ቦታ አላት።

ኢትዮጵያውያን ብዙ ላናውቅና ላንረዳ እንችላለን እንጂ፣ ከኢትዮጵያ ከኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያዊኒዝም አስተሳሰብና ፍልስፍና ተወልዷል። ኢትዮጵያኒዝም የተፈጠረው በኃይማኖትና በፖለቲካ ከጭቆና ውስጥ የነበሩ የጥቁር ዘር ባላቸው ሰዎች ነው።

አፈጣጠሩ አፍሪቃ ለአፍሪቃኖች ትገባለች የሚለውን የፓናፍሪካ ፍልስፍና አስቀድሞ በመጀመሪያ የገለፀ ነው። ሲጠነሰስ ጀምሮ መንፈሳዊነትን ከሰው ልጆች ነፃነት ጋር አጣምሮ አቀናጅቶ አስተባብሮ የተፈጠረ ፍልስፍና ነው።ኢትዮጵያኒዝም በስፋት የተጀመረው 1660 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን ከ1776 ከአሜሪካ የነፃነት ትግል በኋላ እያየለ መጣ። አፍሪቃ/አሜሪቃኖች በአሜሪካ ነፃነት በተፈጠረው ለቀቅ ያለ ሁኔታ በመጠቀም ኢትዮጵያኒዝምን ፈጠሩ።

በ1808 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ቤ/ክ በአሜሪካ አቋቋሙ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና በዓለም ተስፋፋ። የሚገርመው ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም የታወቀ ፍልስፍና ሆኖ አልገባም። ትልቁ ጥያቄ አሁን ኢትዮጵያኖች እንዴት ይህን ፍልስፍና ያዩታል? የሚለው ነው።

ስለ ሐገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ ይጠቅማል ብለው ይሄን ፍልስፍና መመርመርና መወያየት ቢችሉ ጥሩ ነው የሚል አስተያየት አለን። እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ቀላል የምንቆጥረው ኢትዮጵያዊነት በኢትዮጵያኒዝም መልክ በሌሎች ሕዝቦች ዘንድ ያለውን አዎንታዊ ተጽእኖ ብንረዳው የበለጠ ኢትዮጵያዊነታችንን ለማጠናከር ሊረዳንም ይችል ነበር።

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍናን ያስፋፉት እነማን ናቸው? 

ኢትዮጵያኒዝምን በመጀመሪያ ያስፋፉት በ19ኛው ክፍለ ዘመን በመንፈሳዊ ዓለም የተሰማሩት በአሜሪካና በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ቄሶች ናቸው።

በመሠረቱ ዘረኝነት በፖለቲካና በኢኮኖሚ ዓለማዊ ዙሪያ ላይ ብቻ ሳይሆን በጥቁሮች መንፈሳዊ ዓለም ላይም ከባድ ጫና ነበረው። በሃይማኖት ሳይቀር ጥቁርን እንደ ሰይጣን ነጭን እነደ መልዓክ ማየት የተለመደ የነጭ ቄሶች እምነትና ተግባር ነበር።

በመሠረቱ ነፃነት የሚፈልጉ የጥቁር ቄሶች ሁለት ችግሮች ገጠሟቸው፤ የነጭ ቄሶች ሲሰብኩ ጥቁርን እንደ ሉሲፈር (ሰይጣን) ስለሚቆጥሩ የነሱ ቄስ ሆኖ ማገልገል በራሳቸው በጥቁሮች ላይ መንፈሳዊ ኩነናን እንደ መቀበል መስሎ ስለ ታያቸው መቀበል አልዋጥላቸው አለ።

በሁለተኛ ደረጃ የነጭ ቄሶች ለጥቁር ቄሶች ምንም ቢሆን ያመራር ተግባር እንዳያገኙ ከለከሏቸው። ሌላው በጣም ያማረራቸው ደግሞ የነጭ ቄሶች ሲሰብኩ የጥቁር ቄሶች ቀና ብለው ወደ ላይ አምላክን ከማየት ወደ ታች አንገታቸውን ደፍተው ቁልቁል እንዲያዩ አምላክን አሻቅበው እንዳያዩ የነጭ ቄሶች እንዳገዷቸው እንደሳፈሯቸውና እንደ ጨቆኗቸው ይናገራሉ። ጭቆናው እየቀጠለ በሄደ ቁጥር ነጮች በሚቆጣጠሯቸው ቤተክርስቲያን መቀጠል እንዳንገፈገፋቸው ይናገራሉ።

በአንድ በኩል ቤተክ/ያን እንዲቀይሩ ጥያቄ ያቀርባሉ፤ ካልተቀየረ ግን ሌላ ቤተክ/ ለማቋቋም አቋም ይወስዳሉ። ያቀረቡት ጥያቄ ሙሉ የመንፈሳዊ ነፃነት ማግኘት እንደ ምዕመናን ወደ እግዚአብሔርና ወደ ክርስቶስ ካላንዳች ዘረኝነትና አድልዎ የሚያገናኝ ሃይማኖትና ቤተክ/ ፈለጉ።

የነጮች ቤተክ/ ይህንን ጥያቄያቸውን ሊያሟሉ አልቻሉም፤ ስለዚህ አዲስ ቤተክ/ ማቋቋም ወይም የነበረውን ቤተክ/ መቀየር ፈለጉ፤ እናም በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ስሟ የተጠቀሰው ኢትዮጵያ ስለ ሆነች የኢትዮጵያ ቤተክ/ እያሉ ማቋቋም ፈለጉ።

ኢትዮጵያ የጥቁር ሐገር በመሆኗ ሌላው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ስለሚል ያለምንም መድልዎና ዘረኝነት ወደ እግዚአብሔር እምታገናኘን ቤተክ/ ናት ብለው ኢትዮጵያኒዝምን አቋቋሙ።

ይቀጥላል...

No comments