Ethiopianism

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ በነገው የጋዜጠኞች ጥያቄና መልስ ቢጠየቅ ብዬ የማስባቸው. . . አቻምየለህ ታምሩ

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ በነገው የጋዜጠኞች ጥያቄና መልስ ቢጠየቅ ብዬ የማስባቸው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በነገው የጋዜጠኞች ጥያቄና መልስ ላይ ቢጠየቅ መልካም ይሆናል ብዬ የማስባቸው ጥያቄዎች፦

፩. የመዋቅርና የሕግ ለውጥ ሳይካሄድ በተመሳሳይ መንገድ [በአብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ በጎሳ ፌድራሊዝም፣ ሕጋዊነት በሌለው ሕገ መንግሥት፣ መለስ ዜናዊ ባቋቋመው 36 አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ፣ ወዘተ. . . ] እየተሄደ ከመለስ ዜናዊና የሱ ራዕይ አስቀጣይ ከነበረው ከኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዘመን የተለየ ውጤት ማምጣት ይቻላል ወይ?  

የሚቻል ከሆነስ ችግሩን በፈጠረ አስተሳሰብ፣ መዋቅርና አደረጃጀት እየተመሩ በዘላቂነት የተለየ ውጤት ያመጡና አገራዊ ተቋማትን የፈጠሩ አገሮች አሉ ወይ?

፪. ዲሲ በነበረው የጥያቄና መልስ ፕሮግራም በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት እንዳልተፈጸመ ሲነገር ሰምተናል። ለመሆኑ ባለፉት 27 የወያኔ የአገዛዝ ዓመታት የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 269 ስለ ዘር ማጥፋት ወንጀሎች ምንነት ከተብራሩ ዝርዝሮችን ውስጥ በአማራ ላይ ያልተፈጸመ ወንጀል አለን?  

 ሌላው ቢቀር በኦፊሴል የቀረበውና በወያኔ ዘመን ጠፋ የተባለው 2.4 ሚሊዮን አማራ እያለ፤በዚህ መጠን systematically ቁጥር የጎደለ ነገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ይመስል በአማራ ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ለመካድ ሲባል ብቻ በእገሌ ነገድ ላይምኮ እንዲህ ሆኗል፤ እንዲያ ሆኗል ማለት ሞራላዊና ፍትሐዊ ነውን?  

፫. ከመጀመሪያውኑ መታሰር የሌለባቸው የሕሊና ሰዎች ከአመታት የጭካኔ እስርና ስቃይ በኋላ ገላቸው ተተልትሎ፤ ጸጉራቸው በደረቁ ተነቅሎ፤ ጺማቸው ተነጭቶ፤ የእግርና የእጅ ጥፍሮቻቸው በጉጠት ወልቀው፤ በብልታቸው ላይ የታሸገ ውሃ እንዲንጠለጠል ተደርጎ ተኮላሽተው፤ በኤሌክትሪክ ሽቦ ሰውነታቸው ተቃጥሎ ፤ እንደ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተዘቅዝቀው በግፍ ተሰቅለው፤ ሞራላቸው ላሽቆ፤ ትዳራቸው ፈርሶ፤ ቤተሰባቸው ተበትኖ፤ አካላቸው ተጎድቶና ስብዕናቸው ተፍቆ ከጠባቡ የማሰቃያ ቤት መውጣታቸው ብቻ ፍትሕ ነውን?  

በሌላ አነጋገር ሕጻናት ሊቧርቁ ከቤት ወጥተው በስናይፐር እንደወጡ ያስቀሩ፣ በግፍ የረሽኑ፣ በጭካኔ ያሰቃዩ፣ ጥፍር የነቀሉ፣ የዘር ፍሬ ያኮላሹ፣ የዘር ማጥፋት የፈጸሙ፣ እንደ ክርስቶስ በእንጨት ላይ ንጹሐንን እየሰቀሉ ሲያሰቃዩ የኖሩትና ባጠቃላይ የግፍና ጭካኔ ክብረ ወሰን የተቀዳጁ ወንጀለኞች ለፍርድ ሳይቀርቡና ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ ሳይሆኑ የሕሊና እስረኞች ይሰቃዩበት ከነበረው ቦታ መውጣት ብቻ ፍትሕ እየተሰጠ ስለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ሊቀርብ ይችላልን?

፬. የሕወሓቱ ኤፌርት ከኢትዮጵያ ሕዝብ በግፍ የዘረፈው ሀብትና ደርግ ከሕዝብ የወረሰው ንብረት ሳይመለስ ኢኮኖሚያዊ ፍትሕን ማስፈንና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ confidence አግኝቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ስር እንዲሰድ ማድረግ ይቻላል ወይ?

፭. አገዛዙ ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከማስተንፈስ ባሻገር የኢትዮጵያ አየር መንገድ [የተወሰነ ድርሻው]ወደ ግል ይዞታ እንዲሸጥ የታሰበው በምን የኢኮኖሚ አመክንዮ ነው?

No comments