Ethiopianism

መንግስት በህግ ስም ለመግዛት ሳይሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር ይሰራል – ጠ/ሚ ዶክተር ዐቢይ



ጠ/ሚ ዶክተር ዐቢይ

(ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መንግስት በህግ ስም ለመግዛት ሳይሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር እንደሚሰራ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሃገር ጋዜጠኞች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚህ ወቅት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም መንግስት በህግ ስም ለመግዛት ሳይሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የህግ ልዕልና ጥያቄ ውስጥ አይገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የራስን ፍላጎት በሌሎች ላይ በመጫን ሳይሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር እንሰራለን ብለዋል።

ከዚህ አንጻርም ህግ የማያከብርና የማያስከብር መንግስት ህልውና እንደሌለው ጠቅሰው፥ ሁሉም ነገር በህግ አግባብ ይፈጸማልም ነው ያሉት በምላሻቸው።

የዜጎች መፈናቀልና የፀጥታ አካላት ሚና፥ አሁን ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተስተዋለ ካለው ህገ ወጥ ድርጊት ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ በለውጥ ጊዜ ህዝቡ ከሚያሳድረው ተስፋ አንጻር መሰል ክስተቶች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል።

አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች እየተፈናቀሉ በመሆኑ ከዚህ አንጻር እየተወሰደ ያለ እርምጃን በተመለከተ በሰጡት ምላሽም፥ መንግስት ከህግ ልዕልና አንጻር በቂ ዝግጅት በማድረግ በህግ አግባብ ለመዳኘት እየሞከረ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሰጡት ምላሽም አሁን ላይ ከዚህ በፊት የነበረውን አካሄድ ለመቀየር በተሄደበት መንገድ ሁሉም የለውጡ ደጋፊ ካለመሆኑ አንጻር አዳዲስ ችግሮች መታየታቸው የተለመደ መሆኑንም ነው ያነሱት።

ዜጎችን የማፈናቀሉ ጉዳይ የቆየ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን አካሄድ ለመቀየር ብዙ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በየቦታው ግጭት እንዲነሳና ዜጎች እንዲፈናቀሉ የሚያደርጉ ሃይሎች በመኖራቸውም እነዚህ ሃይሎች ስራቸውን እንዳይሰሩ የሚያደርግ ጠንካራ ተቋም መገንባትና ሃሳባቸውን የሚያመክን ህዝብ መፍጠር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን የማፈናቀሉን ጉዳይ ከለውጡ ጋር ማያያዝ ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው፥ ይህ እንዲቆም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት መሆኑን አስታውሰዋል።

መሰል ድርጊቶች ለማስቆም በተሰሩ ስራዎችም አሁን ላይ በጅግጅጋ ለውጦች እየመጡ መሆኑን አስታውሰው፥ ይህ ጉዳይ ዳግም በሌሎች ክልሎች እንዳይከሰት ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋም ብለዋል በምላሻቸው።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጅ ዞን ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ሙሉ በሙሉ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ጠቁመው፥ በምዕራብ ጉጅ ዞንም መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን አውስተዋል።

ለተፈናቃይ ዜጎች ከሚደረገው እርዳታ ጋር በተያያዘም መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘም ከፌደራል የሄዱ የፀጥታ አካላት በትግራይ ክልል ታግተዋል ተብሎ የተናፈሰው ወሬ ስህተት መሆኑን ጠቁመዋል።

በወቅቱ ለስራ ወደ ትግራይ ክልል ያመሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት በተፈጠረ የመረጃ ክፍተት ተይዘው እንደነበር ጠቅሰው፥ ከዛ ውጭ ግን የተፈጠረ ችግር እንዳልነበር አስረድተዋል።

ከፀጥታ መዋቅር ማሻሻያ ጋር በተያያዘም በመከላከያ፣ በፌደራል እና በፖሊስ ሰራዊት እንዲሁም በደህንነት ተቋም ላይ ከለውጡ ጋር አብረው እንዲጓዙና ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲፈጽሙ የሚያስችል ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ይህም ለውጡን ለማስቀጠል ያስችላል ያሉ ሲሆን፥ በፖሊስ ሰራዊት አባላት ላይ ግን ብዙ ስራዎች እንደሚሰሩ አውስተዋል።

በምስራቅ ኢትዮጵያ ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘም የሚደረገው ጣልቃ ገብነት በሃይል ሳይሆን በህግ አግባብና በጥንቃቄ የሚፈጸም መሆኑንም ነው በምላሻቸው ያነሱት።

በወቅቱ የተከሰተው ድርጊት አሳፋሪ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ጋር ተያይዞ በድሬዳዋም በጅቡቲ ዜጎች ላይ የታቀደ ጥቃት በመፈጸም ክልሉን ብቻ ሳይሆን ቀጠናውን ወደ ግጭት ለማስገባት ተሞክሯል ነው ያሉት።

የፍርድ ሂደት መዘግየት፥ በሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃትና ከኢንጅነር ስመኘው ሞት ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን ከማሳወቅና ለፍርድ ከማቅረብ አንጻር መዘግየቶች አሉ የሚል ጥያቄ ተነስቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በምላሻቸው ወንጀለኛን አጣርቶና በትክክለኛ እና በሙያ በተደገፈ መረጃ ተመርኩዞ በማጣራት ፍትህ ለመስጠት በሚኖር የማጣራት ሂደት መዘግየቶች እንደሚፈጠሩ አስረድተዋል።
የተፈጠሩ መዘግየቶችም ጉዳዩን በህግ አግባብ ለመዳኘት ጊዜ ወስዶ ማጣራት ስለሚያስፈልግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮችን ባለሙያዎች መረጃውን አጣርተው ለህዝቡ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

የግልና ማህበራዊ ሚዲያ፥ አሁን አሁን በርካታ የግል ሚዲያ በተለይም የህትመት ሚዲያ ተቋማት በአቅም ማነስ እየተዘጉ በመሆኑ መንግስት በዚህ ላይ ያለውን ሃሳብ የተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

በምላሹም መንግስት ሚዲያው ነጻና ክፍት ሆኖ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና ጥያቄ የመጠየቅ መብት ተሰጥቶታል ተብሏል።

ከዚህ አንጻርም ሚዲያው ራሱን በማደርጀት ትክክለኛና ሙያዊ የሆነ መረጃ ለመስጠት ከግለሰቦች የተሻለ ሆኖ መንቀሳቀስ እንዳለበትም በምላሻቸው አንስተዋል።

ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከመልካም ጎኑ ይልቅ አሉታዊነቱን ይጎላል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፥ ማህበራዊ ሚዲያ ባለቤት አልባና የሚነሳው ትችት ከተቋም ይልቅ ግለሰቦችን የሚመለከት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ ሃላፊነት ከመውሰድ አንጻር ክፍተቶች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ግለሰቦች በሚያሰራጩት መረጃ ችግር እንዳይፈጠር ማሳወቅና ማስተማር የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ አውስተዋል።

ችግር ተፈጥሯል በተባለበት አካባቢ ኢንተርኔት መዝጋትን በተመለከተም አካሄዱ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰው፥ ይህን በማድረግና ቴክኖሎጅን በመገደብ የሚፈጠር ተቃርኖን የማርገቡ ስራ ትክክል አለመሆኑንም በምላሻቸው ተነስቷል።
ከዚህ አንጻር ግን ኢንተርኔትን ዘግቶ የሰው ህይዎት ማትረፍ መልካም ነው ብለዋል፤ ወደ ፊት መሰል ችግሮች ሲከሰቱ ጉዳዩን እልባት የመስጠቱ ጉዳይ በዜጎች ንቃተ ህሊና እንደሚወሰን በመጥቀስ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ለህግ ታራሚዎች በተደረገው ምህረትና ይቅርታ ስለመካተታቸው ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ ቀይ ሽብር በህገ መንግስቱ በምህረት ስለማይካተት እርሳቸው ተጠቃሚ አይሆኑም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

No comments