Ethiopianism

ኦነግ “የመገንጠል” ፖሊሲውን እንዳልቀየረ አስታውቋል - አለማየሁ አንበሴ

ኦነግ “የመገንጠል” ፖሊሲውን እንዳልቀየረ አስታውቋል

“ወሳኙ ህዝብ ነው፤ ከመንግስት የሚጠበቀው ዲሞክራሲውን ማስፋት ነው” ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ

በአሥመራ በተደረገ ድርድር ወደ ሃገር ቤት ተመልሶ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ የወሰነው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፤ ኦሮሚያን የመገንጠል የፖለቲካ ፖሊሲውን እንዳልቀየረ ያስታወቀ ሲሆን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፤ “በጉዳዩ ላይ ወሳኙ ህዝብ ነው፣ ከመንግሥት የሚጠበቀው ዲሞክራሲውን ማስፋት ነው” ብለዋል፡፡  


ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የትጥቅ ትግል ሲያደርግ የቆየው በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ክንፍ፤ ከሰሞኑ በአስመራ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተደረሰው ስምምነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጾ፤ “የመገንጠል ጥያቄን” ጨምሮ የድርጅቱ የቀድሞ የፖለቲካ ፕሮግራሞቹ አሁንም እንደሚቀጥሉ አስታውቋል፡፡  

ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ በኦነግ በኩል ደግሞ ሊቀ መንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳና የአመራር አባላቱ፡- አቶ ኢብሳ ነገዎ፣ አቶ አቶምሳ ኩምሳ፣ አቶ ቶሌራ ኢዳባና አቶ ገመቹ አያና ድርድሩን ማካሄዳቸውን ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።  

በተካሄደው ድርድርም ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ መንግሥትና በኦነግ መካከል የነበረው ጦርነት መገታቱን እንዲሁም ኦነግ ወደ ሃገር ቤት ገብቶ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ስምምነት ላይ መደረሱ ታውቋል፡፡ ከስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች ሥራ ላይ መዋላቸውን የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ኦነግ አስታውቋል፡፡  

በአስመራ በተደረገው ድርድርና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለአዲስ አድማስ ማብራሪያ የሰጡት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤ ኦነግ በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት የመጀመሪያውን ልኡክ ይልካል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ የተደረሰው ስምምነትም ለሃገሪቱ ፖለቲካ በእጅጉ ጠቃሚ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡  

“በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ኦነግ ሽብርተኛ ተብሎ መፈረጁን ተከትሎ፣ የኦሮሚያ ክልል አመራሮችን ጭምር ማሸማቀቂያ መሳሪያ ተደርጎ ነበር” ያሉት ዶ/ር ነገሪ፤ “በኦነግ ስም በርካቶች ታስረው ተሰቃይተዋል፣ በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ የሚገኙ ምሁራን ጭምር በኦነግ ምክንያት ሁልጊዜ በጥርጣሬ ይታዩ ነበር” ብለዋል፡፡
አሁን በተደረሰው ስምምነት መሰረት ከእንግዲህ በኦነግ ስም ሰውን መክሰስና መፈረጅ አይኖርም፤ ይህም ትልቅ ፖለቲካዊ ድል ነው ይላሉ፤ ዶ/ር ነገሪ፡፡

በሌላ በኩል፤ ኦነግ ኦሮሚያን የመገንጠል የቀድሞ ፖሊሲውን እንደሚቀጥልበት አስታውቋል፡፡ በተፈጥሮ ኦሮሚያን ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የመገንጠል ሃሳብ ተግባራዊ ይሆናል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ነገሪ፤ ኦሮሚያ የኢትዮጵያ መሃል በመሆኑ መገንጠል የማይቻል ነው፤ የኦሮሞ ህዝብም የሚያነሳው የመገንጠል ጥያቄ ሳይሆን የዲሞክራሲና የመብት መረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡  

መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ዲሞክራሲን ለማጎልበት ጠንካራ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ያብራሩት የኮሚኒኬሽን ኃላፊው፤ ማንኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ወደ መድረክ መጥቶ ህዝብ የሚወስንበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል፡፡ 

“አንድ የፖለቲካ ድርጅት የፈለገውን አመለካከትና ሃሳብ ይዞ ሲመጣ፣ ዲሞክራሲን በማስፋፋት ህዝብ እንዲወስን ማድረግ ያስፈልጋል” ያሉት ዶ/ር ነገሪ፤ ”ኦሮሚያ ማለት ኢትዮጵያ ናት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ መኖርን የሚመርጥ ነው” ብለዋል፡፡  

በሌላ በኩል፤ የኦነግ አመራሮች ወደ ሃገር ቤት ሲገቡ ክብራቸውን የሚመጥን አቀባበል እንደሚደረግላቸው ገልጸው፤ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ምቹ ሁኔታም ይፈጠራል ብለዋል፡፡

No comments