Ethiopianism

እነ አንዷለም አራጌ ህይወት እንደገና - ቢቢሲ

እነ አንዷለም አራጌ ህይወት እንደገና


"ልጄ ድምፄን ሲሰማ አለቀሰ"
የአንድነት ለፍትህና ዲሞክራሲ ፓርቲ መሪ የነበረው አቶ አንዱአለም አራጌ ካለፉት 12 ዓመታት ስምንት ተኩል የሚሆነውን ያሳለፈው በእስር ነው።

የታሰረው ሁለት ጊዜ ሲሆን በሽብርተኝነት ተከሶ እንደ አውሮፓውያኑ 2011 ላይ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ከስድስት ዓመት በላይ በእስር አሳልፏል። በቅርቡ ከዓመታት እስር በኋላ ከተለቀቁ እስረኞች መካከል አንዱ የሆነው አንዱአለም ከተፈታ አምስት ወራት አልፎታል።

ከዓመታት እስር በኋላ ህይወትን ፤ኑሮን ዳግም እንዴት ጀመርከው ስንል ጠይቀነው ነበር።

  • "እንደምፈታ ያወቅኩት ባለፈው መስከረም ነበር" አንዷለም አራጌ
  • እስክንድር ነጋና አንዷለም አራጌ በይቅርታ ሊፈቱ ነው ተባለ
  • "ህልም አለኝ":-በቀለ ገርባ
ነገሮች በጣም ከባድ እንደነበሩ የሚናገረው አንዱአለም "ባልወደውም እስር ህይወቴ ሆኖ ነበር እና ከዚያ ህይወት ወደዚህ ስመጣ ነገሮች ፈታኝ ሆነውብኝ ነበር"ይላል።

እንግዳ ስለሆነባቸው ልጆቹ ሊቀርቡት ተቸግረው ነበር።በመግለፅ አንድ የተለየ አጋጣሚን ያስታውሳል።

"ተፈትቼ የመጀመሪያው እለት መብራት ጠፍቶ ነበር እና ልጄ ድምፄን ሌሊት ሲሰማ ልክ ሌባ እንደገባ አይነት ነገር ማነው እያለ አለቀሰ" በማለት ከልጆቹ ጋር መቀራረብ ተቸግሮ እንደነበር ይናገራል።

እስር በአዲስ አበባ እና በባህር ዳር
ማህበራዊ ትስስሩ ከሰዎች ጋር መቀራረቡም ሌላ አስቸጋሪ የሆነበት ነገር ነው። ለአመታት ብቻውን መኖሩ አሁን በሰው መሃል መገኘት ፣ እንደ ካፍቴሪያ ያሉ ቦታዎች ላይ ብዙ ድምፆችን መስማት ምቾት እንዲነሳው አድርጓል።

አንድ አካባቢ ላይ የብዙ ሰዎች መገኘትም ይረብሸዋል። "ሁሉም ነገር ለእኔ እንግዳ ስለሆነ የተንሳፈፍኩ ያህል ይሰማኛል። እውነቱን ለመናገር ገና መሬት አልረገጥኩም"ይላል አንዱዓለም።

መንገድ ላይ መንቀሳቀስ ፣ ሻይ ቤቶች ውስጥ ከሰዎች ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መጫወት ይደሰትባቸው ነፃነት እንዲሰማው ያደርጉ የነበሩ ነገሮች ነበሩ።

"እስር ቤት ሆኜ ሁሌም ይናፍቀኝና ከህይወቴ አጣሁት የምለው ጠዋት ከሶስት እስከ አራት ሰዓት ላይ ፀሃይ እየሞቅኩ አንድ ጥግ ላይ ሆነ እያሰብኩ ወይም ጋዜጣ እያነበብኩ ማኪያቶ መጠጣት ነበር" በማለት በትዝታ ወደ ኋላ ይመለሳል።

የሚያዘወትረው አራት ኪሎና ከአራት ኪሎ መገናኛ በሚወስደው መንገድ በተለምዶ ቤሊየር ተብሎ የሚጠራ አካባቢ ያለ ካፍቴሪያን ነበር።

ዛሬ የቅርብ ወዳጆቼ የሚላቸው አገር ውስጥ ባይኖሩም አሁንም ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ሻይ ቡና ቢልም አሁን መሄድ ስለማይፈልግ አራት ኪሎ ግን ትዝታው ሆና ቀርታለች።

"አራት ኪሎ ስሄድ ድሮ የማውቃቸውን ሰዎች አላይም።ከዘመኑ ጋር ሰዎች አልፈዋል ቦታዎቹም ተቀያይረዋል።ያለ እነሱ ደግሞ ስሜት አይሰጥም ባይተዋርነትም ይሰማኛል"ይላል።

ቀድሞም ለቴክኖሎጂ እምብዛም ነበርኩ ለሚለው አንዱዓለም እንግዳ የሆነበት ሌላው ነገር ሰዎች ከስልካቸው ጋር ያላቸው ቁርኝት ነው።

ከዓመታት በፊት ቤትም ይሁን ካፍቴሪያ ውስጥ ሰብሰብ ተብሎ ማውራት መጫወትም ነበር። "የትም እንደ ድሮ ከቦ ማውካካት የለም።አንድ ላይ ተቀምጦም ሁሉም ከስልኩ ጋር ነው የሚያወራው።በዚህ የዘመኑን መፍጠን መለወጥ አይበታለው"ብሏል።

"መግቢያ ስላልነበረኝ የ87 ዓመት እናቴ ቤት ነው የገባሁት"
የአራት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ በሽብር ተፈርዶባት ከዘጠኝ ዓመታት እስር በኋላ የተፈታችው በቅርቡ ነው።

ከእስር ስትለቀቅ የአዲስ አበባውን ቤቷን እንደነበር አላገነችውም። "መሳሪያ ደብቃለች ተብሎ ቤቴን አፍርሰውት ነው የጠበቁኝ"በማለት ቤቷ ፈርሶ ልጆቿም ስለተበተኑ ጎንደር የሚገኙት የ87 ዓመት ወላጅ እናቷ ቤት ልትገባ ግድ እንደሆነባት ትናገራለች።

ከደረጀ ኑሮና ቤቷ ወጥታ በዚህ እድሜዋ የእናቷ ጥገኛ መሆን ከባድ እንደሆነ ነገር ግን እናቷ የእድሜ ባለፀጋ ሆነው መጠጊያ ስለሆኗት ፈጣሪዋን እንደምታመሰግን እማዋይሽ ትገልፃለች።

አንዱ ልጇ እሷን እስር ቤት አጥር ውስጥ ማየትን መቋቋም ባለመቻሉ መሰደዱን ትናገራለች።

"አንደኛዋ ልጄ ለዲፕሎማ እየተማረች ነበር።በትምህርቷ ትገፋለች ብዬ አምን የነበረ ቢሆንም ትምህርቷን አቋርጣ ወልዳ ነው ያገኘኋት። ስታሰር የ11 ዓመት የነበረች ልጄ ደግሞ በስደት ኬንያ ትገኛለች" በማለት ልጆቿ እንዴት እንተበተኑባት ትገልፃለች።

በሽብር ስለተከሰሰች መጀመሪያ ላይ ኬሎች እስረኞች ጋር እንድትቀላቀል አይፈቀድላትም ነበር። ኋላ ግን እየሩሳሌም ተስፋው፣ቀለብ ስዩምና በሽብር ታስራ የነበረች ፈቲያ የምትባል ሙስሊም ጓደኞቿ እንደነበሩ ትናገራለች። "ከሪኦት አለሙ ጋር የነበረኝ ጓደኝነት ግን የተለየ ነበር።ሁሉን ተካፍለን ነበር የምንበላው" በማለት ታስታውሳለች።

የቀድሞ የስራ ባልደረቦቿ ጓደኞቿም ከተፈታች በኋላ እንገናኝ የሚሏት ቢሆንም "በደከምኩበት የሞትኩበት በመሆኑ በብዛት የማገኘው የእስር ቤት ጓደኞቼን ነው" ትላለች።

"የእስር ቤት ጓደኝነት ስሜት የሚነካ ነው"
ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ በሽብር ተፈርዶበት ሰባት ዓመታትን በእስር አሳልፏል። ከተፈታ አምስት ወር የሆነው ውብሸት አብዛኛው እስረኛ በህክምና እጦትና በድብደባ የጤና ችግር እንደሚያጋጥመውና እሱም ከእስር ህመም ይዞ እንደወጣ ይናገራል።

ብዙዎች ከእስር በመለቀቃቸው ተደስተው ሳይጨርሱ ከዘመድ ወዳጅ ጋር ሆነው ያላወጡት የእናት የአባት እንዲሁም የእህት የወንድም ሞት እርምን ለማውጣት አንብተዋል ልባቸውም ተሰብሯል።

አባቱ የሞቱት በእስር ላይ እያለ በመሆኑ ውብሸትም በዚህ የሚሰብር ስሜት ውስጥ ሊያልፍ ግድ ሆኖበታል።

"እኔ እድለኛ ስለሆንኩ ትዳሬ አልፈረሰም ሚስቴ ሸክሜን ተሸክማልኝ ኖራለች"የሚለው ውብሸት የሚያውቃቸው ብዙዎቸ ከስር ሲወጡ ትዳራቸው ፈርሶ ማግኘታቸውን ይናገራል።

ወደ ኑሮ ለመመለስ ወይም አዲስ ነገር ለመጀመር አሲስ አለም አዲስ አገር ላይ ያሉ እስኪመስል ድረስ ነገሮች በጣም ፈታኝ እንደሆኑ "ሲስተም ውስጥ መግባት በጣም ከብዶኛል" በማለት ስሜቱን ይገልፃል።

ከሁሉም በላይ ሲታሰር የሁለት አመት ከሰባት ወር ልጅ ከነበረውና አሁን 10 ዓመት ከሆነው ልጁ ጋር መቀራረብ ከብዶታል።

"ልጄ በጥርጣሬ ነው የሚያየኝ"የሚለው ውብሸት እንደ አባት ሳይሆን እንደ እንግዳ እንደ ውጭ ሰው የገዛ ልጁን አባብሎ እንደሚቀርበው ይናገራል።

እንደሚለው እስር ላይ እያለ ምንም እንኳ ባለቤቱ ልጁ እንዲያየው ቢያደርግም ልጁን መንካትም ሆነ ማቀፍ አይፈቀድለትም ነበር።ስለዚህም ባለፉት አመታት ሁሉ ልጁ አባቱን ከአጥር ጀርባ መመልከቱ ለዛሬው ስሜቱ ምክንያት ሆኗል።

ብዙ ጓደኞቹ በመሰደዳቸው ከቀድሞ ጓደኞቹ የሚያገኛቸው ጥቂት ናቸው። የእስር ቤት ጓደኝነት ስሜት የሚነካና ጥልቅ እንደሆነ የሚናገረው ውብሸትበ በአሁኑ ወቅት አብረውት ታስረው ከነበሩ ጋር እንደሚገናኝ ይናገራል።

No comments