Ethiopianism

ፍኖተ ካርታው ወደ ቀድሞ የትምህርት ፖሊሲ ሊመልሰን ይሆን ? ቢቢሲ

ፍኖተ ካርታው ወደ ቀድሞ የትምህርት ፖሊሲ ሊመልሰን ይሆን ?

ይፋ የሆነው ፍኖተ ካርታ ሰፊ መዋቅሮችን ያካተተ በመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴርን በሶስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የሚያደራጅ መሆኑ ተነግሯል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹም የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ሚኒስቴር፣ አጠቃላይ የትምህርት ስልጠና ሚኒስቴርና የክህሎትና ፈጠራ ሚኒስቴር መሆናቸው ተነግሯል።

ለሁለት ዓመታት ጥናት ሲደረግበት የቆየው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ነሐሴ 14፣ 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚንስትር ፅ/ቤት ይፋ ተደርጓል። የቀረበውን ጥናት መሰረት በማድረግም ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዷ የሆኑት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር በርሄ "የፍኖተ ካርታው እየተተገበረ ያለውን የትምህርት ፖሊሲ ውጤቶችንና ተግዳሮቶቹን በመለየት የቀረበ ነው'' ይላሉ።

ውይይቱ በቡድን ተከፋፍሎ የተካሄደና በእያንዳንዱ ቡድን ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የትምህርት ባለሙያዎችና መምህራን የተሰባጠረ ነው።

ከተነሱት ተግዳሮቶች መካከል የጎልማሶች ትምህርት ውጤታማ አለመሆኑና አሁንም በርካታ ያልተማሩ ወገኖች መኖራቸው ተነግሯል።

ህፃናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በ7 ዓመት ዕድሜያቸው እንዲጀምሩ እና ከዚህ ቀደም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እስከ ስምንተኛ ክፍል የነበረው እስከ ስድስት ቢሆንና ለከፍተኛ ትምህርት የሚዘጋጁበት አራት ዓመት እንዲሆን ጥናቱ ጥቁሟል ሲሉ ወ/ሮ አስቴር ተናግረዋል።

ወ/ሮ አስቴር፤ የመምህራንና ባለሙያዎች ጥቅማ ጥቅም፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ችግር፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ሶስት ዓመት የነበረው ወደ አራት ዓመት ከፍ እንዲል፣ የአማርኛ ቋንቋና እንግሊዝኛ ቋንቋ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲሰጥ የተነሳበት ነው ሲሉ ከብዙ በጥቂቱ ይገልፃሉ።

ወ/ሮ አስቴር "የአተገባበር ችግር ስላለ ነው እንጂ ቀድሞ የነበረው ፖሊሲ የአማርኛ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲሰጥ ያዛል" ይላሉ አሁን በትግበራ ላይ ያለው ፖሊሲ ቀረፃ ላይ እንደተሳተፉ በማስታወስ።

ሌሎች ትምህርት ጋር የተገኛኙ ጉዳዮችም ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልፀውልናል።


አጥኝዎቹ ምን ይላሉ?
"ከማህበረሰቡ በርካታ ትምህርት ነክ ጉዳዮች ሲነሱ ቆይተዋል" ይላሉ ከአጥኝዎች አንዱ የሆኑትን ዶ/ር ፈቀደ ቱሊ።

እነዚህንም ጥያቄዎች ለመፍታት በትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የጥናት ቡድን ተዋቅሮ እስካሁን በትምህርት ስርዓቱ የተመዘገቡ ውጤቶችና ስርዓቱ ውስጥ ያሉ ክፍተቶች፣ ወደፊት እንዴት ይሻሻላል በሚል ጥናቱ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል።

የፍኖተ ካርታውም ቅድመ መደበኛ ትምህርትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት፣ የትምህርት አስተዳደር ጉዳይ በሚል ተከፋፍሎ በ36 አጥኝዎች መካሄዱን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ጥናቱ ጥልቅና ሰፊ በመሆኑ የተገኙ ውጤቶችን አንድ ሁለት ብሎ መዘርዝር ያዳግታል ሲሉ በደምሳሳው አልፈውታል።

በፍኖተ ካርታው የተነሱ ነጥቦች ወደ ድሮው የትምህርት ስርዓት ሊመልሰን ይችላል ወይ ያልናቸው ባለሙያው፤ "የተሻለ ሆኖ ከተገኘ ሃሳብ መውሰዱ ጉዳት ባይኖረውም፤ ይህ ግን ወደ ድሮው የትምህርት ስርዓት የሚመልስ አይደለም። ምን አልባት በአንዳንድ ነጥቦች ላይ የመመሳሰል ነገር ሊኖረው ይችላል። ለመመለስ ዘመኑም አይፈቅድም" ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የፍኖተ ካርታ ጥናቱን እንደ ትምህርት ፖሊሲ ተደርገው እየተወሰዱ መሆናቸውን ያነሳንላቸው ዶክተር ፈቀደ፤ "ከየት አምጥተው እንደሆነ አይገባኝም፤ ፍኖተ ካርታው ረቂቅ በመሆኑ መረጃ የማሰባሰብ ሂደቱ እንደ ቀጠለ ነው፤ ህዝቡ ሳይወያይበትና ጥናቱ ዳብሮ ለሚመለከተው አካል ሳይቀርብ ወደ ፖሊሲ የሚለወጥበት ምንም ምክንያት የለም" ሲሉ መልሰዋል።

ተሳታፊዎቹ እነማን ናቸው?
በረቂቅ ፍኖተ ካርታው ጥናት ውይይት ላይ ከ1300 በላይ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ተሳታፊዎቹም ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የትምህርት ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የትምህርትና ስልጠና ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ሎሎች ባለ ድርሻ አካላትም ተገኝተዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ቀጣይ 
ርምጃ

ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ መምህራን፣ ተማሪዎችና፣ ህብረተሰቡና በትምህርት ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ከመጭው መስከረም ጀምሮ ውይይት እንደሚደረግበት በትምህርት ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር ወ/ሮ ሀረጓ ማሞ ገልፀዋል።

ይህ ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላም ወደ 15 ዓመቱ ዕቅድ ይካተታል የሚባሉት ሃሳቦች ተካተው ፍኖተ ካርታው ይዘጋጃል።

ምንም እንኳን ረቂቅ ፍኖተ ካርታው ያልተጠናቀቀ በመሆኑ አሁን ላይ የቀረበው ፍኖተ ካርታ የፖሊሲ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል አይችልም ብሎ መናገር ባይቻልም፤ የህብረተሰቡን ውይይት መነሻ በማድረግ ሃሳቡን አፅድቆ ወደ ቀጣይ ተግባር መሸጋገሩ ግን አይቀርም ብለዋል።

No comments