በሆሄ የስነ ጽሁፍ ሽልማት በእውቀቱ ስዩም፣ አለማየሁ ገላጋይና ዳንኤል ወርቁ ተሸለሙ
(ቢቢሲ) - ለንባብ ከበቁ መፃሕፍት መካከል በአንባቢዎች እንዲሁም በሥነ-ጽሁፍ ሀያሲያን ዓይን የተደነቁ ሥራዎች የሚሞገሱበት ሆሄ የሥነ-ጽሁፍ ሽልማት በይፋ ከተጀመረ ዓመት ሞላው።
በሆሄ፤ በተለያዩ የሥነ-ጽሁፍ ዘርፎች የላቀ ሥራ ያበረከቱ ጸሃፍት ይሸለማሉ። የሥነ-ጽሁፉ ባለውለታዎችም ይሞገሳሉ።
የዘንድሮው የሆሄ ሽልማት ሲካሄድ በረዥም ልቦለድ ዘርፍ አለማየሁ ገላጋይ "በፍቅር ስም" በተሰኘ መጽሀፉ፣ በልጆች መፃሕፍት ዘርፍ ዳንኤል ወርቁ "ቴዎድሮስ" በተባለ ሥራውና በእውቀቱ ስዩም "የማለዳ ድባብ" በሚለው የግጥም መድበሉ ለሽልማት በቅተዋል።
ለዓመታት መፃሕፍትና አንባቢዎችን በማገናኘት የሚታወቁት መፅሐፍ ሻጩ ተስፋዬ አዳል፣ እንዲሁም እውቆቹ ጸሃፍት ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ፣ አማረ ማሞ እንዲሁም የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር ስለ አበርክቷቸው ተመስግነዋል።
"ደራስያን ያላቸው ሀብት እውቅና ማግኘት ነው" የሚለው ዳንኤል ወርቁ፤ ከላይ የተጠቀሱት አንጋፋ ጸሀፍት በተመሰገኑበት መድረክ በመሸለሙ ክብር እንደሚሰማው ይናጋራል። ሥነ-ጽሁፍ ደጋግሞ እየወደቀ በሚነሳበት ሀገር መሰል ሽልማቶች ቢበራከቱ ደራስያንን እንደሚያበረታቱም ያምናል።
የሥነ-ጽሁፍ ሽልማቶች ለደራስያን እውቅና ከመስጠት ባሻገር ለማህበረሰቡ "እስኪ ይህን መፅሐፍ አንብቡ" የሚል መልዕክት በማስተጋባት ዘርፉን ማበረታታቸው እሙን ነው።
ሆሄ በየዓመቱ ከሚታተሙ መፃሕፍት መካከል በሥነ-ጽሁፍ መስፈርቶች የተሻሉ የሚባሉትን በሙያተኞች ያስገመግማል። አንባቢያንም ድምጽ በመስጠት የወደዱትን መጽሐፍ እንዲጠቁሙ እድል ይሰጣቸዋል።
"የንባብ ባህሉ አልዳበረም" እየተባለ በሚተች ማህበረሰብ ውስጥ መጽሐፍ አሳትሞ አመርቂ ውጤት ማግኘት ፈታኝ መሆኑን የሚናገረው ዳንኤል፤ የሥነ-ጽሁፍ ሽልማቶች መፃሕፍትና ደራሲያንን አስከብረው ዘርፉንም እንደሚያሳድጉ ተስፋ ያደርጋል።
ዳንኤል እየተዳከመ የመጣው የረዥም ልቦለድ መጻሕፍት ህትመት እንዲሁም ብዙም ትኩረት ያልተቸረው የልጆች መጻሕፍት ዘርፍ በሽልማቱ መካታቸውን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በሥነ-ጽሁፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎችም ሽልማት መስጠት አዲሰ አይደለም። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅትና የ1990ዎቹ የኪነ-ጥበባትና መገናኛ ብዙኃን ድርጅትም አይዘነጉም። ሁለቱም ግን መዝለቅ አልቻሉም።
ከሁለቱ ሽልማቶች በተጨማሪ በግለሰቦች ተነሳሽነት የተጀመሩ ሽልማቶችም ይጠቀሳሉ። ሆኖም ብዙዎቹ ከጥቂት ዓመታት ሲሻገሩ አይስተዋልም።
ሆሄ የተወጠነው ለዘርፉ አስተዋጽኦ በማበርከት እንዲዘልቅ ቢሆንም የአቅም ውስንነት እንደሚፈታተናቸው የሽልማቱ አስተባባሪ ዘላለም ምሕረቱ ይናገራል። ከዚህ ቀደም ተጀምረው የተቋረጡ ሽልማቶች ተመሳሳይ ተግዳሮት አንደነበረባቸው ደራሲው ዳንኤልም ይገምታል።
ዘላለምና ዳንኤል መሰል የሽልማት መሰናዶዎች ድጋፍ ካልተደረገላቸው ቀጣይነታቸው እንደማያስተማምን ይስማሙበታል።
መጽሀፍ ሻጩ ተስፋዬ አዳል ለአበርክቷቸው ተመስግነዋል |
በዘላላም ገለጻ "ብዙዎች መርሀ ግብሩን ይወዱታል። በገንዘብ መደገፍ ላይ ግን ሁሉም ወደ ኋላ ይላል። ገንዘባቸውን 'ትርፋማ ' በሚሏቸው ዘርፎች ማፍሰስ ይመርጣሉ።"
የሽልማት ዝግጅቶች ብዙ ርቀት የማይራመዱት አንድም በበጀት ውስንነት ሲሆን፤ ከሽልማት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የፍትሀዊነት ጥያቄዎች እንቅፋት የሆኑባቸውም ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የሬድዯ መርሀ ግብር ዋና አዘጋጅ ጌታቸው አለሙ አንጋፋና አማተር ደራስያንም ሥራቸው እንደተወደደላቸው የሚመሰከርባቸው የሥነ-ጽሁፍ መድረኮች መበራከት አለባቸው ይላል። መፃሕፍትን የማስተዋወቅ፣ ደራስያንን በአንድ መድረክ የማገናኘት ሚና እንዳላቸውም ያክላል።
"መሰል ሽልማት በትልቅ ተቋም መሰጠት ቢኖርበትም ሆሄ በወጣቶች ተነሳሽነት የተጀመረ ተስፋ ሰጪ ዝግጅት ነው" ሲል ሽልማቱን ይገልጻል።
የሽልማት መሰናዶዎች ደራስያንን ያሸለሙ ሥራዎች ጎልተው እንዲወጡ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲነበቡ፣ የውይይት መነሻ እንዲሆኑም ያበረታታሉ።
No comments