Ethiopianism

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ጳጉሜ አራት አዲስ አበባ ይገባል (ኢሳት ዲሲ)

አርበኞች ግንቦት ሰባት

የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮችንና አባላትን ለመቀበል በአዲስ አበባ የተዋቀረው ኮሚቴ ዝግጅቱን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ።

በመላው ዓለም ያሉት የንቅናቄው አመራርና አባላት ጳጉሜን አራት አዲስ አበባ እንደሚገቡ ለማወቅ ተችሏል።

ትላንት በአዲስ አበባ የስብሰባ ማዕከል በተካሄደው የአቀባበል ኮሚቴው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መገኘታቸው ታውቋል።

ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴን ጨምሮ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች የንቅናቄውን አመራሮች ፎቶግራፍ የሚገኝበት ቲሸርት በመልበስ አቀባበሉን ለማድመቅ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ዋዜማ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከመላው ዓለም የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮችና አባላት አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከአሜሪካ ከአውሮፓ ከአውስትራሊያ ከኤርትራና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የንቅናቄው አመራሮችና አባላት አዲስ አበባ በሚገቡ ጊዜ የደመቀ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅቱ ቀጥሏል።

ናፍቆት በሚል ስያሜ የሚጠራው አቀባበል በከፍተኛ ድምቀት ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም በአዲስ አበባ የተቋቋመው የአቀባበል ኮሚቴ አስታውቋል።

በአዲስ አበባ በየክፍለከተማ በፍቃድ የተቋቋመ ኮሚቴ ለአቀባበሉ ትዕይንት አስተዋጽኦ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ተገልጿል።

ለአርበኞች ግንቦት ሰባት አቀባባል በሚል የተቋቋመው ኮሚቴ የአርበኞች ግንቦት 7 ለዴሞክራሲ እና ለአንድነት ንቅናቄ በሀገር ውስጥ በመግባት በሚያውቀው እና በሚናፍቀው ሠላማዊ እና በዜግነት ላይ በተመሠረተ የፖለቲካ ትግል ለመሳተፍ መወሰኑን በመግለጽ ለዚህ ከ250 በላይ አመራሩና አባላቱ በንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመራት ጳጉሜ 4 ቀን 2010 ዓ·ም ወደ አዲስ አበባ ይገባሉ ሲል መግለጫ ሰጥቷል።

ትላንት በአዲስ አበባ የስብሰባ ማዕከል በተከናወነው ህዝባዊ መድረክ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተገኝተው አቀባበሉን ለማድመቅ ስለሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ሰንድቅ ዓላማ የተዋበውና በንቅናቄ ዋና ጸሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ድርሰት በሆነው ላንቺ ነው ኢትዮጵያ በተሰኘው ዜማ የደመቀው መድረክ የተሳካ እንደነበረ የአቀባበል ኮሚቴ ገልጿል።

በመድረኩ ላይ ታዋቂ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴም ለአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች አድናቆትን በመግለጽ መልዕክት አስተላልፏል።

ጋዜጠኞችና በሰብዓዊ መብት መከበር ትግል ውስጥ ሚና የተጫወቱ ግለሰቦችም ተገኝተዋል። የአቀባበል ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ መላው የአዲስ አበባ ነዋሪም ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህ፣ ለእኩልነት እና ለሀገር አንድነት ሲሉ መስዋዕትነት የከፈሉ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮችና አባላትን ህዝቡ በነቂስ በመውጣት እንዲቀበል እና የአቀባበል ሥነ ሥርዓቱም የተሳካ እንዲሆን የበኩላችሁን እንድታደርጉ እንጠይቃለን ብሏል።

No comments