Ethiopianism

ጃካርታ በውሃ እየተዋጠች ያለችው ከተማ

ጃካርታ በውሃ እየተዋጠች ያለችው ከተማ

(ቢቢሲ) - አስር ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ የሚኖርባት የኢንዶኔዢያዋ ዋና ከተማ ጃካርታ በፍጥነት ውሃ ውስጥ እየሰመጠች መሆኑ ተነግሯል።

ይህም አፋጣኝ እርምጃ ተወስዶ መፍትሄ ካላገኘ ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በውሃ እንደምትዋጥ አጥኚዎች ተናግረዋል።

እንደባለሙያዎቹ በረግረጋማ ስፍራ የተመሰረተችውና 13 ያህል ወንዞችን በውስጧ የያዘችው ጃካርታ በተደጋጋሚ በጎርፍ ትጠቃለች፤ አሁን ግን ሁኔታው በእጅጉ እየከፋ መሆኑንም ተገልጿል።

በዚህም ሳቢያ ይህች ግዙፍ ከተማ በውሃ እየተዋጠች ከምድረ ገፅ እየጠፋች መሆኑም ተነግሯል።

ላለፉት ሃያ ዓመታት በባንዱግ የቴክኖኢሎጂ ኢንስቲቲዩት ውስጥ የጃካርታን በውሃ መዋጥ ሲያጠኑ የቆዩት ሄሪ አንድሪያስ እንደሚሉት "የከተማዋ በውሃ የመዋጥ ነገር በዋዛ የሚታይ ነገር መሆን የለበትም" ብለዋል።

የከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች በውሃ የመዋጥ ክስተት እየታየ ሲሆን በሰሜናዊ ጃካርታ 2.5 ሜትር የመሬት አካል በአስር ዓመታት ውስጥ በውሃ ተውጧል።

ይህም በአንዳንድ አካባቢዎች በ25 ሴንቲ ሜትር በየዓመቱ እየሰመጠ ሲሆን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ባሉ የባሕር ዳርቻዎች ካጋጠመው ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ በላይ የሆነ ክስተት ነው ተብሏል።

ጃካርታ በየዓመቱ በአማካይ ከ አንድ አስከ 15 ሴንቲ ሜትር ድረስ እየሰመጠች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የከተማዋ ግማሽ ያህል ከባህር ጠለል በታች ይገኛል።

No comments